ዩራኒየም የገንዘብ ምንጭ የጤና ጠንቅ | አፍሪቃ | DW | 13.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዩራኒየም የገንዘብ ምንጭ የጤና ጠንቅ

ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ በተፈጥሮ ማዕድኖች የበለጸገች ናት። ዜጎቿ ግን የዚህ ሃብት ተጠቃሚ አለመሆናቸዉ ግልፅ ነዉ። በምስጢር የተያዘዉና በህገወጥ መንገድ የሚመረተዉ የዩራኒየም ማዕድን በስዉር ለተለያዩ ሃገሮች እንደሚሸጥ ነዉ የሚገለፀዉ።

ኮንጎ ዉስጥ የዩራኒየምን ማዕድን ማዉጣት በህግ የተከለከ ነዉ። ሆኖም ለኢራንና ለሰሜን ኮርያን ጭምር ሳይሸጥ እንዳልቀረ የሚጠቁም መረጃም የተመድ ይፋ አድርጓል። ኮንጎ ዉስጥ በርካቶች በዚህ ማዕድን መጎዳታቸዉን ይገምታሉ፤ በየጊዜዉም የተለያዩ የአካል ጉዳቶች ያሏቸዉ ህጻናት ይወለዳሉ።

ኪሚሎሎ የተሰኘዉ በካፉቡ ወንዝ ዳርቻ የሚገኘዉ አነስተኛ የሰፈራ መንደር በደቡባዊ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ከሉቡምባሺ ከተማ ወጣ ብሎ ይገኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመለከተዉ ሁሉም አማን ይመስላል። ከወንዙ ሰዉሰራሽ የዓሳ ማራቢያ አነስተኛ ኩሬዎች አሉ። የኩሬዉ ዓሶች በየጊዜዉ ይሞታሉ፤ የአካባቢዉ ኗሪዎች ደግሞ በበሽታ ይሰቃያሉ። ምክንያቱን ማወቅ የሚሹት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ጃን ክላዉደ ባካ ለአስር ዓመታት ያህል የዉሃዉን ናሙና ሲወስዱ ቆይተዋል። ባካ አንድ ስጋት አላቸዉ፤ አደገኛ የአቶም ጨረር። መረጃ ማግኘቱ ግን ለሕይወት አደጋ ነዉ ይላሉ፤

Jean Claude Baka Wasserproben

ጃን ክላዉደ ባካ

«የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እዚህ የምንሠራዉ አደገኛ ነገር ነዉ፤ ከማዕድን ማዉጫዉ አካባቢ ናሙና እንሰበስባለን። ስለዚህ ህገወጥ የዩራኒየም ማዕድን ስፍራ የበለጠ ለማወቅ የሚፈልግ በጣም ጥንቁቅ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም በፖለቲካዉም ሆነ በኤኮኖሚዉ ዋና የሚባሉት ሰዎች ከዚህ ህገወጥ ማዕድን ንግድ ገንዘብ ያገኛሉ። ከሁለት ዓመት በፊት አንድ የጭነት መኪና ከተዘጋዉ የሽንኮሎብዌ የማዕድን ጉድጓድየወጣ ዩራኒየም እንደጫነ ተይዟል። አንድ ጋዜጠኛ ፎቶግራፍ አንስቷል፤ የጨረር መጠኑንም መዝኗል። ከጥቂት ቀናት በኋላ ህይወቱ አለፈ። አሟሟቱ የተፈጥሮ ይሁን ይህን ታሪክ በመዘገቡ ግድያ ተፈጽሞበት ይሁን የተገኛ መረጃ የለም፤ ፈጣሪ ብቻ ነዉ ያንን የሚያዉቀዉ።»

ቁጥር 17 የተሰኘዉ ክሊኒክ ሉቡምባሺ ዉስጥ የሚገኝ ነፍሰጡር ሴቶችን የሚያስተናግድ የህክምና ጣቢያ ነዉ። እዚያ የሚያገለግሉት ፕሮፌሰር ጋብርየል ካፓያ ፅንስ በማህጸን ሳለ አስቀድሞ የሚኖረዉን የአካል ጉድነት በመለየቱ ሙያ የተካኑ ሲሆን ላለፉት 20 ዓመታት በማዕድን ማዉጫዉ ስፍራ የሚሰሩ ሴቶችን ሲያክሙ ቆይተዋል። አብዛኞቹ ሴቶችም የተለያዩ ጉዳቶች የደረሱባቸዉን ህጻናት መገላገላቸዉን ይናገራሉ።

«እዚህ የምንገኝ ሃኪሞች የምንመዘግባቸዉ የከፋ የአካል ጉድለቶች እየጨመሩ ሄደዋል፤ በተለይም የሸቀጦች ዋጋ በናረባቸዉ በ2006 እና 2007ዓ,ም። እዚህም አንዳንድ ፎቶዎች አሉኝ፤ ይህ ጽንስ የተከፈተ የሆድ ክፍል አለዉ፤ ይህኛዉ ደግሞ ከአካሉ ላይ ትልቅ እጢ አለበት፤ ቀጣዩ ፎቶላይ ደግሞ የጽንሱ ጾታ አይታወቅም፤ እነዚህ ሁሉ እንግዲህ በማዕድኑ ማዉጫዉ ስፍራ ከሚኖሩና ከሚሰሩ ወላጆች የተገኙ ልጆች ናቸዉ።»

ካፓያ ወላጆቹ በአደገኛዉ ጨረር እንደተጎዱ እርግጠኛ ናቸዉ። በዚያ ላይ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸዉ በተመድ እና በኪንሻ የአሜሪካን ኤምባሲ አማካኝነት የተሰበሰቡ መረጃዎች ህገወጥ የማዕድን ማዉጣት ተግባሩ በዚህ አካባቢ መቀጠሉን ያመለክታሉ።

Gynäkologe Gabriel Kapya zeigt Fotos von Missbildungen

ፕሮፌሰር ጋብርየል ካፓያ

ሽንኮሎብዌ ከሉቡምባሺ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የሚርቅ በዓለም ረዥም እድሜ ያስቆጠረ የዩራኒየም ማዕድን ማዉጫ ስፍራ ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1945ዓ,ም ዩናይትድ ስቴትስ የጃፓን ከተሞች ሄሮሽማና ናካሳኪ ላይ የጣለችዉ አቶም ቦምብ ከዚህ ስፍራ በተገኘዉ ዩራኒየም የተሠራ ነዉ። የዛሬ ዘጠኝ ዓመት የማዕድን ማዉጫ ስፍራዉ በይፋ ተዘግቷል፤ አደገኛ ጨረር የሚያስከትለዉ ማዕድንም እንዳይሸጥ በህግ ተከልክሏል። ሆኖም የአፍሪቃ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ኃላፊ ጎልደን ሚሳቢኮ በህገወጥ መንገድ ግን ድርጊቱ እንደሚፈፀም መረጃ ይፋ አድርገዋል። ይህን በማድረጋቸዉም ለእስራት ተዳርገዋል። አሁን የእሳቸዉን ስፍራ የያዙት ጃን ክላዉድ ባካ በዉሃና በአፈር ዉስጥ የሚገኘዉን የአደገኛ ጨረሩን መጠን መለካት ቀጥለዋል። እሳቸዉ ሉቡምባሺ ዉስጥ የሚፈጸመዉን ህገወጥ የዩራኒየም ማዕድን ንግድ ለማጋለጥ ጥረት ሲያደርጉ፤ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ላይ ደግሞ ፖለቲከኞች ከኒኩሊየር የኤሌክትሪክ ኃይል ስለማመንጨት ይነጋገራሉ። ኪንሻሳ ላይ በጎሮጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር 1958ዓ,ም የተገነባ በአፍሪቃ የመጀመሪያዉ የኒኩሊየር ማብላያ ይገኛል። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተዘግቶ ቆይቷል። ሆኖም በቅርቡ ተመልሶ ስራ ሊጀምር ይችላል። ያኔ ደግሞ የኮንጎ መንግስት መልሶ ዩራኒየም ማዕድን ማዉጣትን ዳግም ህጋዊ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዚሞነ ሽሊንድቫይን

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic