1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

30 አመት የድፍነዉ የኢራን እስላማዊ አብዮት መንስኤ

ሰኞ፣ ጥር 25 2001

ከሁለት ሺሕ አምስት መቶ አመታት በላይ የፀናዉ የጥንቷ ፋርስ የኋላዋ የኢራን ንጉሳዊ አገዛዝ ተገረሰሰ

https://p.dw.com/p/GllQ
ሆሚኒ

ደንገዝገዝ እንዳለች የዋለችዉ የቁም ጀምበር ሳትደምቅ-ከመጥለቋ፣ የሰዉዬዉ ከተንበሪ በሐይል ተንኳኳ።እንደተከፈተ-አንኳኪዎቹ እየተጣደፉ ገብተዉ ሰዌዉን ይዘዉ ወጡ።ፀጥታ አስከባሪዎች ናቸዉ።ጊዜ አላጠፉም።ወደ ቴሕራኑ ማሕረባድ አዉሮፕላን ማረፊያ ከነፉ።ወደ ቱርክ ከሚበረዉ አዉሮፕላን ወረዎሯቸዉ።ሕዳር-4 1964 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።ሰዉዬዉ፣ እንደ ሌባ-በጠፍ ጨረቃ ተጋዙ።በአስራ-አምስተኛ አመታቸዉ ቴሕራን ሲገቡ-ግን ሚሊዮነ-ሚሊዮናት የጀግና አቀባበል አደረጉላቸዉ።።
ድምፅ (መፈክር)
አያቶላሕ ሩሑላሕ ሙሳቪ ኾሚኒ።ትናንት ልክ ሰላሳ-አመቱ።የሆሚኒ ትግልና የኢራን እስላማዊ አብዮት መንስኤ፥ የዛሬ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

ሲ ኤን ኤን በሚል የእንግሊዝኛ ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ «አለምን መግዛት የሚሹ» የምትላቸዉ የኢራን ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲንኒጃድ ኢራን ጠንካራነች አሉ-በቀደም።አንበሳም።
ድምፅ
«ኢራን ጠንካራ ሐገር መሆንዋን መዘንጋት የለባችሁም።ልክ ሰዎች እንደሚሉት ኢራን ካንድ ጥግ እንዳደፈጠ አንበሳ ናት።እኛ የምንመክራችሁ በአንበሳዉ ጭራ እንዳትጫዎቱ ነዉ።»

በርግጥም የዛሬዋ ኢራን በፋርስ ባሕረ-ሠላጤ ፦ በድፍን መካካለኛዉ ምሥራቅም ያላት ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።በ1980ዎቹ በሳዳሟ ኢራቅ ግንባር ቀደም ተዋጊነት፣በዩናይትድ ስቴትስና በተባባሪዎችዋ አስተባባሪነት ካንዲት ሶሪያ በስተቀር አብዛኛዉ አረብ ባንድ አብሮ ሲቀጠቅጣት ያለቀላት መስሎ ነበር።

ስምንት አመት ባላባራዉ ጦርነት ከሁለቱም ወገን በሚሊዮን የሚቆጠር ሰዉ አልቋል።ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል።ኢራንም፥ ከሁሉም በላይ ጦርነቱ ያለመለት የኢራን እስላማዊ አብዮትም አልጠፉም።ረጅሙ ጦርነት ካበቃ በሕዋላ ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ሁለቴ የዘመቱባት በኢራቅ ላይ እንጂ በኢራን ላይ አልነበረም።

የሳዳም ሁሴን ሕይወት፥በአዝ ፓርቲያቸዉ፥ ሐብታም አሐገራቸዉ ጠፉ-ወደሙ እንጂ የኢራን እስላማዊ አብዮት በርግጥ አልተቀበለሰም።ከሒዝቡላሕ እስከ ሐማስ ያሉ አክራሪ ድርጅቶች በመካከለኛዉ ምሥራቅ ማሕበረ-ፖለቲካ- ምጣኔ ሐብታዊ ሒደት ላይ ተፅዕኖ ማሳራፍ ከቻሉ የችሎታቸዉ መሠረት ከቴሕራን የሚደረግላቸዉ ድጋፍ መሆኑ አያነጋግርም።

ይሕ እዉነት ፕሬዝዳት አሕመዲን ኒጃድ መንግሥት፦ ሐገራቸዉን ባንበሳ ለመመሰል እብሪት አድርሷቸዉ ይሆናል።ወይም የሲኤን ኤ ዋ ዘጋቢ-እንዳለችዉ አለምን ለመግዛት አንጠራርቷቸዉ ይሆናል።የኢራን እዉነታ ግን ሁለቱንም የሚፈቅድ አለመሆኑ እንጂ-ዚቁ።የኢራን አጠቃላይ አመታዊ ምርት (ጂዲፒ) አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ በአመት ለአንድ መስክ፥ ለጦር ሐይል ብቻ የምጣወታዉን ሁለት መቶኛ አያክልም።

አሕመዲንነጃድ ሐገራቸዉ በላሸቁት፥ በሙስና በዘቀጡት፥ በሕዝባቸዉ በተጠሉት በባግዳድ ገዢዎችና በተባባሪዎቻቸዉ አረቦች ላይ የተቀዳጀችዉን ድል፥ እርስ በርስ ከሚናቆሩት ጎረቤቶቿ አንፃር ያላትን ጥንካሬ፥ በነሐማስ-ሒቦላሕ ላይ ያላትን የበላይነት የአለም አንበሳ የመመሰሏ እብጠት ማድረጋቸዉ ስሕተት የመሆኑን ያክል-አለምን መግዛት የሚሹ መባላቸዉም በርግጥ ጅልነት ነዉ።
ድምፅ (መሸጋገሪያ)

ጄኔራል ሬዛ ሳቫድ ኩሒ ወይም ካሕን የሶቬት አብዮተኞች ተፅዕኖ፥ የሐገር ዉስጥ ተቃዉሚዎች ግፊት፥የምዕራቡን ሥልጣኔ ፈላጊዎች ጥያቄ ግራ ቀኝ የወጠረዉን የቃጃር ሥርወ-መንግሥትን የመጨረሻ (ንጉሥ) አሕመድ ሻሕ ቁጃርን በ1923 ከሥልጣን አስወግደዉ ዘዉድ ለመድፋት ብዙም አልደከመ ነበር።

ሬዛ-ሻሕ ፓሕሌቭ የሚለዉን የንግሥና ማዕረግ ካጠለቁ በሕዋላ አዉራ-መንገዶችን በማስገንባት፥ የመጀመሪያዉን የቴሕራን ዩኒቨርስቲ በመክፈት፥ ዘመናይ ትምሕርትን በማስፋፋት፥ ከሁሉም በላይ ለሐይማኖት ያልወገነ-ሥርዓት በመትከላቸዉ በወግ አጥባቂዎቹ የሚተቹ-የሚወቀሱትን ያህል ከዘመናዊዉ በተለይም ከአዉሮጳና ከአዉሮጳ ቀመሱ የምዕራቡን ባሕል፥ ወግ ፖለቲካዊ ሥርዓትም የተቀበሉ እየተባሉ ሲንቆለጳጳሱ ነበር።

ሬዛ-ሻሕ የሚሰነዘርባቸዉ ትችት ወቀሳ-ዙፋናቸዉ እንዳላሳጣቸዉ ሁሉ የሚወርድላቸዉ ሙገሳ አድናቆትም የሥልጣናቸዉ ዋስትና አለመሆኑ ነዉ-ዚቁ።የምዕራቡን ሥርዓት የሚከተሉት ንጉስ ሁለተኛዉ የአለም ጦርነት እንደተጀመረ ከምዕራቦች መሐል-ጀርመንን መርጠዉ ወደ በርሊን ማድላታቸዉ የሞስኮ ኮሚንስቶችን ከለንደን ካፒታሊስቶች ባንድ አሳብሮ የዘመነ-ሥልጣናቸዉ ፍፃሜ ሆነ።

ብሪታንያና ሩሲያ ሬዛ-ሻሕን ከሥልጣን አስወግደዉ ወንድ ልጃቸዉን መሐመድ ሬዛ ፓሕሌቪን አገሱ።1941።አባት ተወግደዉ ልጅ የነገሱበት እርምጃ ለሁለት ሺሕ አምስት መቶ አመታት በፀናዊ በፋርስ ፖለቲካዊ ሥርዓት ዉስጥ የመጀመሪያዉ የዉጪ ጣልቃገብነት የታየበት ሆነ።በዉጪ ሐይላት ድጋፍ ሥልጣን የያዙት ወጣቱ ንጉስ ከሕዝባቸዉ ፍላጎት ይልቅ ለዉጪዉ በተለይም ለብሪታንያና ለዩናትድ ስቴትስ ደጋፊዎቻቸዉ ፍላጎት ማድላታቸዉ ጋዜጠኛ ጋሲም ቶላኒይ እንደሚለዉ ኋላ አያቶላሕ ኾሚኒን የመሳሰሉ ተቃዋሚዎቻቸዉን ለማፍራት ጥሩ መደላድል ሆኗል።

ድምፅ

«አያቶላሕ ሆሚኒ ከመጀመሪያዉ ጀምሮ የእስልምና እሴቶችን ገቢር የሚያደርግ ሥርዓት መመስረት ነበር የሚሹት።ለዚሕ አላማቸዉ ስኬት መሠረት ያደረጉት ደግሞ እሳቸዉ ራሳቸዉ ገና 1960ዎቹ የነደፉትን ወላያት «ኢ-ፈቂሕ» (የሙስሊም ሊቃዉንት አመራር) የተሰኘዉን መርሕን ነዉ።»

የሐገር ዉስጡ ቅሬታ-ወደ ቅራኔ አድጎ በ1951 በተደረገዉ ምርጫ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የያዙት ዶክተር መሐመድ ሞሳደግሕ የሚመሩት መንግሥት ፍፁማዊዉን ንጉስ ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ዙፋንነት ይገፋዉ ገባ።ብሪታንያ የምትቆጣጠረዉን የኢራን የነዳጅ ዘይት ኩባንያ የወረሰዉን የጠቅላይ ሚንስትር ሞሳደግሕ መንግሥትን ለማስወገድ የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ የስለላ ድርጅቶች የዶለቱት ሴራ ሲከሽፍ-ሻሑ ቅሌን ጨርቄን ሳይሉ ዙፋናቸዉን ጥለዉ ኮበለሉ።

ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ዘመቻ-አጃክስ ባሉት ሴራ ጠቅላይ ሚንስትር ሞስዳግሕን ከሥልጣን አስወግደዉ ንጉሱን ወደዙፋናቸዉ ለመመለስ ጊዜ አልወሰደባቸዉም።በዉጪ ሐይላት ዘዉድ የጫኑት፥ በዉጪ ሐይላት ሥልጣናቸዉን መልሰዉ የጨበጡት ሻሕ፥ በሕዝብ በተለይም በተቃዋሚዎቻቸዉ ላይ የሚወስዱት እርምጃ ወትሮም ያቄሙትን የእስልምና ሐይማኖት ምሕራንና ቁጣ አጋገመዉ።

ንጉሱ በ1964 &ነጩ ተሐድሶ» ያሉት የፖለቲካ መርሕ ሲያስተዋዉቁ መርሁን በመቃወም አደባባይ የወጡ ሰዎችን ማስገደል፥ ሆሚኒን የመሳሰሉ እዉቅ የሐይማኖት ሊቃዉንታትን ማሳሰር-ኋላ ማስጋዛቸዉ የዘመነ-ሥልጣናቸዉ ፍፃሜ ምልክት፥የኢራን እስላማዊ አብዮት ጥንስስ ሆነ።በአስራ-አምስተኛ አመቱ የማይቀረዉ ሆነ።
ድምፅ (የሕዝብ መፈክር)
ካንዴም ሁለቴ ወሕኒ የተወረወሩት፥ የተጋዙት፥ ከቱርክ ኢራቅ፥ ከኢራቅ ፈረንሳይ ሲንከራተቱ አስራ-አምስት አመት ያስቆጠሩት አያቱላሕ ሆሚኒ በድል አድራጊነት ቴሕራን ሲገቡ፥ እስከዚያ ዘመን ድረስ የተገበሩት፥ የማይደፈሩት፥ የሚፈሩት የለንደን ዋሽንግተኑ ታማኝ ንጉሱ ኮበለሉ።በከሐዲነትም ተወነጀሉ።
ድምፅ

«ከሐዲዉ መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ መኮብለሉን ለናንተ መናገር አለብኝ።ሁሉም ከበዘበዘ በሕዋላ ኮብልሏል።ሐገራችንን አዉድሟቷል።መካነ-መቃብራትን በአስከሬን ሞልቷቸዋል።ምጣኔ ሐብታችንን አድቅቆታል።የራሱን ብልፅግና ለማማመቻቸት በሐገር እድገት ሥም ሐገራችንን ከትቢያ ቀይጧታል።ባሕላችንን ጨቁኗል።ሰዎችን አጥፍቷል።የሰራተኛ ሐይልና እምቅ ሐብታችንን አዉድሟቸዋል።»


ከሁለት ሺሕ አምስት መቶ አመታት በላይ የፀናዉ የጥንቷ ፋርስ የኋላዋ የኢራን ንጉሳዊ አገዛዝ ተገረሰሰ።በአለም ላይ እስልምናን ከአብዮት ጋር የቀየጠ የመጀመሪያዉ ፖለቲካዊ ሥርዓት ተተከለ።የኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክ።ዘንድሮ የካቲት ሰላሳ አመቷን ደፈነች።የሳላሳ አመቱ አጉዞ ብዙ ያስብላል።ለዛሬዉ ግን ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Negash Mohammed

ZPR,Wikipedia