ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በጊኒ | አፍሪቃ | DW | 23.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በጊኒ

የቀድሞው የጊኒ ቢሳው ፕሬዚደንት ማላም ባካይ ሳና ከጥቂት ወራት በፊት ከረጅም ሕክምና በኋላ ከሞቱ ወዲህ የምክር ቤት ፕሬዚደንት ራይሙንድ ፔሬራ ሀገሪቱን እስካሁን በተጠባባቂነት በመምራት ላይ ይገኛሉ። በዛሬው ዕለት ግን የጊኒ መራጭ ሕዝብ የማላም ባካይ ሳናን ተተኪ ይመረጣል።

የቀድሞው የጊኒ ቢሳው ፕሬዚደንት ማላም ባካይ ሳና ከጥቂት ወራት በፊት ከረጅም ሕክምና በኋላ ከሞቱ ወዲህ የምክር ቤት ፕሬዚደንት ራይሙንድ ፔሬራ ሀገሪቱን እስካሁን በተጠባባቂነት በመምራት ላይ ይገኛሉ። በዛሬው ዕለት ግን የጊኒ መራጭ ሕዝብ የማላም ባካይ ሳናን ተተኪ ይመረጣል። ለዚሁ ከፍተኛ የሀገሪቱ ሥልጣን ዘጠኝ ዕጩዎች በተፎካካሪነት ይወዳደራሉ። በምርጫው ጥሩ የማሸነፍ ዕድል አላቸው የሚባሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ካርሎስ ጎሜስ ጁንየር ናቸው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጊኒ ቢሳውና ለኬፕ ቬርዴ ደሴቶች ነፃነት የታገለው የቀድሞውን የአንድነት ፓርቲ በመወከል ነው የሚወዳደሩት። በሴኔጋል በስተደቡብ የምትገኘው ጊኒ ቢሳው ካለፉት ብዙ ዓመታት ወዲህ በምዕራብ አፍሪቃ ካሉት ሀገሮች መካከል መረጋጋት የጎደላት ሀገር በመሆን ትታወቃለች። በዚችው ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ውስጥ በፖለቲካ ልዩነት የሚነሱ ችግሮች በውይይት ወይም በመደራደር ሳይሆን በጦሩ መሣሪያ ኃይል ነው የሚፈቱት። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ፡ የተመድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፡ ይህችው ሀገር ለዓለም አቀፉ ህገ ወጥ የአደንዛዥ ዕፅ ግድ መናኸሪያ የሆነችበት ድርጊት የሀገሪቱን ችግር ይበልጡን አባብሶት ተገኝቶዋል።

በብዙ መቶ የሚገመቱ ሰዎች በመዲናይቱ ቢሳው በሚገኘው በቀድሞው ገዢው ለጊኒ ቢሳውና ለኬፕ ቬርዴ ደሴቶች ነፃነት የታገለው የቀድሞውን የአንድነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በር በመሰብሰብ ሲዘፍኑና ሲደንሱ ይታያሉ። ለነገሩ ሕዝቡን እንዲህ የሚያስፈነጥዝ ነገር በሀገሪቱ አልተፈጠረም። ግን በሀገሩ የተሻለ ጊዜ ይመጣል የሚለው የጊኒ ቢሳው ሕዝብ ተስፋ ጠንካራ በመሆኑ ብቻ ነው።

እንዲያውም፡ በተመ የዕድገት መለኪያ መዘርዝር መሠረት፡ ጊኒ ቢሳው እጅግ ኃላ ቀር ከሚባሉት የመጨረሻዎቹ አሥራ አንድ የዓለም ሀገሮች መደዳ ነው የምትቆጠረው።

ጠቅላይ ሚንስትር ካርሎስ ጎሜስ ጁንየር ወክለውት የሚወዳደሩለት ፓርቲ በሀገሪቱ በሚገባ የተደራጀ ብቸኛው ፓርቲ በመሆኑ ድል እንደሚቀዳጁ ይሰማቸዋል።
« ሕዝቡ በኔ ላይ እምነት አለው። እርግጥ፡ በምርጫው እንደማሸንፍ አምናለሁ። በሕዝባችንና በፓርቲያችን አባላት ላይ እተማመናለሁ። »
በጊኒ ቢሳው እአአ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት የመድብለ ፓርቲው ሥርዓት ቢተዋወቅም፡ የጦር ኃይሉ በየጊዜው ባካሄደው መፈንቅለ መንግሥት የተነሳ፡ አንድም የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመኑን እፍፃሜ ላይ ማድረስ አልቻለም። የጊኒ ቢሳው የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ ታግሜ ና ዋዬ በአንድ የቦምብ ጥቃት ከተገደሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላም የቀድሞው ፕሬዚደንት ኒኖ ቪየራ በ 2009 ዓም በጦር ኃይል አባላት መገደላቸው ይታወሳል። የፕሬዙደንቱ ገዳዮች እስከዛሬ አልተያዙም።


እና ይህ ሁሉ ግድያና ጥቃት ሲታሰብ የጊኒ ቢሳው ሕዝብ በሀገሩ ሰላምና መረጋጋት እንዲወርድ ያለው ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑ አያስገርም። በመሆኑም ለውድድር የቀረቡት ዕጩዎች ይህንኑ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላትና የወደፊቱን ሁኔታም ለማረጋጋት ቃል እየገቡ ነው።

የምክር ቤት አፈ ጉባዔ የሆኑት ሴሪፎ ናማጆ የገዢው ፓርቲ አባል ቢሆኑም ለምርጫው በነፃ ዕጩነት ለመወዳደር ተመዝግበዋል። ይህንንም ያደረጉበትን ምክንያት ሲያስረዱ፡
« መፍትሔ ለመስጠት ስል ነው ራሴን በዕጩነት ያቀረብኩት። ለሀገሪቱ ችግር መፍትሔ የሚያስገኘው ክፍል አካል ነኝ። ማህበራዊውን ተሳትፎ ለሚያራምድ ፖለቲካ የቆምክ ሲሆን፡ የሀገሪቱ ተቋማት በጠቅላላ ካላንዳች ውዝግብ መስራት የሚችሉበትን ዘዴ ማስገኘት የሚችል ዳኛ መሆን እፈልጋለሁ። ሟቹ ፕሬዚደንት ማላም ባካይ ሳና ይከተሉት የነበረውን በሳል አስተሳሰብ የታከለበትን ፖሊሲያቸውን የመተካት ሕልም አለኝ። »

ከረጅም ሕመም በኋላ ባለፈው ጥር ወር ያረፉት የቀድሞው ፕሬዚደንት ማላም ባካይ ሳና በሥልጣን በቆዩባቸው ሦስት ዓመታት ጊኒ ቢሳውን ከሙስና፡ ከተዛባ አስተዳደር እና የጦር ኃይሉ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ካሳረፈው ጠንካራ ተፅዕኖ ለማላቀቅ ሞክረዋል። ዋነኛው መፈክራቸው ለውዝግብ በድርድር መፍትሔ ማስገኘት የሚሰኝ ነበር። ይሁን እንጂ፡ ጊኒ ቢሳው በፕሬዚደንት ሳና አመራርም ቢሆን መረጋጋት ያልወረደባት ያልተረጋጋች ሀገር እንደሆነች ነው የቀጠለችው። ሚያዝያ 2010 ዓም ላይ የጦር ኃይሉ ዋና አዛዡን ሳሞራ ኢንዱታን ካላንዳች ምክንያት አንስቶ ማሰሩናና በርካታ የመንግሥቱን ባለሥልጣናትን፡ ጠቅላይ ሚንስትር ካርሎስ ጎሜስ ጁንየርን ጭምር ለብዙ ሰዓታት በቁጥጥሩ ማዋሉ የሚታወስ ነው። ያኔ ፕሬዚደንቱ እና ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ሁኔታ የማስለወጥ አቅም አልነበራቸውም። በ2011 ዓምም የጦር ኃይሉ እንደገና መፈንቅለ መንግሥት ቢያካሂድም ሁኔታው ከቁጥጥር እንዳይወጣ ማድረጉ ተሳክቶዋል።
በ 2009 ዓም በጊኒ ቢሳው በመጨረሻ በተካሄደው ምርጫ በማላም ባካይ ሳና የተሸነፉት የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑት ባለተቋሙ ኤንሪኬ ሮዛም ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ በዕጩነት ቀርበዋል። በ 2003 ዓም ከተካሄደው የጦር ኃይሉ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ኤንሪኬ ሮዛ ከዚያ በኋላ ለቀጠሉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱን በጊዚያዊ ፕሬዚደንትነት አገልግለዋል።


« በጊኒ ቢሳው የሚታየው የአለመረጋጋት ሁኔታ ከማህበራዊው ኢፍትሓዊነት ጋ እጅ ለእጅ የሚሄድ ነው። በሀኪም ቤቶች፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ እንዳለ በሚገባ እናውቃለን። ያለን። እና ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ምን ዓይነት ህብረተሰብ መገንባት እንደምንፈልግ ነው። የምንኖርበት ህብረተሰብ መምህራንና ዳኞች ደሞዝ የማይከፈሉበት፡ የትምህርት ቤቶች ሁኔታ እና ባጠቃላይ የኑሮው ሁኔታ የተበላሸበት ነው። »
በዚህም የተነሳ ኤንሪኬ ሮዛ ለጦር ኃይሉ ድጎማ እየተሰጠ ያለበትን ሁኔታ አጥብቀው ይቃወማሉ። የጦር ኃይሉ ስምንት ሺህ አባላትን ያጠቃለለ ሲሆን፡ አንድ ነጥብ ስድስት ሚልዮን ሕዝብ ላላት ንዑሷ ጊኒ ቢሳው ይኸው ቁጥር ብዙ እንደሆን ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት። እንደተሰማውም ሁለት ሺህ አምስት መቶ ወታደሮች በቅርቡ ጡረታ ይወጣሉ። በጊኒ ቢሳው የጦር ኃይል ውስጥ ተሀድሶ ለማነቃቃት የአውሮጳ ህብረት ያደረገው ሙከራ ከከሸፈ በኋላ ፡ ልክ እንደ ጊኒ ቢሳው የቀድሞ የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት የነበረችው አንጎላ በወቅቱ የዚችኑ ምዕራብ አፍሪቃዊቱን ሀገር ጦር ኃይል ተሀድሶን እንደገና ለማንቀሳቀስ እየሞከረች ነው።
የጦር ኃይሉን ተፅዕኖ መቆጣጠር ካልተቻለበት ድርጊት ጎን የህገ ወጡ አደንዛዥ ዕፅ ንግድ ለሀገሪቱ ትልቅ ፈታኝ ሁኔታ ፈጥሮዋል። ተገቢው ቁጥጥር የማይደረግባቸው በርካታ ደሴቶች ያሉዋት ጊኒ ቢሳው ከደቡብ አሜሪካ ወደ አውሮጳ ለሚያልፈው ህገወጡ አደንዛዥ ዕፅ ዋነኛ መሸጋገሪያ ድልድይ ሆናለች።
በምህፃሩ ፒ አር ኤስ የሚባለው የመሻሻልና የተሀድሶ ፓርቲ ዕጩ ኩምባ ያላ መንግሥት በዚሁ አሳሳቢ ህገወጥ የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ አንጻር በቂ ርምጃ አልወሰደም ሲሉ ወቅሰዋል።
« አደንዛዡ ዕፅ ጊኒ ቢሳው ሊገባ የቻለው በገዢው ፓርቲ ድጋፍ ነው። ይህ ጥያቄ ለገዢው መንግሥቱ ዕጩ ጠቅላይ ሚንስትር ካርሎስ ጎሜስ ጁንየር መቅረብ ይኖርበታል። እኛ የሀገራችን መንግሥት እና የግሉ የሕዝብ ኑሮ እንዳይታወክ ህገወጡን የአደንዛዥ ዕፅ ንግድን ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል። »
የፍልስፍና ትምህርታቸውን በፖርቱጋል ያጠናቀቁት እና ባንድ ወቅት ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ኩምባ ያላ እአአ በ 2000 ዓም በጊኒ ቢሳው በተካሄደው ነፃና ትክክለኛ ምርጫ አሸንፈው የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን ይዘው ነበር። ግን በርሳቸው አመራር ጊዜ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የመናገርና አስተያየት የመስጠቱ ነፃነት በጉልህ ነበር የተጨቆነው። ከሦስት ዓመት በኋላም እአአ በ 2003 ዓም ደም ባላፋሰሰ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው ተወገዱ። ያም ሆን ግን በ 2009 ዓም እንደገና ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በተወዳደሩበት ጊዜ ለሁለተኛው ዙር ምርጫ ደረሰው አንድ ሦስተኛውን የመራጭ ድምፅ ማግኘታቸው ይታወሳል። በነገው ዕለት በሚደረገውም ምርጫ፡ በጊኒ ቢሳው ካሉት ጎሳዎች በጠቅላላ ሠላሣ ከመቶውን በመሸፈን ትልቁ ከሆነው ከባላንታ ጎሳ ብዙ ደጋፊ ስላላቸው፡ ጥሩ ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችል ነው የሚጠበቀው። በነገው ምርጫ ከሚወዳደሩት ዕጩዎች መካከል አንዱ ከሀምሣ ከመቶ የበለጠ ድምፅ ካላገኘ ቀደሚዎቹን ሁለት ቦታ በያዙት መካከል ሁለተኛ ዙር ምርጫ ይደረጋል።
አርያም ተክሌ/ሄለና ደጉቪያ
መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 23.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/14MC6
 • ቀን 23.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/14MC6