1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዜና | 31.08.2015 | 17:36

አዲስ አበባ፤የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ጥያቄ ውስጥ ነው

የደቡብ ሱዳን መንግስት በአማጽያን ይዞታዎች ላይ የሚፈጽመው ጥቃት በተፋላሚ ኃይላቱ የተፈረመውን ስምምነት ውድቀት ላይ የሚጥል ነው ተባለ።

የደቡብ ሱዳን የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንትና የአሁኑ የአማጽያን መሪ ሪየክ ማቻር መንግስት የተፈረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት ባለማክበሩ ስጋት እንዳላቸው በአዲስ አበባ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት ከእሁድ ጀምሮ ገቢራዊ የሚሆን የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመው የነበረ ቢሆንም በአፐር ናይልና ዩኒቲ ግዛቶች ስምምነቱ መጣሱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። የተፈረመውን ስምምነት በመጣስ የመንግስት ወታደሮች ጥቃት እየፈጸሙብን ነው በማለት የከሰሱት ሪየክ ማቻር የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ወታደሮቻቸውን እንዲቆጣጠሩ ጥሪ አቅርበዋል። የደቡብ ሱዳን ጦር በበኩሉ የተኩስ አቁሙን ስምምነት የጣሱት የሪየክ ማቻር ወታደሮች ናቸው ሲል ይከሳል።

ናይሮቢ፤ ሶማሊያ የረሐብ ስጋት

በሶማሊያ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ መጨመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ። «የምግብ እጦትና የተመጣጠነ ምግብ ጉድለቱ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል።» ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶማሊያ ልዑክ ዋና ሃላፊ ፒተር ደ ክለርክ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶችና ለጋሾች ከዚህ የከፋ እንዳይሆን ተከላክለዋል።» ብለዋል።

የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከቀደሙት ስድስት ወራት በ17 በመቶ ጨምሯል ተብሏል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ደህንነትና የተመጣጠነ ምግብ ክትትል ቡድን ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት 730 ሺህ የነበረው የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 855 ሺህ አሻቅቧል።

በዝናብ እጥረት ምክንያት የተስተጓጎለው ዓመታዊ ምርት እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 215 ሺህ ህጻናት ላይ የምግብ እጥረት ሲያስከትል ከእነዚህ መካከል ወደ 40 ሺህ የሚደርሱት በሽታና ሞት ያሰጋቸዋል ተብሏል።

በአገር ውስጥ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሶማሊያውያን እጣ ፈንታ አሳሳቢ ነው ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባዎቹ ሁኔታው አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማሉ ብሏል።

     

ሌጎስ፤ቦኮ ሐራም በናይጄሪያ እየተስፋፋ ነው

የናይጄሪያ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሐራም በተለያዩ ግዛቶች መረቡን እየዘረጋ መሆኑን የአገሪቱ የደህንነት ባለስልጣን አስታወቀ። የናይጄሪያ የደህንነት ቢሮ ይህን ያስታወቀው የአሸባሪው ታጣቂ ቡድን አባል ናቸው ያላቸውን 20 ሰዎች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ነው።

ስምንት ወራት በወሰደው አሰሳ ከታጣቂ ቡድኑ መሪ አቡባካር ሼካው ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም የተባለውና በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ የተከሰቱ ፍንዳታዎችን በማቀነባበር የተጠረጠረው ዑስማን ሹዓይቡ የተባለ ግለሰብ ይገኝበታል ተብሏል። አህመድ መሐመድ የተባለ የታጣቂ ቡድኑ የቦምብ ባለሙያም በቁጥጥር ስር መዋሉን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የአገሪቱ ደህንነት በአካሄደው አሰሳ የሌጎስ ከተማን ጨምሮ በጎምቤና ካኖ ግዛቶች የታጣቂ ቡድኑ ህዋሶች መገኘታቸውን አስታውቋል።

በናይጄሪያ በጥብቅ እስላማዊ ህግጋት የሚመራ አገር የመመስረት እቅድ እንዳለው የሚነገርለት የቦኮ ሐራም ታጣቂ ቡድን ከጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በፈጸማቸው የሰርጎገብ ጥቃቶች ከ14,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በሳዑዲ አረቢያ ሴቶች በምርጫ ሊሳተፉ ነው

በሳዑዲ አረቢያ አካባቢያዊ ምርጫ ሴቶች በእጩነትና ድምፅ በመስጠት ሊሳተፉ ነው። ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ እንስቶች ከሶስት ወራት በኋላ ለሚካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ በእጩነት ለመመዝገብ ፈቃደኝነታቸውን ማሳየታቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የቀድሞው የሳዑዲ አረቢያ መሪ ንጉስ አብደላ ሴቶች በመራጭነትም ይሁን በእጩነት እንዲሳተፉ የፈቀዱት ከአራት አመታት በፊት ነበር።

እንስቶች መኪና ማሽከርከር በማይችሉባት ሳዑዲ አረቢያ ለእጩነት መመዝገባቸውና በአገራዊ ምርጫ ተሳትፎ ማድረጋቸው በዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት አግኝቷል። ወግ-አጥባቂ በምትባለው ሳዑዲ አረቢያ መኪና ማሽከርከር ለሴቶች የተከለከለ ሲሆን ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር፤ለመስራት፤የጉዞ ሰነድ ወይም ፓስፖርት ለመያዝና ትዳር ለመመስረት የወንዶችን ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

በርሊን፤ የስደተኞች ቀውስ ለአውሮጳ ህብረት ፈተና ነው ተባለ

የጀርመኗ መራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ወቅታዊው የስደተኞች ቀውስ የሰብዓዊ መብት መሰረታዊ ፅንሰ-ሐሳቦችና የአውሮጳ ሕብረትን አንድነት እየተፈታተነ ነው ሲሉ ተናገሩ። «ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መርህ ከአውሮጳና የውህደት ታሪኳ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።» ያሉት መራሒተ-መንግስት አንጌላ መርክል አሁን የተከሰተው የስደተኞች ቀውስ ግን ፈተና ሆኗል ብለዋል። «አውሮጳ በስደተኞች ጉዳይ ላይ የተነሳውን ጥያቄ መመለስ ከተሳናት፤ከሰብዓዊ መብት ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝትም ከተሰበረ አውሮጳ የምንፈልጋት አውሮጳ አትሆንም።» በማለት አባል አገራት ተገን ጠያቂዎችን በፍትሃዊነት እንዲቀበሉ ወትውተዋል።

ጀርመን በዚህ ዓመት ብቻ 800,000 ስደተኞችን ትቀበላለች ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት ወደ አገሪቱ ከገቡት ስደተኞች ቁጥር በአራት እጥፍ የሚልቅ ሲሆን የትኛውም የአውሮጳ ሕብረት አባል አገር ከተቀበለው ይበልጣል። «የሌሎች ሰዎችን ክብር ለሚነኩ ትዕግስት የለንም ።» ያሉት መራሒተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ሁሉ ሕግ በሙሉ ጉልበቱ ተግባራዊ ይደረግባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። 

ኬየቭ፤በፖሊስና ተቃዋሚዎች ግጭት ሞትና ጉዳት ደረሰ

በዩክሬን ዋና ከተማ በፖሊስና ተቃዋሚዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት አንድ ሰው ሲሞት 100 የሚደርሱ የጸጥታ አስከባሪዎች ቆሰሉ። የ25 አመቱ የዩክሬን ብሄራዊ ዘብ አባል ከተቃዋሚዎች በተተኮሰ ጥይት ደረቱ ላይ ከተመታ በኋላ በቀዶ ጥገና ጠረጴዛ ላይ ህይወቱ ማለፉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ግጭቱ የተቀሰቀሰው የአገሪቱ ምክር ቤት በምስራቅ ለሚገኙ የመገንጠል አቀንቃኞች ከፍ ያለ ድምፅ ለመስጠት የቀረበውን ሃሳብ ተከትሎ ነው።

የአገሪቱ ብሄራዊ ዘብ ቃል አቀባይ ስቪትላና ፓቭሎቭስካ ተቃዋሚዎች ተቀጣጣይ ነገሮችን በጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ከመወርወራቸው ተጨማሪ ሽጉጦችን መጠቀማቸውን ተናግረዋል። የምክር ቤቱን ሃሳብ በመቃወም አደባባይ የወጡት የአንድነት አቀንቃኝ የሆኑ 100 አካባቢ የሚጠጉ የስቮቦዳ ፓርቲ አባላት ናቸው ተብሏል። ለምስራቅ ተገንጣይ ቡድኖች ከፍ ያለ ድምጽ የሚሰጠው ሃሳብ ከ450 በላይ የምክር ቤት አባላት መካከል የ265ቱን የመጀመሪያ ድጋፍ አግኝቷል ተብሏል። የውሳኔ ሃሳቡ የዩክሬንን ግጭት ለማስቆም ከሰባት ወራት በፊት የተፈረመው የስልጣን ክፍፍል ስምምነት አካል ነው።

EB / AT