ጋና እና የነዳጅ ዘይቱ ምርትዋ | ኢትዮጵያ | DW | 05.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ጋና እና የነዳጅ ዘይቱ ምርትዋ

ጋና በባህር ጠረፍዋ ከሚገኘው ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ንጣፍ ካለፈው ታህሳስ ወዲህ የነዳጅ ዘይት ማምረት ጀምራለች።

default

በጠበብት ግምት መሰረት በዚሁ የባህር ጠረፍ አለ የሚባለውን እስከ አራት ቢልዮን በርሜል የነዳጅ ዘይት የማውጣቱን ስራ የብሪታንያ እና ያሜሪካውያን ኩባንያዎች እያካሄዱ ነው።

የጋና መንግስት ከዚሁ ከነዳጅ ዘይት የሚገኘው ገቢ ለሀገሪቱ ልማት ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚያስገኝ ተስፋ አድርጓል፤ የሀገሪቱም ህዝብ ከድህነት እና ከለጋሽ ሀገሮች ርዳታ እንደሚያላቅቀው ተስፋ አድርጓል

Ghana Öl Geld

ያለፉ አንዳንድ ተሞክሮዎች እንደሚጠቁሙት ግን፡ የጥሬ አላባ ግኝት የሚጠበቀውን አዎንታዊ ውጤት በማስገኘት ፈንታ ተጻራሪውን ሁኔታ ሊያስከትል ይችላል። ናይጀርያን በምሳሌነት መጥቀስ ይበቃል። ከአንጎላ ቀጥላ በአፍሪቃ ሁለተኛዋ የነዳጅ ዘይት አምራች የሆነችው ናይጀርያ ከነዳጅ ዘይቱ ሽያጭ የተገኘው ገቢ የተፈጥሮ ሀብት በሚወጣበት አካባቢ ሁከት እንዲነሳ፡ ሙስና እንዲስፋፋ እና አካባቢ እንዲበከል ምክንያት ሆኖዋል። ብዙዎች ይገኛል ብለው የጠበቁት ብልጽግና ገሀድ ሳይሆን ነው የቀረው፤ በዚህ ፈንታ የተወሰኑ ባለስልጣናት ብቻ እስከዛሬ ድረስ ተጠቃሚዎች ሆነዋል።

በጀርመን ኤኮኖሚ ድርጅት የአፍሪቃ ማህበር ባልደረባ የሆኑት ፓትሪክ ሮይተር ግን የጋና ሁኔታ ከናይጀርያ የተለየ ነው ብለው ያምናሉ።

Goldgewinnung Ghana

« አካባቢውን እና ባካባባኢው ያሉትን ነዳጅ ዘይት አምራች ሀገሮችን ስንመለከት ጋና ከሁሉም የበለጠ መረጋጋት የሰፈነባት ሀገር መሆንዋን እናያለን። ካለፉት ሀያ ዓመታት ወዲህ በትክክለኛ እና ነጻ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የህግ የበላይነትን አረጋግጣለች። የተጠናከረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የምትከተል ሀገር ናት። »

ማዕድኑን ወርቅ እና ካካዎን ወደ ውጭ በንግድ በመላክ በዓለም ሁለተኛነቱን ቦታ የያዘችው ጋና ጥሩ ዕድገት ያሳየ የምጣኔ ሀብት አላት። ይሁን እንጂ፡ ከጋና ህዝብ መካከል ከማዕድኑ ወርቅ ሽያጭ ገቢ እስካዛሬ ድረስ ተጠቃሚ የሆነው ጥቂቱ ብቻ ነው። በተመድ መዘርዝሮች መሰረት፡ ከጋና ህዝብ መካከል ሰላሳ ከመቶው አሁንም በከፋው ድህነት ውስጥ ነው የሚገኘው።

አሁን የነዳጅ ዘይቱ ምርት ከተጀመረ ወዲህ የሀገሪቱ መንግስት የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ቃል ገብቷል። የጋና መንግስት ከወርቁ ምርት ሽያጭ የተገኘውን ገቢ በሚገባ ያላዋላበትን ስህተት አሁን ለመድገም እንደማይፈልግ በበርሊን የሚገኙት የጋና አምባሳደር ለጀርመን ኤኮኖሚ ድርጅት የአፍሪቃ ማህበር ገልጸዋል። የነዳጅ ዘይቱ ንጣፍ የተገኘበት ጊዜ አሁን መሆኑ ለጋና ጥሩ ዕድል ከፋች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ምክንያቱም የጋና መንግስት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን አሰራር የሚመለከት ህግ በማርቀቅ ላይ ይገኛል። ከዚሁ ገቢ መካከል አንዱ ከፊል ለአጠቃላዩ በጀት፡ የተቀረው ደግሞ ለትምህርት እና ለሀኪም ቤቶች፡ እንዲሁም፡ለመንገድ ግንባታ እንዲውል ታቅዷል። በገቢው ታዳሽ የኃይል ምንጮችን የማስፋፋት ዕቅድ አለ። ህጉ እስካሁን ገና ባለመጽደቁ፡ ካለፈው ታህሳስ ወዲህ የተመረተው የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ገቢ እንዴት ጥቅም ላይ በመዋል ላይ መሆኑ ለህዝቡ ገና ግልጽ እንዳልሆነለት በጋና መዲና አክራ የሚገኘው የኢማኒ ፖለቲካ ምርምር ማዕከል ተንታኝ ብራይት ሳይመንስ አስረድተዋል።

« ነዳጅ ዘይቱን ለማውጣት የሚያስፈልገው ወጪ ምን ያህል መሆኑን መንግስት እስካሁን ግልጽ አላደረገም። ይህም ምን ያህል ገቢ መገኘቱን ለመገመት አልቻልንም ማለት ነው። የሀገሪቱ መንግስት ህገወጥ ስራ እየሰራ ከሆነ፡ እኛ እንደ ጋና ሲቭል ማህበረሰብ የአቅጣጫ ለውጥ ለማነቃቃት በጣም የተወሰነ ችሎታ ነው ያለን። »

በጋና በአሁኑ ጊዜ ይህንን ሂደት በቅርብ መከታተል የሚችል ቢያንስ አንድ ሲቭል ማህበረሰብ መኖሩ መልካም ነው። ጋና ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ የጥሬ አላባ ንግድን ግልጽነት ለማበረታታት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ድርጅት አባል ናት። ከመንግስታት፡ ከተቋማት፡ ከሲቪል ማህበረሰብ እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋ ባንድነት ትሰራለች። የዚሁ ድርጅት አባል ለመሆን የጋና መንግስት ታማኝ ሆኖ ለመስራት፡ በመንግስትና በኢንዱስትሪው መካከል የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ በየጊዜው ይፋ ለማውጣት ዕቅድ እንዳለው ማረጋገጥ ነበረበት። ብራይት ሳይመንስ ርምጃውን ቢያሞግሱም ድርጅቱ በብዙ ቢሮክራሲ የታጠረ ሆኖ ያዩታል።

« ፕሬሱ በቀጥታ ግንኙነት እንዲኖረው ጠይቀናል። ኢንዱስትሪውን ስራ እንዴት በተሻለ መንገድ ልንረዳ የምንችልበት ሁኔታ በቂ ውይይት አልተደረገበትም። ለምሳሌ ሁሉም ጋናውያን ስለነዳጅ ዘይቱ ምርት መረጃ ሊያገኙበት የሚችሉ ድረ ገጽ ማውጣት እንችላለን። »

በጋና ባህር ጠረፍ አሁን መውጣት የጀመረው ነዳጅ ዘይት መጠን ንዑስ በመሆኑ በናይጀሪያ እንደታየው ዓይነት ሁከት ያስከትላል ብለው አያምኑም፤ ብራይት ሳይመንስ። ችግር ሊፈጠር የሚችለው የነዳጅ ዘይቱ ሽያጭ ገቢ በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ አንዳችም አዎንታዊ ተጽዕኖ ካላሳረፍ ይሆናል። እና ጋና ይህ አሁን የተገኘውን ዕድል ማሳለፍ አይኖርባትም።