ያልተቋጨዉ የአዉሮጳ የስደተኞች ጉዳይ ዉዝግብ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 17.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ያልተቋጨዉ የአዉሮጳ የስደተኞች ጉዳይ ዉዝግብ

በአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት መካከል በስደተኞች ምክንያት የተነሳዉ ዉዝግብ መቋጫ አጥቷል። የኅብረቱ አባል ሃገራት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ነገሩን እያነሱ ቢጥሉም አግባቢ ከሚባል ነጥብ ላይ መድረስ አልቻሉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:57

የአዉሮጳ የስደተኞች ጉዳይ ዉዝግብ

በአሁኑ ወቅት አዉሮጳ ዉስጥ የበረከቱትን ስደተኞች በሚመለከት ጀርመን ብዙም ደጋፊ ሀገር አላገኘችም። የስደተኞቹ ጉዳይ ከኅብረቱ ሃገራት ጋር በጉዳዩ ላይ ለሚሟገቱት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ላይ የተጣለ መስሏል።

ሁሉን የሚያግባባ መፍትሄ ማምጣቱ ስላልተቻለ ይመስላል የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብራስልስ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ የስደተኞች ቀዉስ በመነጋገሪያ ነጥብነት አልተያዘም ነበር። እንዲያም ሆኖ ግን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በዚህ አጣዳፊ ጉዳይ ናይ ተነጋግረዋል። ከስምምነት ላይ ባይደርሱም። የተነጋገሮባቸዉ ነጥቦችም የፊታችን ሐሙስ እና ዓርብ ለሚካሄደዉ የመንግሥታት እና የሃገራት መሪዎች ጉባኤ በይደር ተቀምጠዋል። የኅብረቱ ኮሚሽን ያቀረበዉ ስደተኞች ግሪክ ላይ እየተመዘገቡ ወደተለያዩ የኅብረቱ አባል ሃገራት በኮታ ይከፋፈሉ የሚለዉ ሃሳብ፤ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም በሃገራቱ ተቀባይነት አላገኘም። ጣሊያን እና ግሪክ ዉስጥ ወደተለያዩ ሃገራት ይከፋፈላሉ ተብሎ ከተመዘገቡት 160,000 ጥገኝነት ፈላጊዎች መካከል 500ዎቹ ብቻ ናቸዉ ወደሌላ ሀገር የተሻገሩት። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም የግሪክ እና ቱርክ ድንበር ለሕገወጥ ስደተኞች እንዲዘጋ እና ጥገኝነት ፈላጊዎች በቀጥታ ከቱርክ ማቆያ ጣቢያዎች ወደአዉሮጳ ኅብረት ሃገራት እንዲሻገሩ ይደረግ የሚለዉ እቅድም እጅግም ድጋፍ አላገኘም። ሌላዉ ቀርቶ የቅርብ አጋሯ ፈረንሳይ እንኳ ይህን መከተል አልፈለገችም። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፍራንክ ቫልተር ሽታይነር ከምንም በላይ የምሥራቅ አዉሮጳ አካል የሆኑ የኅብረቱ አባል ሃገራት እና የኦስትሪያን ከግሪክ እና ሜቄዶንያ ጋር የሚያገናኛቸዉን የድንበር አካባቢ የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ሲባል የማጠር ሃሳብ እና ርምጃን አጥብቀዉ ተችተዋል።

«የአዉሮጳ ኅብረት አባል የሆነችዉ ግሪክ የአዉሮጳ የዉጭ ድንበር እንደሌላት ብጤ እንዲህ ያለዉን ቀላል መፍትሄ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሞክር ሁሉ ርምጃዉ የትም አያደርሰዉም። በይፋም ሆነ በሌላ መንገድ የአዉሮጳ ኅብረትን ድንበር እንደአዲስ መገንባት አንችልም። ግሪክ አንድ አባል ሀገር ናት። ስለዚህም የግሪክን የዉጭ ድንበር በምንችለዉ ሁሉ የመከላከል ግዴታ አለብን።»

እንዲያም ሆኖ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ቫልስ ኮታ የሚለዉን ሀገራቸዉ እንደማትቀበል ነዉ የገለፁት። አዲሱ የፈረንሳይ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን- ማርክ አይሩል ከኅብረቱ አባል ሃገራት አቻዎቻቸዉ ጋር ብራስልስ ላይ ሲገናኙ የጀርመን እና ፈረንሳይ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ነዉ በዲፕሎማሲ መንገድ የገለፁት። የፓሪስ በርሊንን ግንኙነት በማጠናከርም ሌሎች ተጓዳኞችም የሚስማሙበት ሃሳብ በጋራ ሊያቀርቡ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። ሜርክል በበኩላቸዉ ያቀረቡት ሃሳብ ምን ያህል ረድቷል የሚለዉ በመጪዉ የመሪዎቹ ጉባኤ ትኩረት እንዲያገኝ ይሻሉ።ከነገ በስተያ ሐሙስ በሚካሄደዉ ጉባኤ ላይም የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመት ዳቮቱጉሉ ይገኛሉ። የአዉሮጳ ኅብረት በተለይም ከቱርክ ጋር የሚያገናኘዉ የድንበር አካባቢ በአግባቡ አስተማማኝ ጥበቃ ይደረግለት እንደሆነ ማረጋገጥ ይፈልጋል። በሕገወጥመንገድ ሰዉ የሚያሸጋግሩትን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻልም ይመክራል። የግሪክ ባለስልጣናት ከሳምንታት መዘግየት በኋላ በአጊያን ባህር ዳርቻ ላይ ሶስት አዲስ የስደተኞች መመዝገቢያ ጣቢያ እንደሚከፈት ይፋ አድርገዋል። በተቃራኒዉ አቴንስ በኅብረቱ አባልነቷ የሚጠበቅባትን አላደረገችም በማለት አጥብቀዉ የተቹት የስሎቫኪያ ባለስልጣን ግሪክ ከነአካቴዉ ከሸንገን ስምምነት አባልነት እንድትወጣ ጠይቀዋል።

በአንድ ወገን የአዉሮጳ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብራስልስ ላይ በዚህ ጉዳይ ሲነጋገሩ ፕራግ ላይ ደግሞ የፖላንድ፤ ቼክ ሪፑብሊክ፤ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ተወካዮች የባልካን አካባቢን ከስደተኞች መሸጋገሪያነት ለመጠበቅ ስለሚያጥሩት አጥር መክረዋል። በሃንጋሪዋ ቪስጋርድ ከተማ የተሰየመዉ የሃገራቱ ስብስብ ስደተኞችን በኮታ መቀበል የሚለዉን በማጣጣል በሰርቢያ የዉጭ ድንበር ላይ ለሚገነባዉ አጥር ከኅብረቱ የሚጠብቀዉ የገንዘብ ድጋፍ አሳስቦታል።

ምንም ዓይነት ስደተኛ የማይቀበሉት የምሥራቅ አዉሮጳ ሃገራት በዚህ ጉዳይ ላይ ኅብረቱን የሚሞግቱ ከሆነ ለአንድነቱ አደጋ ነዉ ይላሉ የሉክዘንበርግ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን አሰልቦርን፤

«በዚህ ጉዳይ ክርክር ዉስጥ ከገባን አደገኛ ነዉ የሚሆነዉ፤ ያ ደግሞ እንዲህ ባስጠኳይ ላይመጣ ይችላል፤ በአንድ ደረጃ ላይ ግን ፈጥኖ መከሰቱ አይቀርም። ሁሉም ከብራስልስ ትብብር ይጠቀማል፤ በአፀፋዉ ምላሽ መስጠትም ይኖርበታል። አለበለዚያ ሥርዓቱ በዚህ መልኩ ሊሠራ አይችልም።»

ለስሎቬኪያዊዉ የአዉሮጳ ኅብረት ምክር ቤት አባል ሪቻርድ ሱልክ ግን የአዉሮፓ ኅብረት የትብብር መድረክ ሳይሆን በዉል የታሠረ ስምምነት ዉጤት ነዉ። እንደእሳቸዉ በስደተኞች መበራከት የተፈጠረዉን ቀዉስ በገንዘብ መፍታት ፈፅሞ አይቻልም።

«የአዉሮጳ ኅብረት እቃዎች፤ አገልግሎቶች እና ሰዎች እንዲሁም ገንዘብ በነፃ መንቀሳቀስ መቻላቸዉን መሠረት ባደረገ ሃሳብ ላይ ነዉ የተገነባዉ። ይህ መጠበቅ ይኖርበታል። ኅብረቱ ዉስጥ ያሉት ሰዎች ጀርመንን ጨምሮ ሁሉንም ነገር በገንዘብ መፍትሄ መስጠት ይቻላል ብለዉ ማሰብ የለባቸዉም። የስደተኞች ጉዳይ በገንዘብ መፍትሄ ሊያገኝ አይችልም።»

በርን ሪገርት/ ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic