ፈላስያን ሠራተኞችና የኤኮኖሚው ቀውስ፣ | ዓለም | DW | 05.11.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ፈላስያን ሠራተኞችና የኤኮኖሚው ቀውስ፣

በግሪክ መዲና በአቲና፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያዘጋጀው ፈላስያን ሠራተኞችን የሚመለከት ጉባዔ ትናንት ተጀምሯል።

default

ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ፣ ወደ አውሮፓ ለመግባት፣ በእስፓኝ ፣ካናሪ ደሴቶች በኩል የተንቀሳቀሱ አፍሪቃውያን ሥራ ፈላጊዎች፣

በጉባዔው የተገኙ ጠበብት፣ የኤኮኖሚ ቀውስንና የፈላስያን ሠራተኞችን ይዞታ የተመለከቱ ጥናቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የግሪክ መንግሥት በበኩሉ፣ መንግሥታት ፣ በዚህ ዓቢይ ጉዳይ ላይ፣ ማለትም ሥራ ፍልጋ ከተለያዩ አገሮች የሚሰደዱ ሰዎችን ይዞታ፣ የኤኮኖሚ ቀውስ ያሳዳረባቸውን ተጽእኖ፣ በሚኖሩባቸው አገሮችም የቱን ያህል በኅብረተሰቡ ታቅፈው እንደሚኖሩ ፍጹም ለማትኮር አልፈለጉም ሲል ነቅፏል። ዓለም አቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ፣ በውጭ ሀገራት ከሚሠሩ ሰዎች ወደ ትውልድ አገራቸው የሚላከው የገንዘብ መጠን እጅግ እንዲቀነስ ሰበብ ሆኗል ። ለምሳሌ ያህል በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ደርሶ እንደነበረ የተነገረለት ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ አገራቸው የሚልኩት የገንዘብ መጠን ወደ 10 ከመቶ ገደማ መቀነሱ ነው የሚነገረው። የሶማሌዎች ደግሞ 25 ከመቶ ነው የቀነሰው። የሶማልያ ተወላጆች፤ ወደ ትውልድ አገራቸው የሚልኩት የገንዘብ መጠን 1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ከአቴንስ ፣ ከያኒስ ፓፓዲሚትሪው የተላከውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

ከትውልድ አገራቸው ፈልሰው፣ ሥራ ፍልጋ፣ በዓለም ዙሪያ የተበተኑ ሰዎች፣ በዓለም አቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ክፉኛ መጎነጣቸውን አቲና ፣ ግሪክ ላይ የተሰበሰቡ ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠበብት አስታውቀዋል። በውጭ ሀገራት እየተከሩ ወደ ትውልድ አገር የሚልኩት የገንዘብ መጠን ከብዙ ዓመታት ወዲህ ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን በማሽቆልቆል የ 6% ፣ ማለትም የ 317 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱ፣ አይቀርም ነው የተባለው። እ ጎ አ ከ 2011 በፊት ይህ አሉታዊ አዝማሚያ ይገታል ተብሎም አያታሰብም። በመሆኑም ገንዘብ ወደ ትውክድ አገር የሚልኩ ሰዎች በቀላል ክፍያ የሚያሸጋግሩበት ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት «ኦንላይን አገልግሎት» እንዲቋቋም የሚል ሃሳብ ቀርቧል። የቅርቡ የተባበሩትን መንግሥታት የጥናት ውጤት ያቀረቡት ወ/ሮ ጀኒ ክሉግማን ፣ ፋላስያን ሠራተኞች ከባድ ዘመን የሚጠብቃቸው ይላሉ።

«ፈላስያን ክፉኛ ነው የተጎዱት። የኤኮኖሚው መዳከም ሥራ የማግኘት ዕድልን አማናምኗል። ሥራ አጥነት ፣ በአጥፍ ነው የጨመረው። የውጭ ተወላጆቹ ደግሞ በሰፊው ተሠማርተው የነበሩት በጣም ክሥረት ባጋጠመው በግንባታው ዘርፍ ነው። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ባወጣነው የጥናት ውጤት መሠረት ፣ ፈላስያን ሠራተኞች በአመዛኙ የሚገኙት፣ በኤኮኖሚ ቀውስ እጅግ በተጎነጡት ዩናይትድ እስቴትስን በመሳሰሉ አገሮች ነው። ስለዚህ እነዚሁ ባዕዳን ሠራተኞች በግልጽ ነው የኤኮኖሚው ቀውስ ሰለባዎች የሆኑት።»

በውጭ ሀገራት ሥራ ፍለጋ የተሠማሩ ፈላስያን፣ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ መንግሥታት፣ ከሚሰጡት የልምታ እርዳታ እጅግ የላቀ ገንዘብ ነው ወደመጡበት ሀገር የሚልኩት። ¾ኛው ገንዘብ የሚላከው በአውሮፓና በዩናይትድ እስቴትስ ከተሠማሩት ነው። ይሁን እንጂ ወ/ሮ ጀኒ ክሉግማን እንዳስረዱት አስተናጋጆቹ አገሮች፣ በፈላስያኑ ሠራተኞች የኤኮኖሚ ኃይል ተጠቃሚዎች ናቸው። እናም ፣ በአንዱስትሪ የገሠገሡት አገሮች፣ የኤኮኖሚ ቀውስን አሳበው ፣ የውጭ ሰዎች እንዳይገቡ የሚከተሉት የፖለቲካ መርኅ ግራ የሚያጋባ ነው።

«እርግጥ ነው፣ ከውጭ ሀገራት ፈልሰው በመግባት፣ በሙያቸው የተሠማሩ ሰዎች፣ ይሠራሉ ፣ ሸማቾችና ገዥዎች በመሆናቸውም ለሚኖሩበት አገር የኤኮኖሚ ጠቀሜታ ይሰጣሉ። የኤኮኖሚ መዳከም አስደንጋጭ ሆኗል፣ የአጭር ጊዜ ድንጋጤ ነው። ግን የረጅም ጊዜ የግንባታ ሂደትን ና የሚያስከትለውን ሁኔታ መመልከት፣ በእርግጥ ይበጃል። እኛ ያቀረብነው ጥናት ከ OECD የጥናት ውጤት ጋር ተማሳሳይ ነው። ግራም ነፈሰ ቀኝ ከውጭ ፈልሰው የገቡ ሠርቶ -አደሮች፣ ለዕድገትና ለአዳዲስ የሥራ ፈጠራዎች አለኝታዎች ናቸው።»

ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ በታየበት በአሁኑ ወቅት ህግ ወጥ በሆነ መንግድ ካገር -አገር የሚዘዋወሩት ሰዎች ቁጥር እየቀነስሰ በመሄድ ላይ መሆኑም ይነገራል። የግሪክ ፈላስያን ጉዳይ ተመልካች ተቋም ኀላፊ አለክሳንድሮስ ዛቮስ፣ የሆነው ሆኖ ለየት ያለና ገሐዳዊውን ይዞታ የሚያንጻባርቅ አቋም ነው ያላቸው።

«በሰው የሚነግዱ፣ ፈላስያንን ወደ ባለጸጎች አገሮች እያሾለኩ የሚያስገቡ ሰዎች፣ ወደፊት እነዚያው ሥራ ፈላጊዎች በሚኖሩበት አገር ከሚያፈሩት ገንዘብ ነው የሚከፈላቸው። ነገር ግን ፣ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሥራ ፈላጊዎችን ካገር አገር በድብቅ የሚያስገቡ ቡድኖች ፣ ሥራ እንደማይገኝ ሥጋት ሲያድርባቸው ፣ ሥራ ፈላጊዎችን በሥውር ካገር አገር ለማሸጋገር በቂ ምክንያት አይኖራቸውም። »

የሆነው ሆኖ፣ ሰዎችን ከቦታ ቦታ የሚያሸጋግሩ ህገ-ወጥ ቡድኖች ኖሩ-አልኖሩ፣ የተሻለ ሥራ ይገኛል ብሎ በማሰብ የሚንቀሳቀሰውን መግታት የሚቻል አይመስልም። በአቲናው ጉባዔ የቀረበው የጥናት ውጤት እንደሚያስረዳው፣ በኢንዱስትሪ ወደ በለጸገ አገር እንደምንም ብለው የሚገቡ ሥራ ፈላጊዎች፣ በትውልድ አገራቸው ያገኙት ከነበረው 15 እጥፍ ገቢ ያገኛሉ። ለዚህም ነው ይላሉ ጥናቱን ያቀረቡት ሰዎች፣ በአሁኑ ጊዜ፣ ከ 215 ሚሊዮን ህዝብ በላይ፣ ከትውልድ አገሩ ፈልሶ በሌላ ሀገር የሚኖረው።

ተክሌ የኋላ/ነጋሽ መሐመድ