ጀርመን ከምርጫ በኋላ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመን ከምርጫ በኋላ

ጀርመናውያን የምክር ቤት ተወካዮቻቸውን ትላንት መርጠዋል፡፡ የምርጫው ውጤት የጀርመንን የፖለቲካ ምህዳር ለውጦታል፡፡ ለመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም ቢሆን መጥፎ ዜና ነበር፡፡ የእርሳቸው የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት እና የጥምር መንግስታቸው አባል የነበረው የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ በምክር ቤት የነበራቸውን በርካታ ወንበሮች አጥተዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:01
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:01 ደቂቃ

ሜርክል መጪው አራት ዓመት ከባድ ይሆናል ብለዋል

የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ትላንት አመሻሹ ላይ ከፓርቲያቸው የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ህብረት ዋና ጽህፈት ሲደርሱ በፊታቸው ላይ የቆራጥነት ስሜት ይነበብ ነበር፡፡ እምብዛም ሳይቆይ ይፋ የተደረገው የመጀመሪያ ዙር የምርጫ ውጤት ግን ፓርቲያቸውን ሽንፈትን ያከናነበ ነበር፡፡ በእርግጥ ፓርቲያቸው 32.9 ከመቶ ድምጽ አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ይህ የዛሬ አራት ዓመት ከተካሄደው ምርጫ ጋር ሲነፃፀር በዘጠኝ ከመቶ ያነሰ ነው፡፡ ሜርክል የምርጫውን ውጤት ተከትሎ  ባደረጉት ንግግር ቀጣዩን መንግስት ለመምራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ቢያሳውቁም፣ በስልጣን ላይ የሚቆዩበት መጪው አራት ዓመት ከባድ እንደሚሆን አልሸሸጉም፡፡   

“አስራ ሁለት ዓመታትን በስልጣን ከቆየን በኋላ እንደገና ቀዳሚ መሆናችን ያልተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ከፊታችን ትልቅ ተግዳሮት ተደቅኖብናል፡፡ AFD ወደ ምክር ቤት ገብቷል፡፡ ለAFD ድምጻቸውን የሰጡ መራጮች የሚያሳስባቸውን ጉዳይ ከምር በመውሰድ እና ሀገሪቱን በሚገባ በመምራት እነዚህን መራጮች እንደገና ወደ እኛ ለመመለስ እንፈልጋለን” ብለዋል ሜርክል፡፡ 

በርካታ መራጮች ለክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት ጀርባቸውን የሰጡት ሜርክልን በተከተሉት ለዘብተኛ የስደተኞች ፖሊሲ ሊቀጣቸው ስለፈለጉ ነው፡፡ ARD በተባለው አንዱ ዋነኛ የጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት እንዳመለከተው ወደ አንድ ሚሊዩን የሚጠጉ ቀደም ሲል ለክርስቲያን ዲሞክራቶቹ ድምጻቸው ይሰጡ የነበሩ መራጮች አሁን ወደ ቀኝ አክራሪው AFD ተገልብጠዋል፡፡ በጀርመን ያሉ የውጭ ዜጎችን ለመቀነስ ተግቶ ሲቀሰቅስ የነበረው መጤ ጠሉ ፓርቲ ከአጠቃላዩ ድምጽ 13 ከመቶውን አግኝቷል፡፡ የፓርቲው ዋነኛ ዕጩ አሌክዛንደር ጋውላንድ “በምክር ቤት ውስጥ ሶስተኛው ጠንካራ ፓርቲ እንሆናለን፡፡ ቀጣዩ መንግስት በደንብ ተዘጋጅቶ መጠበቅ አለበት፡፡ ወይዘሮ ሜርክልንም ሆነ ማንኛውንም ከመታገል አንመለስም፡፡ ሀገራችን እናስመልሳለን” ብለዋል፡፡  

በእርግጥም ከዚህ በኋላ ነገሮች  ለመራሂተ መንግስት ሜርክል ቀላል አይሆኑም፡፡ አሁን ባለው ጥምር መንግስት አጋራቸው የነበረውን የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ አጥተዋል፡፡ ሶሻል ዲሞክራቶቹ በዚህ ምርጫ በታሪካቸው አስመዘግበውት የማያውቁትን 20.5 በመቶ ዝቅተኛ ውጤት አግኝተዋል፡፡ የፓርቲው መሪ ማርቲን ሹልስ ለARD እንደተናገሩት ፓርቲያቸው የጥምር መንግስቱን አይቀላቀልም፡፡ ይልቁንም ተቃዋሚ ሆኖ ለመቀጠል ወስኗል፡፡ “በዚህ ጊዜ የሚያስፈልገን ጠንካራ ተቃዋሚ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ለAFD ልንተውለት አንችልም፡፡ በዚህ ሀገር በጣሙኑ የሚያስፈልጉትን ውይይቶች የመፍጠሩ ስራ የእኛ ነው የሚሆነው” ሲሉ ሹልስ የወደፊት አካሄዳቸውን አሳውቀዋል፡

የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ በጥምሩ መንግሥት ላለመሳተፍ የወሰደው ውሳኔ ሜርክልን አንድ አማራጭ ብቻ ነው የተወላቸው። ይኸውም ከአከባቢ ተቆርቋሪዎቹ የአረንጓዴ ፓርቲ እና የንግድ መስፋፋት ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP ፓርቲ ጋር ጥምር መንግስታቸውን ለመመስረት መሞከር ይሆናል። ነገር ግን እንዲህ አይነት ጥምረት  በብሔራዊ ደረጃ ተሞክሮ አያውቅም፡፡ ከዚህ ባሻገር ሶስቱ ፓርቲዎች በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ልዩነቶቹ ከሚመዘዙባቸው ጉዳዮች መካከል ግብር፣ የአካባቢያዊ ፖሊሲ እና የስደተኞች ጉዳይ ይገኙበታል፡፡ በፓርቲዎቹ መካከል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን የመከፋፈል ስራም ቢሆን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ጁዲ ዴምፕሲ ካርኔጄ የጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው፡፡ 

“መራሂተ መንግስት ሜርክል አረንጓዴዎቹን እና ነጻ ዴሞክራቶቹን ወደ መንግስት በማምጣት ለጀርመን ፖለቲካዊ መረጋጋት ማምጣት እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ በሶስት ፓርቲዎቹ መካከል የሚፈጠረውን ውስጣዊ ሽኩቻ ማሰብ ትችላለህ፡፡ ማነው የገንዘብ ሚኒስቴርን የሚወስደው? የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትንስ ማን ይረከባል? ወጣም ወረደ ሶስቱም ፓርቲዎች ስልጣን ይፈልጋሉ” ይላሉ ጁዲ፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም ሶስቱ ፓርቲዎች ጥምረት ለመመስረት ከመወሰናቸው በፊት ወራት ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ከተጠናቀቀ ሜርክል በድጋሚ መራሂተ መንግስት ሆነው በምክር ቤቱ ይመረጣሉ፡፡ ቀጣዩ አካሄድ ምን ይሁን? በሚለው ላይ ለመወያየት የሁሉም ዋና ዋና ፓርቲዎች ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ዛሬ በበርሊን ተስበስበዋል፡፡     

 

ዳንኤል ፔልስ/ ተስፋለም ወልደየስ 

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች