ድርቅና የምግብ ዋስትና | ጤና እና አካባቢ | DW | 27.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ድርቅና የምግብ ዋስትና

የአንድ አገር የምግብ ዋስትና የሚረጋገጠዉ አገሪቱ የተፈጥሮ ሃብቷን በግባቡ በምትይዝበት ስልት ላይ ይወሰናል።

default

ባለሙያዎች እንደሚሉት በየደረጃዉ የሚደረጉ የግብርና ምርምሮች እና ተቀባይነት ያገኙ ዉጤቶች ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርሱት ቢደረግ በየአገራቱ የሚገኙ ህይወታቸዉ ከግብርና ጋ የተገናኘ ወገኖች ለርሃብና ለከፋ አደጋ የመጋለጣቸዉን አጋጣሚ መቀነስ ይቻላል። በአንፃሩ አሁን የተጀመረዉ የሃብታም አገራት በድሃ አገራት ለእርሻ ተስማሚ መሬቶችን መግዛትና ለህዝባቸዉ የሚሆን ሰብል ማምረት ሌላዉ አቅማቸዉ አነስተኛ የሆነ አርሶአደሮችን ህይወት ለችግር እየዳረገ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። የምግብ ዋስትና ያላረጋገጡ ሃብታም አገራትና ባለሃብቶች ህዝባቸዉን ለመመገብ በአንዳንድ በድሃ አገራት መሬት ገዝተዉ ማምረት መጀመራቸዉ እየተለመደ መምጣቱን መቀመጫዉን ሳንፍራንሲስኮ ያደረገዉ የኦክላንድ ተቋም ያቀረበዉ አዲስ ጥናት በትችት አጅቦ ይፋ አዉጥቶታል። በዓለም የምግብ እጥረት ቀዉስ መፈጠሩን ተከትሎ ከየድሃ አገራቱ መሬት ለመግዛት የተደረገዉ መሯሯጥ ወደ1,5ቢሊዮን የሚደርሱ ዝቅተኛ አርሶ አደሮችን ኑሮ ማናጋቱን ታላቁ የመሬት ቅርምት በሚል ርዕስ የወጣዉ ጥናት ጨምሮ ገልጿል። እንደሳዉዲ አረቢያ፤ ኩዌት፤ ደቡብ ኮርያ፤ ቻይናና የተባበሩ አረብ ኤሜሬትን የመሳሰሉ አገራት ቱጃሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ፤ በሱዳን፤ ፓኪስታን፤ ማዳጋስካር፤ ካምቦዲያ እና ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ እህል የሚያመርቱባቸዉን መሬቶች እንደገዙ አለያም በድርድር ላይ መሆናቸዉ ተመልክቷል። ጥናቱ እንደሚለዉ ከ2006ዓ,ም አንስቶ እስከያዝነዉ የአዉሮጳዉያኑ ዓመት ድረስ ከ37እስከ 49ሚሊዮን ኤከር የእርሻ መሬት ለባለሃብቶች ተሰጥቷል አለያም ለድርድር ቀርቧል።

ሸዋዬ ለገሠ/አርያም ተክሌ