ጋዜጠኞቹ እስራት ተበየነባቸው | ኢትዮጵያ | DW | 03.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ጋዜጠኞቹ እስራት ተበየነባቸው

ኢትዮጵያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለት ጋዜጠኞችን ጨምሮ በ19 ተከሳሾች ላይ ዛሬ የቅጣት ዉሳኔ ሰጠ። የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ሰኢድ አብደላ ለዶቼቬለ እንደገለጹት በሽብር ህጉ መሰረት ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾቹ  ጽኑ እስራት ተበይኖባቸዋል ። ለጋዜጠኞች መብት የሚከራከረዉ ድርጅት ሲ ፒ ጄ በጋጠኞቹ ለይ የተላለፈዉን የእስር ቅጣት አወግዟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:13

ጋዜጠኞቹ እስራት ተበየነባቸው


የኢትዮጵያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬዉ እለት በአድስ አበባ ከተማ ባስቻለዉ ችሎት ፤ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪንና ካሊድ መሀመድን ጨምሮ በ19 ተከሳሾች ላይ የእስር ቅጣት ዉሳኔ ማስተላለፉን የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ሰኢድ አብደላ ለዶቸቬለ ተናግረዋል። እንደ ጠበቃ ሰኢድ ገለጻ ከአሸባሪወች ጋር በመተባበር የሚል ክስ ተመስርቶባቸዉ ላለፉት ሁለት አመታት ጉዳያቸዉ በፍርድ ቤት ሲታይ የቆዩት 19ኙ ተከሳሾች፤ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ናችሁ በመባላቸዉ ከ4 አመት እስከ 5 አመት ከስድስት ወር የሚደርስ ጽኑ እስራት ተወስኖባቸዋል ብለዋል።
                      
በሽብር ህጉ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 1 ን ተላልፋችሁ የሽብር ድርጅት ዉስጥ በመሳተፍ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ እባላት የሆኑትን  እነአቦበክር አህመድን እናስፈታለን ብላችሁ ተንቀሳቅሳችሗል  በሚል ጥፋተኛ እንደተባሉ የገለጹት ጠበቃ ሰኢድ አብደላ፤ ለተከሳሾቹ በተሰጠ የጥፋት ማቅለያ መሰረት ፍርዱ እንደተበየነ ተናግረዋል።
13 ተኛ ተከሳሽ ዳርሰማ ሶሪ በጤናዉ ላይ እክል ስላጋጠመዉ እንደ አንድ የቅጣት ማቅለያ ተወስዶ ከተከሳሾቹ መካከል እሱ ብቻ በ4 ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራት መቀጣቱን ጠበቃዉ ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ በተባሉበት ወንጀል በሰዉም ይሁን በንብረት ላይ ያደረሱት ጉዳት ባለመኖሩ በዝቅተኛ የቅጣት ዉሳኔ ሊቀጡ ሲገባ በመካከለኛ የቅጣት ዉሳኔ ብይኑ መተላለፉ  ቅሬታ እንዳሳደረባቸዉ ጠበቃዉ አብራርተዋል። በማስረጃ ረገድም በአቃቤ ህግ ደረጃ የቀረበዉ ማስረጃ ተከሳሾቹን  ጥፋተኛ ለማስባል በቂ ያልነበረና የዓይን ምስክር ሳይቀርብ ተከሳሾቹ ለፓሊስ በሰጡት ማስረጃ  ላይ ብቻ የተላለፈ የቅጣት ዉሳኔ በመሆኑ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አቶ ሰኢድ አስረድተዋል።

ለጋዜጠኞች መብት የሚከራከረዉ ድርጅት በምህጻሩ ሲፒጄ በበኩሉ በሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ የተላለፈዉን የእስር ቅጣት አውግዟል ። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የ ሲፒጄ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሙረቲ ሙቲጋ ብይኑን አሳዛኝ ብለውታል ። 
«ለጋዜጠኞች መብት የሚከራከረዉ ድርጅት  cpj የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ያስተላለፉትን ይህንን ዉሳኔ በጥብቅ  ያወግዛል። በእኛ እምነት ጋዜጠኞች  ስራቸዉን ስለሰሩ ብቻ መታሰር የለባቸዉም።ኢትዮጵያ ብዙ ጋዜጠኞችን ማሰር  መቀጠሏ በጣም አሳዛኝ ነዉ።በእነዚህ ሁለት ጋዜጠኞች የተላለፈዉ የእስር ዉሳኔም በጣም አሳዛኝ ነዉ።ይህ የሚያሳየዉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ለይ የሚወስዱትን እርምጃ  እንደገና በደንብ ሊፈትሹ እንደሚገባ ነዉ።»
የጋዜጠኖች እስር የመረጃ ነጻነትን የሚጋፋ በመሆኑ በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ሁሉ በነጻ እንዲለቀቁም ሙረቲ ሙቲጋ ጥሪ አቅርበዋል።
ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic