ጀርመን 2,3 ቢሊዮን ይሮ ለሶርያ ርዳት | ዓለም | DW | 05.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ጀርመን 2,3 ቢሊዮን ይሮ ለሶርያ ርዳት

በሶርያ የርስበርስ ጦርነት ሰበብ ችግር ላይ ለወደቁ ሶርያውያን ርዳታ የሚያሰባስብ ዓቢይ ጉባዔ በብሪታንያ መዲና ለንደን ተካሂዶአል።። በዚሁ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ከሰባ የሚበልጡ ሀገራት ርዕሳነ ብሔር፣ የተመድ ዋና ጸሐፊ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲሁም፣ የግል ዘርፍ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተሳታፊዎች ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:03 ደቂቃ

ርዳታ ለሶርያ

የሁለት ቀኑን የለንደን ጉባዔ በጋራ የሚያስተናግዱት ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ኖርዌይ፣ ኩዌት እና የተመድ ተሳታፊዎቹ ፣ከአምስት ዓመት የርስ በርስ ጦርነት በኋላ፣ በሀገር ውስጥ ለተፈናቀሉት 13,5 ሚልዮን፣ እንዲሁም፣ ወደ ጎረቤት ሀገራት ለተሰደዱት 4,4 ሚልዮን ሶርያውያን ዘጠኝ ቢልዮን ዶላር እንደሚሰጡ ተስፋ አድርገዋል። በተመድ ዘገባ መሰረት፣ ወደ 2,1 ሚልዮን የሚጠጉ ሶርያውያን ስደተኞች ወደ ምዕራቡ ዓለም ተሰደዋል።

ጀርመን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት 2,5 ዶላር ለሶርያ እና ለአካባቢው ርዳታ እንደምትሰጥ ፣ ከዚህም መካከል 1,4 ቢልዮን ዶላር ገደማው በዚህ ዓመት እንደሚሰጥ ደግሞ በለንደኑ ጉባዔ በይፋ ቃል የገባች ሲሆን፣ በጉባዔው የተሳተፉት ጀርመናዊው የልማት ትብብር ሚንስትር ጌርድ ሚውለር ለጋሽ ሀገራት ካሁን ቀደም ለመስጠት የገቡትን ቃል አለመጠበቃቸውን በጥብቅ ተችተዋል።

Bundesentwicklungsminister Gerd Müller CSU

ሚንስትር ጌርድ ሚውለር

« ለጋሽ ሀገራት ለሶርያ ጠንካራ የገንዘብ ርዳታ ለመስጠት ቃል የሚገቡት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የሶርያው ጉባዔ ፣ ለስደተኞቹ ችግር፣ በዚያው በሀገሪቱ መፍትሔ ሊገኝለት እንደሚችል ግልጹን መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆን ይገባዋል። ችግሩ አውሮጳን ብቻ የሚነካ አይደለም። በመጀመሪያ፣ የሕዝቡ ደህንነት መረጋገጥ ይኖርበታል። ቀጥሎም፣ የወደፊት እጣ ፈንታቸው አስተማማኝ መሆን አለበት። አስር ቢልዮን ዶላር ርዳታ ቢገኝ፣ ቀውስ ፈጥኖ የሚነካቸው ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ ቱርክ፣ እንዲሁም ሰሜን ኢራቅን ለማረጋጋት እንችላለን። እና ጉባዔው ለሶርያውያኑ አስተማማኝ ሁኔታ እንደምንፈጥርላቸው በማጉላት ፣ ሶርያውያኑ በዚያው ባካባቢያቸው እንዲቆዩ የሚለውን ግልጹን ምልክት ማስተላለፍ ይኖርበታል። »

ብሪታንያም ቢያንስ 1,7 ቢልዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ብትገባም፣ የአሁኑ ጉባዔ ገንዘብ በማሰባሰቡ ተግባር ላይ ብቻ አለማትኮሩን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካምረን ገልጸዋል። የተመድ የአስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት፣ በምህፃሩ የ«ኦቻ» ቃል አቀባይ የንስ ሌርከም፣ የምግቡ፣ መድሀኒት እና መጠለያ ለማቅረብ ከሚያስፈልገው የገንዘብ ርዳታ ጎን ከለጋሾች ዘላቂ ትብብር እንደሚሹ አመልክተዋል።


« እጎአ ከ2013 ዓም ወዲህ በተካሄዱት እና ኩዌት ባስተናገደቻቸው ሶስት ጉባዔዎች እንዳደረግነው ሁሉ፣ ለሶርያ እና ለጎረቤት ሀገራት ለሰብዓዊ ርዳታገንዘብ ለማግኘት እንሞክራለን። ግን፣ አሁን የሶርያውያኑን ስደተኞች የወደፊት እጣ ለማሻሻል ለሕፃናቱ ትምህርት በመስጠቱ እና ለአካለ መጠን ለደረሱት ደግሞ የስራ ቦታ በመፍጠሩ ዘርፎች ላይ ከለጋሾች ዘላቂ ትብብር እንሻለን። በተለይ፣ የስራ ቦታ የመፍጠሩ ሂደት ሶርያውያኑን ስደተኞቹን ብቻ ሳይሆን የአስተናጋጆቻቸውን ሀገራት ዜጎችም የሚጠቅም ነው። ለምሳሌ፣ በስደተኞች ብዛት የተጨናነቁትን ግዙፍ ችግር ያጋጠማቸውን ሀገራት መሰረተ ልማት ለማሻሻል ይህን ዓይነቱን ትብብር በማፈላለግ ላይ ነን። »
ኖርዌይ በሚቀጥሉት አራት ሀገራት 1,1 ቢልዮን ዶላር፣ የአውሮጳ ህብረት 3,36 ቢልዮን ዶላር ፣ ዩኤስ አሜሪካ ደግሞ 925 ሚልዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ዩኤስ አሜሪካ ከምትሰጠው ገንዘብ መካከል 600 ሚልዮን ዶላሩ ለምግብ እና መጠለያ፣ የተቀረው ደግሞ በዮርዳኖስ እና ሊባኖስ ለሚገኙት ወደ 300,000 ሶርያውያን ስደተኞች ትምህርት ለመስጫ እንደሚውል ገልጾዋል።

ቬዝል ባርባራ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic