«ጉዞ ዓድዋ» እና 120ኛዉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ | ባህል | DW | 26.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«ጉዞ ዓድዋ» እና 120ኛዉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ

በ 46 ቀናት ዉስጥ ዓድዋ ለመድረስ ጥር ዘጠኝ ቀን ከአዲስ አበባ የተነሱት የሦስተኛ የዓድዋ ተጓዦች ጥቂት ኪሎሜትር ቀርቶናል ሲሉ ነግረዉናል። የካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ታላቁ የዓድዋ ድል የ120ኛ ዓመት መታሰብያ ክብረ በዓል በታላቁ ንጉሰ ነገሥት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ረቡዕ ጠዋት ከ2፡30 ጀምሮ በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:44

120ኛዉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ

ወደ ዓድዋ ተጓዦችም ሆኑ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ቀኑን በልዩ ዝግጅት እንደሚያከብሩት እየተነገረ ነዉ። ወራሪው የጣልያን ጦር የዛሬ 79 ዓመት በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ በግፍ የፈጃቸው 30 ሺህ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸዉ ሲሉ ሰማዕትነትን የተቀበሉበት የካቲት 12ም በኢትዮጵያዉያን ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ ነዉ ታስቦ የዋለዉ። በእለቱ ዝግጅታችን ሦስተኛ ዙር የዓድዋ ተጓዦችን ይዘን 120ኛዉን የዓድዋን መታሰብያ ለማክበር የሚደረገዉ መሰናዶ እንቃኛለን ።
በጎርጎሪሳዊዉ አቆጣጠር 1896 ዓ,ም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ የጣልያን ጠላትን ጦር ከአገር ያባረሩበት 120ኛ ዓመት በመላዉ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ በድምቀት ይከበራል ይታሰባል። በተለይ አዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ከፍተኛ ዝግጅት እንደሚደረግ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገልጸዉልናል። ማኅበሩ በዝግጅቱ ላይ የአፍሪቃ ሃገራት ተወካዮችን እንዲሁም የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር እዲገኙ ጥሪ ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆኑም ተሰምቷል።


በፊልም ሥራዉ የሚታወቀዉ ወጣት ያሪድ ሹመቴ፤ የጉዞ ዓድዋ ዋና አስተባባሪ ነዉ። አንዲት ሴትን ጨምሮ በአጠቃላይ 12 ወጣቶችን ያካተተዉ የዘንድሮዉ ጉዞ አድዋ ቡድን ከአዲስ አበባ ዓድዋ በእግር በ 46 ቀናት ለመድረስ ነዉ የተንቀሳቀሰዉ።
ዘንድሮው ለሰባ ዘጠነኛ ጊዜ ታስቦ የዋለው የሰማዕታት ቀን ለሰማዕታቱ መታሰቢያ በቆመበት በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ሐውልትና በቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በፀሎተ-ፍትሃት ሥነ-ሥርዓት ተዘክሯል። ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ቀኑ በድምቀት ተከብሮ እንደዋለ ተናግረዋል።
«በትግራይ ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር፣
በጎንደር ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር፣
በሸዋ ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር፣
በጎጃም ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር፣
በሰማይ ላይ መጣ በማናውቀው አገር »
በወቅቱ ከወፍ በቀር በሰማይ የሚበር ነገር የማያውቀው ኢትዮያዊ የገጠመው ነዉ። የዓድዋን ሽንፈት ለመበቀል ጣልያኖች በአውሮፕላን እና በታንክ የመርዝ ጢስ ሰንቀው፣ ለቂም በቀል ድግስ መጡ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ‹‹በእንቢኝ ወኔ ›› ብቻ አመጣጡን ላላወቁት ጠላት በሕይወት ከመምበርከክ ሞተው መውደቅን መረጡ። ታድያ ይህ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን አፍሪቃዉያን ሁሉ የሚኮሩበት የትናንቱ ታሪካችን ለዛሪዉ መሰረት ነዉና መታሰብ ታሪኩ መነገር አለበት ሲል የጉዞ አድዋ ዋና አዘጋጅ ወጣት ያሪድ ሹመቴ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተናግረዋል። ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic