የጋህነን አባላት እጃቸውን ሰጡ
ሰኞ፣ ጥር 14 2010የጋምቤላ ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ጋህነን)ቁጥር ሁለት በመባል የሚጠራው ቡድን አባላት ሰሞኑን ለኢትዮጵያ መንግሥት እጃቸውን ሰጥተው ወደ ሀገራቸዉ መመለሳቸው ተሰምቷል። ይህ የሆነውም ከቡድኑ ጋር በተደረሰ ስምምነት ነው። እጃቸውን ከሰጡት 148 የጋህነን ቁጥር ሁለት አመራር እና አባላት መካከል ከ 18 በላዩ ሴቶች እንደሆኑ የጋምቤላ ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ ቱት ዛሬ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። እንቅስቃሴውን በተመለከተ ሲያስረዱም « እነዚህ ሰዎች ኤርትራ ውስጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው። ወደ ደቡብ ሱዳንም የገቡበት ሁኔታ ነበር። » ብለዋል።ሺንዋ ዜና ምንጭ አማፂያን እንደሆኑ የጠቆማቸው እነዚህ ወገኖች በትክክል እነማን ናቸው? አላማቸውስ ምን ነበር? እንደ አቶ ጋትሉዋክ ገለፃ « ጋህነን ቁጥር ሁለት በተለይ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው። ጋህነን ቁጥር ሁለት የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ነው።»
በተለያየ አካባቢ የነበሩትን የዚሁ የጋህነን ቁጥር ሁለት እንቅስቃሴ አባላትን ለማግባባት ጊዜ እንደወሰደ እና ከሦስት ወራት በኋላ ሰላም ፈጣሪ ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ጋትሉዋክ ተናግረዋል። « መንግሥታችን በሰላማዊ መንገድ ከእነሱ ጋር ከስምምነት እንዲደርሱ አድርጓል። አላማው የሀገራችንን እና የክልላችንን ሰላም ለመጠበቅ ነው። እጃቸውን የሰጡት አባላትም ከጥር 11 ጀምሮ የተሀድሶ ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነ እና ከስልጠናው በኋላ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንደሚቀላቀሉ ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ አክለው ገልጸዋል።
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሰ