1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

14 የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት አባላት አሜሪካንን ወቀሱ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 30 2010

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት አባላት ዶናልድ ትራምፕ ያሳለፉትን ውሳኔ ወቀሱ። ትናንት በኒው ዮርክ በተካሔደው የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ 14ቱ የምክር ቤቱ አባላት ተራ በተራ የዶናልድ ትራምፕን ውሳኔ ተችተዋል።

https://p.dw.com/p/2p5UH
Israel Proteste nach Jerusalem Entscheidung der USA
ምስል Getty Images/AFP/T. Coex

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ አሜሪካ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ስትል እውቅና መስጠቷ የበርካቶችን ተስፋ ያደባየ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ከፍ ያለ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ስሜታዊ ትርጉም ባላት እየሩሳሌም ላይ በአንድ ወገን ብቻ የሚወሰድ ርምጃ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ያሉት አምባሳደር ተቀዳ ሰላም ይመጣል የሚለውንም ተስፋ ያመነምናል ሲሉ ተናግረዋል።

የእስራኤል እና ፍልስጤምን ቀውስ ለመፍታት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል፣ ትክክለኛ፣ ፍትኃዊ እና ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚችለው በሰላም ጎን ለጎን መኖር የሚችሉ ሁለት አገሮች መመስረት ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል። "በማያስገርም ሁኔታ ገና ካሁኑ የመካከለኛው ምሥራቅን ያምስ የያዘው ይኸ እርምጃ  ሰላም ያመጣል፣ የሰላም እና የተረጋጋ ጸጥታ መሰረት እንዲሁም  ለሁለት አገሮች የመፍትሔ ሐሳብ መሰረት ይጥላል ብለን አናምንም።  በእርግጥ የቀጣናውን ብቻ ሳይሆን የመላውን ዓለም ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል  የጸጥታ መደፍረስ የሚታይበት እና ውስብስብ ፈተናዎች የተጋረጡበት የመካከለኛው ምሥራቅ ይኸ አያስፈልገውም።" አምባሳደር ተቀዳ ጥቂት ተስፋ የነበራቸው ጭምር አሜሪካ ከወሰደችው ውሳኔ በኋላ ተስፋ መቁረጣቸውን ጠቅሰው ርምጃውን ወቅሰዋል።

የአምባሳደሩን ሥጋት የብሪታኒያ፣ የፈረንሳይ፣ የስዊድን፣ የጀርመን እና የጣልያን አምባሳደሮችም ተጋርተውታል። አምባሳደሮቹ ከስብሰባው በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫ የአሜሪካ ውሳኔ ከጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ውሳኔዎች ጋር ያልተስማማ በቀጣናው ሰላም ለማስፈን ለሚደረገው ጥረትም ጠቃሚ ያልሆነ ብለውታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሔሊ በፕሬዝዳንታቸው ውሳኔ የቀረበውን ወቀሳ አጣጥለዋል። "ዩናይትድ ስቴትስ እስራኤላውያንን እና ፍልስጤማውያንን እኩል በማስተናገዱ ረገድ ፍትኃዊነት በሚጎድላቸው አገራት የሚያቀርቡት ዲስኩር አትቀበልም።" አሜሪካ በምክር ቤቱ ባላት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ምክንያት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ይፋ የወቀሳ መግለጫ የሚያወጣ ግን አይመስልም። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ እስራኤል በጋዛ ሠርጥ በሚገኙ ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች ላይ ዛሬ ማለዳ በፈጸመችው የአየር ድብደባ ሁለት የሐማስ ታጣቂ አባላት ተገደሉ። የእስራኤል ጦር ጥቃቱ በታጣቂ ቡድኑ ለተተኮሱ ሮኬቶች ምላሽ መሆኑን ገልጧል። ጦሩ እንዳለው አራት የሐማስ ወታደራዊ ሰፈሮች የጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል። 

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ