44 ሺሕ መፅሐፍት ለትምህርት ቤቶች ያሰባሰቡ ምሁር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 09.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

44 ሺሕ መፅሐፍት ለትምህርት ቤቶች ያሰባሰቡ ምሁር

ነዋሪነታቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በተለያየ መልኩ ሀገራቸውን ለመርዳት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ በአሜሪካ የኖርዝ ካሮላይና የግብርና እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶ/ር አበበ ከበደ ከእንዲህ አይነቶቹ ይመደባሉ፡፡ መምህሩ ወደ 44 ሺህ ማጣቀሻ መጽሐፍትን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች አከፋፍለዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:35

ምሁሩ ተንቀሳቃሽ ቤተ-ሙከራን ለማምጣት እየጣሩ ነው

የዛሬ ስምንት ዓመት ግድም ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ የሚገኘው የጭላሎ ተራራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጥቁር ሰማያዊ የደንብ ልብሳቸውን እንደለበሱ እንግዶቻቸውን ለመቀበል ተሰልፈዋል፡፡ ገሚሶቹ በሌጣ እጆቻቸው እያጨበጨቡ፣ ሌሎቹ ደብተሮቻቸውን እየመቱ በመሀላቸው ሰንጥቀው የሚያልፉትን እንግዶች በፈገግታ ይመለከታሉ፡፡ የባህል ልብስ ያጠለቁ ወጣት የኪነት ቡድን አባላት በባህላዊ ዜማ እና በእልልታ እንኳን ደህና መጣችሁ ይላሉ፡፡ 

እንዲህ አይነቱ የአቀባበል ስነ-ስርዓት የተከናወነው ከዓመታት በፊት በዚያ ትምህርት ቤት አስተምረው የነበሩ የአሜሪካ የሰላም ጓድ አባላት እና የቀድሞ ተማሪዎች ለጉብኝት እንደገና መምጣታቸውን በማስመልከት ነበር፡፡ ጉብኝታቸው የቆየ ትዝታን ማደስ ብቻ አልነበረም፡፡ ዓላማ ነበረው፡፡ የእዚህ ጉብኝት ጠንሳሽ እና አስተባባሪ የቀድሞው የትምህርት ቤቱ ተማሪ ዶ/ር አበበ ከበደ አንድ ዓመት ቀደም ብለው ወደዚያ ጎራ ባሉ ጊዜ ያስተዋሉት ችግር ነው የጉብኝቱን ዓላማ የወለደው፡፡ ያኔ የቪዲዮ ካሜራቸውን አንግበው በትምህርት ቤቱ እየተዘዋወሩ ያሉትን ችግሮች ጠይቀዋል፡፡ በወቅቱ ስናፍቅሽ አበበ የተባሉ የትምህርት ቤቱ የቤተ መጽሐፍት ሰራተኛ በትምህርት ቤቱ የመጽሐፍት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እንዳለ ነግረዋቸዋል፡፡ 

የቤተመጽሐፍቱን ሰራተኛ ገለጻ በዚያ ወቅት የትምህርት ቤቱ ተማሪ የነበረው በሱፍቃድ ጌታቸውም ይጋራዋል፡፡ በ1941 ዓ.ም የተመሰረተው የጭላሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በበሱፍቃድ ጊዜ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ሆኗል፡፡ የዘጠነኛ እና 10ኛ ክፍል ተማሪዎችን ብቻ በሚያስተናግደው በዚያ ትምህርት ቤት ያለውን የመጽሐፍ እና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች አቅርቦት እንዲህ መለስ ብሎ ያስታውሳል፡፡

“መሰናዶ ትምህርት ቤት ላይ ጠልቀን የተለያዩ መጽሐፍትን ስለማናጣቅስ በሰዓቱ ያን ያህል ብዙ መጽሀፍትን አንፈልግም ነበር፡፡ ግን ያሉትን የምንፈልጋቸው መጽሐፍት ግን በብዛት ደረጃ ጥቂት ነበሩ፡፡ ያው ትንሽ ተማሪዎች ከያዟቸው አይገኙም፡፡ መጠበቅ ይኖርብሃል የተወሰነ ጊዜ፡፡ በተረፈ ግን ጭላሎ ትምህርት ቤት እያለሁ በወቅቱ የነበረው ነገር ኮምፒውተር አለ ብሎ ለመናገርም አያስደፍርም” ይላል በሱፍቃድ፡፡

በትምህርት ቤቶች የመጽሐፍት እና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች እጥረት በተማሪዎች ውጤት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንደሚያሳድር በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ጭላሎ ተራራን ጨምሮ በአሰላ የሚገኙ ሶስት የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናትም ይህንኑ በማስረጃ አስደግፎ ዘርዝሯል፡፡ የጥናቱ አማካሪ የነበሩት እና በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የትምህርት እና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ መምህር ዶ/ር ይልፋሸዋ ስዩም ስለ ጉዳዩ ተከታዩን ብለዋል፡፡

“መጽሐፍት እንግዲህ በአሁኑ ሰዓት ታትመው የተጠረዙት ብቻ አይደሉም፡፡ የታተሙት በጣም ውድ ናቸው፡፡ ሶፍት ኮፒዎችን ለማግኘት የኢንተርኔት እና የኮምፒውተር አገልግሎት እንደዚሁ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይህን ዕድል የሚያገኙት ወይ የሉም ወይ ቁጥራቸው በጣም ውስን ነው፡፡ በጣም አስፈላጊ እና መሟላት ያለባቸው ናቸው፡፡ መንግስትም ይህን ይቀበላል” ይላሉ መምህሩ፡፡

ለጭላሎ ተራራ ትምህርት ቤት መጽሐፍትን ለማምጣት ቃል የገቡት ዶ/ር አበበ መጽሐፍት እንዴት ውድ እንደሆኑ አልሳቱትም፡፡ የግዢውን ወጪ ለመቀነስ ግን መላ ዘይዱ፡፡ ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ትምህርት ቤቱን ከጎበኙት የቀድሞ የሰላም ጓድ አባላትን እና የአሰላ ወዳጆችን በማስተባበር የቻሉትን ያህል ማሰባሰብ ያዙ፡፡ የፊዚክስ አስተማሪው ዶ/ር አበበ ቅድሚያውን ለሳይንስ ዘርፎች ነበር የሰጡት፡፡ በሌሎች ዘርፎች የተጻፉ እና በርካታ መጽሐፍትን ለማግኘት ደግሞ በዚያው በአሜሪካ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ፤ በመጽሐፍት ዙሪያ የሚሰራ ድርጅትን በር አንኳኩ፡፡

“የመጽሐፍ ችግር የለም፡፡ መጽሐፍ ማሰባሰብም አያስፈልግም፡፡ ግን እኛ ብዙ ሰብስበናል፡፡ የህክምና፣ ህግ፣ ለልዩ ፍላጎት የሚሆኑ ሰብስበናል፡፡ ለስፖርት የሚያገለግል ጭምር ሰብስበናል፡፡ “Books For Africa” የሚባል ድርጅት አለ፡፡ እዚህ ከተመለስን በኋላ ከእርሱ ድርጅት ጋር ተባበርን እና የመጀመሪያው ጭነት [በጎርጎሮሳዊው] 2010 ሄደ፡፡ በነገራችን ላይ “Books For Africa” የእኛ ድርጅት አይደለም፡፡ እነሱ የሚያደርጉት ዋናው ነገር ምንድነው? ፕሮጀክት ትሰጣቸዋለህ፡፡ ይሄን ይሄን እሰራለሁ ብለህ፣ ተጠቃሚው ለይተህ ትሰጣቸዋለህ፡፡ “Books For Africa” መጽሐፉን በነጻ ነው የሚሰጥህ፡፡ ግን መጽሐፍ ሲላክ በኮንቴየነር ሆኖ እስከ 20 ሺህ መጽሐፍት ይላካል፡፡ ለመላኪያ የሚሆነው ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ እስከ 20 ሺህ ዶላር ያወጣል” ይላሉ ዶ/ር አበበ፡፡

በነጻ የተገኘን መጽሐፍ ለመላክ እንዲህ ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልም ዶ/ር አበበ እና ጓደኞቻቸው ለሻይ እና ቡና የሚያወጡትን እየለገሱ፣ ከሌሎች ሰዎች ገንዘብ እያሰባሰቡ ከአንድም አራት ጊዜ መጽሐፍት ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል፡፡ በአጠቃላይ የላኳቸው መጽሐፍት 44 ሺህ ገደማ መድረሳቸውን ዶ/ር አበበ ይናገራሉ፡፡ ለቀድሞ ትምህርት ቤታቸው የተጀመረው የመጽሐፍት ማሰባሰብ በአሰላ እና አርሲ ለሚገኙ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ተርፏል፡፡ ወደ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት ያስተምሩበት የነበረው የጎንደር ዩኒቨርስቲም የትሩፋቱ ተቋዳሽ ሆኗል፡፡ የጭላሎ ተራራ ትምህርት ቤትን ማዕከል በማድረግ ስላከፋፈሏቸው መጽሐፍት ዝርዝር አላቸው፡፡ 

“ያንን ትምህርት ቤት አማካይ በማድረግ በአሰላ አካባቢ እና አርሲ ውስጥ ያሉ ወደ 35 ትምህርት ቤቶች ረድተናል፡፡ ጠቀሜታው ሲታይ ቢያንስ ወደ መቶ እና 150 ሺህ ተማሪዎችን ጠቅሟል፡፡ 44 ሺህ መጽሐፍት ለአሰላ አካባቢ ሄደ በምትልበት ጊዜ እዚያ ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑ ዩኒቨርስቲዎች አሉ፡፡ የአዳማ ዩኒቨርስቲ የህክምና ትምህርት ክፍሉ አሰላ ነው ያለው፡፡ አሁን አርሲ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ይሆናል፡፡ እርሱ በብዛት የህክምና መጽሐፍት ወስዷል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በብዛት የህክምና መጽሐፍት ወስዷል፡፡ እንደገና ብዙ የፊዚክስ መጽሐፍት ወስዷል፡፡ ሌላ ደግሞ ብዙ ሳጥን ለአይነ ስውራን የሚሆን ብሬል ለሳይንስ ለሚያሰተምሩ ተብሎ ተሰጥቷል፡፡ እዚያ የሰጣናቸው ብዙዎቹ የሳይንስ መጽሐፍት ናቸው፡፡ አሰላ አግኝቷል፡፡ ጎንደርም አግኝቷል” ሲሉ ያሰባሰቧቸውን መጽሐፍት መዳረሻ ይዘረዝራሉ፡፡ 

ዶ/ር አበበ መጽሐፍት ለየትምህርት ቤቶቹ እና ዩኒቨርስቲዎቹ በማምጣት ብቻ አልተወሰኑም፡፡ ይልቁንም ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርት ጎን ሁሉገብ እውቀት እንዲያገኙ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ 

“[ከጎርጎሮሳዊው] 2009 እስከ 2014 ድረስ አንዳንድ አውደጥናቶች፣ ወጣቶችን የማብቂያ (youth empowerment) ዝግጅቶች፣ ትምህርታዊ ጉባኤዎችን አካሄደናል፡፡ እንደውም ከአዳማ ዩኒቨርስቲ የህዋ ሳይንስ ክበብ ጋር ተባብረን ለመለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሳይንሳዊ ማስተዋወቂያ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ጎንደር ሄደን የጎንደር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት መስጫ አቋቁመናል፡፡ እንዴት አድርገን አቋቋምነው? እኔ ወደ ኢትዮጵያ ስሄድ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ድሮ እኔ ሰራተኛ ስለነበርኩ ልመጣ ነው ስላቸው እሺ ና እና ትምህርታዊ ጉባኤ ስጥልን ነው የሚሉኝ፡፡ አንድ ብጣሽ ጉባኤ ምን ያደርግላቸዋል፤ ለምን 10 ይዤ አልሄድም እላለሁ፡፡ አስር ልጆች ግማሹ ሂሳብ፣ ግማሹ ኬሜስትሪ፣ ግማሹ የማህበራዊ ጥናት በማንኛውም ዘርፍ አስር ዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ይዤ ልሄድ እችላለሁ ባይ ነኝ እኔ፡፡”

“እንዴት ታደርጋለህ? በለኝ፡፡ ሁልጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስሄድ ባዶ እጄን መሄድ አልፈልግም፡፡ ምንም ነገር ከሌለኝ አልሄድም፡፡ ይቺን ምክንያት አድርጌ ምን አደርጋለሁ? ጓደኞቼን በሙሉ ለዕረፍት ሲሄዱ ‘እባካችሁን ወደ ጎንደር ልሄድ ነውና እንሂድ አብረን’ እላችኋለሁ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ተቋም አስር ሰዎች ከአሜሪካን ሀገር ወይ ከቦታው አንስቶ ጎንደር ድረስ ወስዶ፣ ቀልቦ፣ ደህንነታቸውን ጠብቆ፣ ሌላም ነገር አድርጎ አስር ሰው ለማስተናገድ አንድ ሙሉ ቤተ መጽሐፍት የሚሰራ ወጪ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ እኛ የምናደርገው በራሳችን ወጪ አዲስ አበባ ድረስ እንሄዳለን፡፡ ከአዲስ አበባ በኋላ የሚያስተናግደን ዩኒቨርስቲ ኑ ይለን እና የሀገር ውስጥ ድጋፍ ይሰጠናል፡፡ እዚያ ሄደን የሚሰራውን ስራ ሰርተን ወደ መጣንበት እንመለሳለን” ይላሉ ዶ/ር አበበ፡፡

ከጓደኞቻቸው ጋር እኒህን ተግባራት በየዓመቱ እንደሚያከናውኑ የሚናገሩት ዶ/ር አበበ በየዩኒቨርስቲዎቹ እና ትምህርት ቤቶቹ ሲዘዋወሩ ያስተዋሉት የቤተ-ሙከራ እጥረት ለሌላ ውጥን እንዳነሳሳቸው ይገልጻሉ፡፡ አዲሱ ውጥናቸው ተንቀሳቃሽ ቤተ-ሙከራን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ነው፡፡ አንድ ተንቀሳቃሽ ቤተ ሙከራ ሹፌር፣ መምህር፣ ላብራቶሪ ቴክኒሺያን እና የጥገና ባለሙያ ብቻ እንደሚያስፈልገው በማንሳትም አዋጪነቱን ያሰምሩበታል፡፡ እርሳቸው የሚያስተምሩትን ፊዚክስን በምሳሌነት በመጥቀስ የቤተ-ሙከራን አስፈላጊነት ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር አስተሳስረው ያስረዳሉ፡፡

“አሁን ለምሳሌ ፊዚክስ 101 ሁለት ክፍል አለው፡፡ አንዱ ንድፈ ሀሳባዊው ክፍል ነው፡፡ ዋናውን፣ ዓላማውን ይማራሉ፡፡ ነገር ግን ቤተ ሙከራ ለመስራት ከፈለጉ ምን ይደረጋል መሰለህ? ለምሳሌ ሰመራ ዩኒቨርስቲ [የቤተ-ሙከራ] ዕቃዎች የሉትም ስለዚህ ልጆቹን በአውቶብስ ያደርጉ እና ወይ ጅጅጋ ዩኒቨርስቲ ወይም ቀረብ ያለ ቤተሙከራ ያለበት ይወስዷችዋል፡፡ ከአምቦ ልጆቹን ነቀምቴ ዩኒቨርስቲ ወስደው ያሰሯቸዋል፡፡ ወልዲያም እንደዚሁ፡፡ ይሄ ሁለት ችግር አለው፡፡ አንደኛ ልጆቹ [ትምህርታቸው ላይ] ትኩረት አያደርጉም፡፡ እንደ አገር ጎብኚ በየቦታው ነው የሚዞሩት፡፡ የተረጋጋ አይደለም፡፡ ቤተ-ሙከራ ሊሰሩ  15 ቀን [ወስደው]፣ በአውቶብስ ተጉዘው ነው፡፡ በዚያ ላይ አደጋም ይኖራል፡፡ ለልጆቹም አስተማማኝ አይደለም፡፡

“መደረግ ያለበት ምንድነው? አንድ ታሳቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ዕቃ ለመጫን በዚታዎ የምትስበው አለ አይደለም? ያችን ተሳቢ ውስጧን የሚያስፈልጉቷን የቤተ-ሙከራ ዕቃዎች በማድረግ የራሷ ጄኔሬተር ያላት ማድረግ ይቻላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደውም በጸሀይ ሀይል፣ በባዩ ፊዩል ማንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ እነኛን የቤተሙከራ ዕቃዎች ካደረግኽ በኋላ ‘ሰመራ ዩኒቨርስቲ ቤተ ሙከራ እሰራለሁ፣ ቤተሙከራ ይምጣልኝ’ ካለ እዚያ ታቆምላችዋለህ፡፡ የቤተ-ሙከራ ስራቸውን ሲጨርሱ ዚታዎ ይመጣና ጎትቶ ጅጅጋ ዩኒቨርስቲ ያስፈልገው እንደሆነ እዚያ ያቆማል፡፡ እንደዚያ ውጤታማ ይሆናል ማለት ነው” ሲሉ ከእቅዳቸው ጀርባ ያለውን ምክንያት ያብራራሉ፡፡

ዶ/ር አበበ ይህንን የተንቀሳቃሽ ቤተ-ሙከራ ፕሮጀክት ማጠናቀቃቸውን እና ደጋፊ አጋር እየፈለጉ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ከመጽሐፍ እርዳታው ጎን በትንሹ የጀመሩትን የኮምፒውተር ልገሳንም ወደ መጽሐፍ ማንበቢያ ታብሌቶች የማሳደግ ህልም አላቸው፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic