ግብፅ-ምርጫና ተቃዉሞ ሠልፍ-ሶሪያ ማዕቀብ | ዓለም | DW | 28.11.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ግብፅ-ምርጫና ተቃዉሞ ሠልፍ-ሶሪያ ማዕቀብ

የዛሬዉ ምርጫ ግን እንደ ታሬኽ-ሚስት ወላጅ-ዉላጆቻቸዉን በትነዉ ለሕዝብ ጥያቄ መስዋዕት የሆኑ በትንሽ ግምት-የስምንት መቶ ሐምሳ ግብፃዊን ሕይወት-፥የሺዎች አካል-ደም ዉጤት፥ የሚሊዮኖች ያላሰለሰ ትግል-ድል ነፀብራቅ መሆኑ አያጠያይቅም።

default

ምርጫ

በ1950-60 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የገማል አብድናስር አብዮት-ድፍን ዓረብን ሲያነቃንቅ-ካይሮ ላይ የተመሠረተዉ የግብፅና-የሶሪያ ሕብረት-የአረብ አንድነት ታላቅ-አብነት መስሎ ነበር።ካይሮ-ዛሬ ዜግነት-አላማ የሚያስተሳስረዉን አንድ ሕዝብ ለአመፅ-ምርጫ ተቃርኖ እሁለት ሥፍራ አሰልፋለች።ትናንት የአረቦች የጋራ ማሕበር-የአረብ አንድነት አብነት የነበረችዉን ሐገር ቀጥቶባታል።ሶሪያን።የግብፅ-ሁለት እዉነት፥የአረቦች አንድነት-ከንቱነት በሶሪያ ላይ የተጣለዉ ቅጣት እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ጥምር ቅኝት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

የትልቂቱን ከተማ ትልቅ አደባባይ፣ከትልቁ አደባባይ የሚያደርሱትን ብዙ ጎዳኖች-ነብስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ያዉቃቸዋል።በ2006 ሥራ ከያዘ ወዲሕ ደግሞ ጧት-ማታ ትልቁን አደባባይ ያቋርጧል። አደባባዩን ከሚዋሰነዉ ትልቅ ጎዳና ዳር ሲሰራ-ይዉላል።የትልቂቱ ከተማ ትንሽ ትዉልድ ሥለ ትላልቆቹ ሥፍሮች የዛሬ ትዝታዉ-መሠረት ያን አካባቢ እድሜ ልኩን ማወቁ ነዉ ቢባል በርግጥ እዉነት ይመሳል።እሱ እንደሚለዉ ግን እዉነት መምሰሉ ራሱ ስሕተት ነዉ።

«በዚሕ በኩል ባለፍኩ ቁጥር ነፃነታችንን አስባለሁ።ለነፃነት ያደረግነዉ ፍልሚያ ትዝ ይለኛል።»

ሸሪፍ አልዓ-አብደል አዚም።

ሕዝባዊዉ ፍልሚያ ዛሬም ዒላማዉን ለዉጠ-እንጂ አላባራም።ከጥር ሃያ-አምስት ጀምሮ-የፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ የሰላሳ ዘመን ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት የመገርሰሱ ድል እስከበሰረበት እስከ የካቲት አስራ-አንድ በሕዝብ ጎርፍ ተጥለቅልቆ የነበረዉ ትልቅ አደባባይም ለሌላ ፍልሚያ በቆረጠ ሕዝብ እንደ ተሞላ ነዉ።

ወጣቱ ሸሪፍ አምና ጥር መጀመሪያ እንደ ብዙ ብጤዎቹ መጀመሪያ ፈራ-ተባ፣ደረስ-ሰለፍ፣ ፈከር-መለስ ደግሞ ደበቅ፣ እያለ፥ ኋላ ጭልጥ ብሎ ካመፀመበት፣ ድንኳን ተክሎ አስራ-ስምንት ቀን ከከተመበት ዘንድሮ አልሰፈረም።

ሸሪፍ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትንና ዲሞክራሲያዊ ምርጫን የሚያደራጀዉ የግብፅ መስሪያ ቤት ባልደረባ ነዉ።ዛሬ የተጀመረዉን የምክር ቤት አባላት ምርጫን እንደ ባለሙያም-እንደ አብዮተኛም በማደራጀት-ማዘጋጀቱ ሲባትል ነዉ-የከረመዉ።ምርጫዉ የግብፅ ሕዝብ ትግል-ድሉን ከአንድ እመርታ የሚደርስበት ነዉ ብሎ ያምናል።

ምርጫዉ ለግብፅ ሕዝባዊ አብዮት ታላቅ እመርታ ነዉ-ብሎ በማመኑ፣ እምነቱን እንደ አብዮተኛም እንደ ባለሙያም ገቢር ለማድረግ ሲባትል በመክረሙ ምክንያት ሰሞኑን በሚደረገዉ የአደባባይ ሠልፍ-ያለፈዉን ያክል አልተካፈለም።ወደዚያ አደባባይ ባለፍ አገደም ብቅ ማለቱ ግን አልቀረም። የሆስኒ ሙባረክን ሥልጣን የተረከቡትን ወታደራ ገዢዎች በመቃወም አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ጥያቄም ተገቢ ነዉ-ባይ ነዉ።

Ägypten Demonstration Tahir Platz November 2011

አመፅ

«እንዳለመታደል ሆኖ አብዮቱ ከእጃችን ሊያመልጥ ተቃርቧል።አንዳድ ሰዎች እንደሚሉትማ ጦሩ አብዮቱን ቀምቶናል።» ሸሪፍ እንደሚያምነዉ የአብዮቱ ፍሬ ከሕዝቡ እጅ እንዳይወጣ የዛሬዉ ምርጫ ጥሩ ጋሻ-የአደባባዩ ሠልፍ ደግሞ ሐያል መከታ ይሆናሉ።የሸሪፍን እምነት የሚጋሩ-የመኖራቸዉን ያክል የሚቃወሙትም ብዙዎች ናቸዉ።በምርጫዉ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኛል ተብሎ የሚታመነዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ የምርጫዉን መደረግ-አጥብቆ ደግፎታል።በሁለት ምክንያት።-እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ጠቀም ያለ-የምክር ቤት መቀመጫዎችን ለማግኘት።-አንድ።ሕዝባዊዉን አብዮት ሙሉ በሙሉ ከጦሩ ቁጥጥር ለማትረፍ።-ሁለት።

የግብፅ ሕዝብ ሠላሳ-ዘመን ሥር የሰደደዉን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ያስወገደዉ የመፈክር-ካርቶን፣ የአስለቃሽ ጢስ መከላከያ እራፊ ጨርቅ፥ እጅግ ሲጠነክር ድንጋይ ታጥቆ፥ ታንክ-መድፍ፣ ጠመንጃ-መትረየስ ከታጠቀ ግዙፍ ሐይል ጋር ተጋፍጦ-ብዙ ወገኖችን ሰዉቶ ነዉ።በሙባረክ-የተመለመሉ፣ የተሾሙ-የተሸለሙ፣ በሙባረክ የሚታዘዙት ጄኔራሎች የዚያን ጀግና ሕዝብ ትግል ለማፈን እንደተዉተረተሩ ሁሉ ዉጤቱን-ለመቀማት አልሞከሩም ማለት በርግጥ ያሳስታል።የሕዝቡ ዳግማዊ አመፅ ሲቀጣጠል ግን ለሕዝብ ጥያቄ-ባይንበረከኩ ማጎንበሳቸዉ አልቀረም።

«የሚከተለዉን ወስኛለሁ።በዶክተር ኢሳም ሻራፍ የሚመራዉ መንግሥት ያቀረበዉን የሥልጣን መልቀቂያ ተቀብያለሁ።አዲስ መንግሥት እስኪመሠረት የሽግግር ዘመኑን ከፍፃሜ ለማድረስ በሚደረገዉ ጥረት የሻራፍ መንግሥት ከጦር ሐይሉ ተባብሮ ሥራዉን እንዲቀጥል ሙሉ ሐላፊነት ተሰጥቶታል።የምክር ቤት አባላት ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ይደረጋል።ፕሬዝዳንታዊዉ ምርጫ ደግሞ ሰኔ ማብቂያ ይደረጋል።ጦሩ በፍተኛዉ ምክር ቤት በተወከሉ ባልደረቦቹ አማካይነት ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት የለዉም።ሕዝብ የሚሰይመዉ ሐይል አመራሩን ለመረከብ ዝግጁ እስከሆነ ድረስ ጦሩ ሥልጣኑን አስረክቦ የእናት ሐገሩን ሰላምና ደሕንነት ወደ ማስከበር ሐላፊነት ለመለስ ዝግጁ ነዉ።»

ፊልድ ማርሻል ሁሴይን ታንታዊ።ባለፈዉ ሳምንት ሮብ።

ታንታዊ የሚመሩት ወታደራዊ ምክር ቤት ፀጥታ አስከባሪዎች ለገደሏቸዉ ተቃዋሚዎች በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብም ቃል ገብቷል።ተሕሪር አደባባይን ዳግም ያጥለቀለዉ ሕዝብ ግን የማርሻል ታንታዊን እርምጃ-ቃልም ሆነ ተስፋ አልተቀበለዉም። አላመነቸዉምም።ሰልፉን ከሚያደራጁት አንዳዶቹ እንደሚሉት ደግሞ የታንታዊ-ቃል ጊዜ-መግዣ፥ ተስፋዉ ፕሮፓ ጋንዳ የዛሬዉ ምክር ቤታዊ ምርጫም ማደናገሪያ ነዉ።

ሰልፉ ዛሬም-ድምፅ በመስጡ መሐል እንደቀጠለ ነዉ።የተቃዉሞ ሠልፍ-እና ድምፅ የመስጠቱ ሠልፍ የዚያን ወጣት ልብ እሁለት እንደከፈለዉ ነዉ።የሸሪፍን።ባለፈዉ ሳምንት ግን ከምርጫ ዝግጅቱ ጥድፊያ፣ ከሥራ ዉጥረቱ ፋታ-ጋዜጠኛዉን ተከትሎ ከቢሮዉ ወጣ።

ትልቁን የካይስር አል-አይኒይ ጎዳናን ይዘዉ ወደ ትልቁ-አደባባይ አቀኑ።ተመልከት አለ ሸሪፍ-ጣቱን ከትልቁ ጎዳና ግራ ቀኝ ከተገጠገጡት ትላልቅ ሕንፃዎች ወዳ አንዱ እያመለከተ።የሕንጻዉ በር-መስኮቶች ተሰባብረዋል።ከፊል ደርቦቹ ተቃጥለዋል።ሌሎቹ ወላልቀዋል።

«የሐይል እርምጃ አልወድም» አለ-ይሕ ሕንፃ እንዲሕ ሆኖ ሳይ ግን ግብፅ የመለወጧ ምስክር እያልኩ አስባለሁ።ለዘመናት በግብፅ ሕዝብ ላይ የተፈፀመዉን ግፍ-በደል እዚሕ ነበር የሚወሰነዉ።» እያለ ወሬዉንም ጉዞዉንም ቀጠለ።---ሕንፃዉ-ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (NDP) የተሰኘዉ የሆስኒ ሙባረክ የፖለቲካ ማሕበር ፅሕፈት ቤት ነበር።

ከፓርቲዉ ሕንፃ ፈቀቅ ብለዉ የሕግ-መወሰኛ እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤቶች ሕንፃዎች ከነ ሙሉ ዉበት-ግዝፈታቸዉ ጎን ለጎን ተገጥግጠዋል።ለሙባረክ ሥርዓት ፅናት በሙባረክ ፍቃድና ይሁንታ ይሰየሙ የነበሩት የይስሙላ እንደራሴዎች ከሚሰበሰቡባቸዉ ሕንፃዎች ጥቂት አለፍ ብሎ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ለሙባረክ አገዛዝ ሁለንተናዊ ድጋፍ የመስጠቷ-ምልክት ይመስል ሌሎች ዉብ ሕንፃዎች ተንጣለዋል።የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ሕንፃዎች።

ምርጫ-በማዘጋጀት ማደራጀት ሲጣደፍ የከረመዉን ወጣት-አዕምሮ የያዙት ግን የሁለቱ ምክር ቤቶች ሕንፃዎች ነበሩ።«ከእንግዲሕ የሕዝብ አገልጋዮች መገልገያ---» ሐሳቡን ሳይቋጭ ከትልቁ አደባባይ ደረሱ።ተሕሪር።የሕዝባዊ ትግል-ገድል ታላቅ አዉድ። የሕዝባዊ ድል-ታላቅ ታሪክ ትልቅ ምስክር።

«መንገዶቹ ያዉ ናቸዉ።አልተለወጡም።እኔ ሥለ ከተማዋ በተለይ ደግሞ ሥለ ተሕሪር አደባባይ ያለኝ ግንዛቤ ግን ከአብዮቱ ወዲሕ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል።»

ታሬኽ አብደል ለጢፍ የማሽን ኢንጂነር እንጂ የሸሪፍን ያክል እንኳ የፖለቲካ ፍላጎት እዉቀቱም የለዉም።በሙያዉ በነፃነት የመስራት፥ሁለት-ልጆቹን፥ ባለቤቱንና እራሱን ለማስተዳደር ያደረገዉ ጥረት ሙከራ አልሰምር ቢለዉ ወደ ካናዳ ለመሰደድ ወሰነ።ሙያዉም እድሉም የተመኘዉን አልነፈገቱትም።

ካናዳ የመግቢያ እና የሥራ ፍቃዱንም ተረከበ።ጥር ሊያበቃ ዕለታት ቀሩት።በዚያ ሳምንት የዋለዉ አርብ ለታሬኽ በርግጥ ድርብ በዓል ነበር።በድርቡ በዓል-ከጁማዓዉ ሶላት ግዴታዉንም ምስጋናዉንም አድርሶ ከመስጊድ ሲመለስ ልክ እንደ ሸሪፍ ልክ እንደ ሚሊዮን ብጤዎቹ ከጥርጣሬ-ሥጋት ጋር ወደ ቲሕሪር አደባባይ ጎራ አለ።ቤቱ እንደ ገባ ለባለቤቱ-ለራኒያ ያየ-የሚሻዉን አጫወታት።

«ከዚያ ወደ ቤት ሲመለስ ብዙ የተሰባባሩ መኪኖች ማየቱን አስረዳኝ።የግብፅ ሁኔታ እየተቀየረ ነዉ-የሚል ሥሜት እንዳደረበት አስረዳኝ።ሕዝባዊ አመፅ የተለመደዉ አይነት ሠልፍ አይደለም አለኝ።እና ወደ አደባባይ ተመልሶ መሔድ እንዳለበት ነገረኝ።

የዚያን ቀን ሄደ።በማግስቱ ደገመ በሳልስቱ-አሰለሰም።ግን አልተመለሰም።ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን ተወገደዋል። የነሸሪፍ ድንኳንም ከተሕሪሪ አደባባይ ተነቃቅሏል።በፊት የብሶት-መከራ የቁጣ መፈክር-ጩኸት ኋላ የድል ጮራ ጮቤ ሲረገጥ-ሲዘፈንበት የከረመዉ አደባባይ ቁሻሻ-ፅዳጁን አራግፎ-ፅዳት ፀጥታዉን ተጎናፅፏል።የካቲት አልፎ የመጋቢት የመጀመሪያ ሳምንትም አበቃ።

ታሬኽ ግን ወደ ቤቱ አልተመለሰም።መጋቢት ስምንት።የዚያን ቀን «አንድ ሰዉ የታሬኽ ወላጆችን ቤት አንኳኳ» አለች ባለቤቱ በቀደም።

«ሰዉዬዉ ሰዉ ጠፍቶባቸዉ እንደሆነ ጠየቃቸዉ።ወላጆቹ አዎ ልጃችን ጠፍቶብናል ብለዉ መለሱ።ሰዉዬዉ ወላጆቹንና የታሬክን ወድም ወደ አስከሬኑ ወዳለበት ሆስፒታል ይዟቸዉ ሔደ።»

እሩቅ አሳቢዉ ቅርብ አደረ።ካናዳ አላሚዉ፥ ካይሮ ተቀበረ።ከታሬኽ በፊትና በሕዋላ ብዙዎች ተሰዉተዋል።ሕዝባዊዉ አመም ዛሬም ቀጥሏል።የዛሬዉ ምርጫ ግን እንደ ታሬኽ-ሚስት ወላጅ-ዉላጆቻቸዉን በትነዉ ለሕዝብ ጥያቄ መስዋዕት የሆኑ በትንሽ ግምት-የስምንት መቶ ሐምሳ ግብፃዊን ሕይወት-፥የሺዎች አካል-ደም ዉጤት፥ የሚሊዮኖች ያላሰለሰ ትግል-ድል ነፀብራቅ መሆኑ አያጠያይቅም።

በ1958 ከግብፅ ጋር «የተባበሩት አረብ ሪፐብሊክ» የተሰኘዉን የጋራ-መንግሥት መስርታ የነበረችዉ የሶሪያ ሕዝብ እንደ ቱኒዚያ ግብፅ ሁሉ ከግብፅ ብጤዎቹ እኩል-እንደባባይ ሲወጣ የቱኒስ-ካይሮ ብጤዉን ድል-ደማስቆ ላይ ተመኝቶ ነበር።

በቱኒዚያዎችና ለቱኒዚያዎች ያለመዉ ሕዝባዊ አመፅ-የቱኒዚያ ወጣቶች መስዋዕትነት ከግማሽ ብዙ የራቀ ድል፥ ግብፆች እራሳቸዉ፥ ለራሳቸዉና በራሳቸዉ ያደረጉት ፍልሚያ-ገድል የከፈሉት መስዋዕትነት ቢያንስ ግማሽ ድል ላይ መቆሙ ሲነገር-ሲመሰከር ዛሬ ሶሪያዎች ተጨማሪ ወገናቸዉን መስዋዕት እያደረጉ ነዉ።ከሰስት ሺሕ አምስት መቶ በላይ።

በዚሕ መሐል የአረብ ሊግ መሪዎች ከሳምንት በፊት ራባት-የሔዱት የሞሮክ ሕዝብ በረጅም ጊዜ ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንፃራዊ ነፃነት ያደረገዉን ምርጫ ለመታዘብ አልነበረም።የአረብ ሊግ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ትናንት ካይሮ የተሰበሰቡት የግብፅ ሕዝብ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ባደረገና በሚያደርገዉ ትግል ከጎኑ መቆማቸዉን ለመግለፅ አልነበረም።ሶሪያን ለመቅጣት እንጂ።

Treffen der Minister der Arabischen Liga

የዓረብ ሊግ ስብሰባ


«የምንሠራዉ በሙሉ ጣልቃ ገብነትን ለማስወገድ ነዉ።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በዚሕ ጉዳይ ላይ የእኛን አቋም ከልቡ ተቀብሎ ዉጤት ካላስገኘ ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር ዋስትና መስጠት አልችልም»

የቀጠሩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሼኽ ሐማድ ቢን አል-ሳኒ።ትናንት።በያዝነዉ ዘመን እነ ቀጠር የሚዘዉሩት የአረብ ሊግ አ-ሳኒ እንዳሉት በአባል ሐገራት የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ-አይገባም።ግን መስራቾች አባሉን-አባረረ።ትናንት ደግሞ በማዕቀብ ቀጣ።ቅጣቱ የአል-አሰድን አምባገነናዊ አገዛዝ ለከፋ ብቀላ አነሳስቶ-ተቃዋሚዎቹን ይበልጥ እንዲገድል-እንዳያስር ላለማድረጉ ምንም ዋስትና አይሰጥም። የዚያኑ ያክል ከአሰድ መንግሥት እኩል-የሶሪያን ሕዝብ፥ ከሶሪያ እኩል ሊባኖስ፥ ኢራቅ፥ ዮርዳኖስን መጉዳቱ ነዉ-እንቆቅልሹ።የአረብ ሕዝባዊ አመፅ-በቱኒዝ ካይሮዉ ድል ማግስት ትሪፖሊ ላይ አዲስ መስመር ተበጅቶለታል። ለሰነዓ ሌላ-መንገድ፥ ለደማስቆ-ደግሞ ሌላ።ግን ቀጥሏል።እኛ ይብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ
Audios and videos on the topic