1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

51 ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአሜሪካ

ዓርብ፣ ሰኔ 17 2008

በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አነሳሽነት በተጀመረው የ«ማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ» መርሐ-ግብር እንዲሳተፉ ዘንድሮ 51 ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ አቅንተዋል። ከኢትዮጵያውያኑ ወጣቶቹ መካከል የዞን ዘጠኙ ዘላለም ክብረትም ይገኝበታል።

https://p.dw.com/p/1JDIb
Washington Obama Presidential Summit YALI
ምስል Getty Images/C. Somodevilla

51 ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአሜሪካ

የማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ ይፋ ከሆነ 6 ዓመታትን አስቆጥሯል። ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶም አፍሪቃውያን ወጣቶችን ወደ አሜሪካን በመውሰድ እርስ በእርስ ብሎም አሜሪካን ውስጥ ከሚገኙ ታዋቂ ፖለቲከኞች እና ግለሰቦች ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ እና ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል። በማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ ተሳታፊዎች እድሜያቸው ከ25 እስከ 35 ዓመት የሚደርሱ ወጣቶች ሲሆኑ ዘንድሮ 51 ኢትዮጵያውያን የዕድሉ ተጠቃሚዎች ሆነዋል። የዞን 9 ዓምደ መረብ ጸሓፊ ዘላለም ክብረት ከመርሐ-ግብሩ ተሳታፊዎቹ አንዱ ነው።

«ለአፍሪቃ ወጣት መሪዎች የማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ» የተሰኘው መርሐ-ግብር ይፋ የሆነው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2010 ዓመት ነው። መርሐ-ግብሩ የተጀመረው በአፍሪቃ እድገት እና ብልጽግና፣ ጠንካራ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲሁም ሰላም እና ጸጥታ እንዲጎለብት ለማገዝ በሚል ነው። የአፍሪቃ የወደፊት መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ወጣቶችን አሜሪካን ውስጥ በማሰባሰብ ልምድ እንዲለዋወጡ ዕድሉን ማመቻቸት የመርሐ-ግብሩ ዋነኛ ዓላማ እንደሆነ ይጠቀሳል። ዘንድሮ ዕድሉ የተሰጠው 1000 ለሚሆኑ አፍሪቃውያን ወጣቶች ነው። አምሳ አንዱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ወጣት ዘላለም ክብረት።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት ሞላልኝ በላይ ሁለተኛ ዲግሪውን በማኅበረሰብ ጥናት (sociology) ሠርቷል። ቦስተን ከተማ እስከገባበት ጊዜ ድረስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማስተማር እና የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች ስብስብ ዳይሬክተር በመሆን አገልግሏል። አሜሪካን ሀገር ከመጡት 51 ኢትዮጵያውያን መካከል ይገኝበታል። እሱም እንደ አምደ መረብ ጸሓፊው ዘላለም ክብረት ወደ አሜሪካን የተጓዘው ዐርብ እለት ነው።

በዓለም አቀፍ ሕግ ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪውን በመያዝ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ለ4 ዓመታት አካባቢ በመምህርነት ያገለገለው የዞን ዘጠኙ ዘላለም ክብረት እና ሌሎቹ 50 ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዩናይትድ ስቴትስ የስድስት ሣምንታት ቆይታ እንደሚያደርጉ ተገልጧል። ዘላለም ክብረት ወደ አሜሪካን ማቅናት መቻሉን ያወቀው የመርሐ-ግብሩ ቀነ ገደብ በሚጠናቀቅበት ቀን ነው።

ወጣቶቹ በአሜሪካን ቆይታቸው እንደ ሙያ ዘርፋቸው በጥናት እና ምርምር ተሳታፊ ይሆናሉ። የአመራር ሥልጠናም ይሰጣቸዋል። ከዚያ ባሻገር እርስ በእርስ የግንኙነት መረብ እንዲዘረጉ ሁኔታዎች ይመቻችላቸዋል ተብሏል።

የማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ መርሐ-ግብር ለተሳትፎ የሚመርጣቸው ወጣቶች ንቃተ-ኅሊናቸው የዳበረ በመሆኑ ወጣቶቹ ያገኙትን ልምድ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ ለሌሎች በማካፈል የላቀ አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ ይጠቅሳል። ወጣት ዘላለም በዞን ዘጠኝ የድረገጽ አምድ ላይ በተደጋጋሚ በሳል ጽሁፎችን ለንባብ አብቅቷል። ዘላለም ከሌሎች የዞን ዘጠኝ አባላት እና ጋዜጠኞች ጋርም ቀደም ሲል ለአንድ ዓመት ከአራት ወር ገደማ ለእስር ተዳርጎ ነበር።

ስድስት የድረ ገጽ ፀሐፍት እና ሦስት ጋዜጠኞች የሚገኙበት የዞን ዘጠኝ የድረ ገጽ ጸሐፍት ስብስብ ፓስስፖርታቸው ተይዞ እንደልብ የመንቀሳቀሳቸዉ ነገር ስጋት እንዳጠላበት መዘገባችን የሚታወስ ነው። በአጋጣሚ ፓስስፖርቱን ሲጠይቅ እንደተመለሰለት የገለጠው ወጣት ዘላለም ከአሜሪካን ቆይታው በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ አቅም የሌላቸውን ሰዎች የሚረዳ የሕግ ተቋም መመስረት ፍላጎት አለው።

«ይሄ መርሐ-ግብር ለእኔ በሕይወቴ ካገኘኋቸው ትልቁ ዕድል ነው» ያለው ወጣት ሞላልኝ ዕድሉን ያገኘው የራሱም ተደጋጋሚ ጥረት ታክሎበት እንደሆነ ተናግሯል። ሌሎች ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት ማድረግ አለባቸውም ብሏል።

ሙሉ ዘገባው ከታች በድምጽ ማጫወቻው ይገኛል።

ወጣት ሞላልኝ በላይ ለ«ማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ» መርሐ-ግብር ቦስተን፤ ዩናይትድ ስቴትስ
ወጣት ሞላልኝ በላይ ለ«ማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ» መርሐ-ግብር ቦስተን፤ ዩናይትድ ስቴትስምስል Molalign Belay
የዞን ዘጠኙ ድረ-ገጽ ጸሓፊ ዘላለም ክብረት፤ በቨርጂኒያ ዩናይትድ ስቴትስ
የዞን ዘጠኙ ድረ-ገጽ ጸሓፊ ዘላለም ክብረት፤ በቨርጂኒያ ዩናይትድ ስቴትስምስል Privat

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ