ዩኤስ አሜሪካ እና የፀረ ወባው ዘመቻ ርዳታዋ ለአፍሪቃ | የጋዜጦች አምድ | DW | 10.07.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ዩኤስ አሜሪካ እና የፀረ ወባው ዘመቻ ርዳታዋ ለአፍሪቃ

ዩኤስ አሜሪካ ለድሆቹ የዓለም አካባቢዎች የምትሰጠውን ዓመታዊ ርዳታ እአአ እስከ 2010 ዓም ድረስ በእጥፍ ለመጨመር፡ እንዲሁም፡ በዓለም በወባ የሚሞተውን ሕዝብ አሀዝ ለመቀነስና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የሚከታተሉ ሕፃናትን፡ በተለይም የሴቶቹን ቁጥር በጉልህ ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጅርጅ ዳብልዩ ቡሽ ባለፈው ወር አስታውቀዋል።

በዚሁ የዩኤስ ዕቅድ መሠረት፡ አንድ ነጥብ ሁለት ቢልዮን ዶላር ለፀረ ወባ ዘመቻው፡ አራት መቶ ሚልዮን ዶላር ደግሞ ተጨማሪ ሕፃናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መከታተል ለሚችሉበት ዕድል ይመደባል። ወባን ለመታገል የተነቃቃው ጥረት በተለይ ችግሩ አብዝቶ በሚታይባቸው አሥራ አምስት የዓለም ሀገሮች ውስጥ ለሚኖር አንድ መቶ ሰባ አምስት ሚልዮን ሕዝብ የመርዳት፡ በወባ የሚሞተውን ሕዝብ ቁጥርም በግማሽ የመቀነስና በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ሕይወትን የማትረፍ ዓላማ አለው።
ፕሬዚደንት ቡሽ ባነቃቁት ፀረ ወባ ዘመቻ ርዳታ በመጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆኑት ሀገሮች ታንዛንያ፡ ዩጋንዳና አንጎላ ናቸው፤ እአአ በ 2007 ዓም ሌሎች አራት ሀገሮች፡ እአአ በ 2008 ዓም ደግሞ ተጨማሪ አምስት ሀገሮች በዚሁ ርዳታ እንደሚጠቃለሉ በመግለፅ፡ የበለፀጉ ሀገሮችና የግል ድርጅቶች በዚሁ ጥረታቸው እንዲተባበሩዋቸው ቡሽ ተማፅነዋል።አሜሪካዊው የማይክሮሶፍት የኮምፒውተር ባለተቋም ቢል ጌትስና ባልተቤታቸው ሜሊንዳ ጌትስ ያቋቋሙት የግል ድርጅት አፍሪቃ ውስጥ ለፀረ ወባው ዘመቻው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ብዙ ዓመታት ሆኖዋቸዋል። ይኸው ድርጅት በዛምቢያ በወባ የሚሞተውን ሕዝብ ቁጥር በሰባ ከመቶ ለመቀነስ ዕቅድ ማውጣቱን ከጥቂት ጊዜ ማስታወቁ አይዘነጋም።
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ከጥቂት ሣምንታት በፊት ዋሽንግተንን በጎበኙበት ጊዜ ከሰሃራ በስተደቡብ ላሉ አፍሪቃውያት ሀገሮች የሚሰጠው ርዳታ በጉልህ ከፍ እንዲል ያቀረቡትን ሀሳብ አስተናጋጃቸው ቡሽ ውድቅ ካደረጉና በዚህም የተነሣ ብርቱ ግፊት ከተፈራረቀባቸው በኋላ ነበር አሜሪካዊው ፕሬዚደንት ከላይ የተጠቀሰውን ርዳታ ለመስጠት ቃል የገቡት። በብሌር ሀሳብ ፈንታ ቡሽ ሀገራቸው ለውጭ ርዳታ መድባው ከነበረው ገንዘብ መካከል ጥቅም ላይ ሳይውል የተረፈውን ስድስት መቶ ሚልዮን ዶላር በአፍሪቃ ለተጀመሩ የርዳታ ፕሮዤዎች በዚህ ዓመት እንዲሰጥ አዘዋል። ይህን ይፋ ካደረጉ ከአንድ ሣምንት በኋላም የሀገራቸው የግንዘብ ሚንስቴር ሰባቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሀገሮችና ሩስያ የሚጠቃለሉበት ቡድን ስምንት ግዙፍ የውጭ ዕዳ ለተሸከሙ አሥራ ስምንት የዓለም ሀገሮች ይህንኑ ዕዳቸውን እአሰረዝ ያቀረበውን ዕቅድ ለመደገፍ መስማማቱን አመልከት። ከአሥራ ስምንቱ ሀገሮች መካከል አሥራ አራቱ አፍሪቃውያት ሀገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ፡ ፕሬዚደንት ጆርጅ ዳብልዩ ቡሽ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን እንዲመረጡ የረዱዋቸው ብዙዎቹ የሀገራቸው መንግሥታዊ ይልሆኑ ድርጅቶችና በርካታ ጥቁር አሜሪካውያን ቀሳውስት ይኸው የቡሽ ርምጃ በቂ እንዳልሆነ በማመልከት፡ የሀገራቸው መንግሥት በተለይ ለአፍሪቃ የሚሰጠውን ርዳታ በጉልህ እንዲጨምር ጠይቀዋል።
ቡሽ ለፀረ ወባና ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መከታተያ ለመስጠት ካሰሙት ርዳታ ጎንም፡ የሀገራቸው ምክር ቤት በአራት የአፍሪቃ ሀገሮች ያሉ ሴቶችን ሁኔታ ለማሻሻል የሚረዳ እና በሦስት ዓመት የሚሰጥ ሀምሳ አምስት ሚልዮን ዶላር እንዲመድብ ለመጠየቅ ሀሳብ እንዳላቸው በተጨማሪ አስታውቀዋል። ቡሽ የዚሁ ሀሳባቸው ተጠቃሚዎች የሚሆኑትን አራቱን አፍሪቃዋት ሀገሮች በስም አልጠቀሱም።
የወባ በሽታ በያመቱ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጥ ሕዝብ ሕይወት የሚያጠፋ ሲሆን፡ ከነዚሁ መካከል ዘጠና ከመቶው የሚኖረው ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ አፍሪቃውያት ሀገሮች ውስጥ ነው። ከሚሞተውም መካከል ብዙዎቹ ሕፃናት ናቸው። የተመ የጤና ጥበቃ እና የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ዘገባ መሠረት፡ አፍሪቃ ውስጥ በየቀኑ ሦስት ሺህ ሕፃናት በወባ በሽታ ሕይወታቸው ባጭሩ ይቀጫል። የጤና ጥበቃው ድርጅት ከዓለም ባንክ፡ ከዩኒሴፍና ከተመ የልማት መርሐ ግብር ድርጅት ጋር ባንድነት እአአ በ 1998 ዓም ወባን መታገል በሚል በጀመረው ዘመቻው እአአ እስከ 2010 ዓም ድረስ በወባ የሚያዘውን ሕዝብ አሀዝ በግማሽ ለመቀነስ ወስኖ ነበር፤ ይሁንና፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ በወቅቱ ከዚሁ ዓላማው እጅግ ርቆ ብቻ ሳይሆን የሚገኘው፡ በወባ የሚያዘው ሕዝብ አሀዝ ካለሟቋረጥ በመጨመር- በያመቱ ከሦስት እስከ አምስት ሚልዮን ሕዝብ በወባ እንደሚያዝ በዚህ በቀላሉ ሕክምና ሊወገድ በሚችለው በሽታ የብዙ ሰው ሕይወት መጥፋት በፍፁም ተቀባይነት የለውም የሚሉት የዩኒሴፍ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ አን ቬነማን አስረድተዋል።
ቡሽ በሚቀጥሉት አምስት ዓመት ውስጥ ለፀረ ወባ መታገያው በሚሰጡት አንድ ነጥብ ሁለት ቢልዮን ዶላር መጫቶችና ነፍሰ ጡሮች የሚኖሩባቸው ቤቶች በፀረ ወባ ትንኙ መድሀኒት ይረጫሉ፤ በፀረ ወባ ትንኙ መድሀኒት የተረጩ የአልጋ አጎበሮችና መድሀኒትም ይታደላሉ። ይኸው የገንዘብ ርዳታ በአፍሪቃ ለተጀመረው ለፀረ ወባው ዘመቻ ሁነኛ ድርሻ ሊያበረክት እንደሚችል ተገምቶዋል።