የ G-7 ስብሰባ በዋሺንግተን፤ ናይጄሪያና የዘይት ሃብቷ | ኤኮኖሚ | DW | 18.04.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የ G-7 ስብሰባ በዋሺንግተን፤ ናይጄሪያና የዘይት ሃብቷ

በአሕጽሮት G-7 በመባል የሚታወቁት ቀደምት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት የገንዘብ ሚኒስትሮች ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ዋሺንግተን ላይ ተሰብስበው በዓለምአቀፉ ወቅታዊ የኤኮኖሚ ሁኔታ ላይ መክረዋል።

የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ዎልፎቪትስ

የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ዎልፎቪትስ

ሰንበቱን የዓለም ባንክንና የዓለምአቀፉን ምንዛሪ ተቋም ስብሰባ በጠቀለለው ጉባዔ ስለ ምንዛሪ ዋጋ ውጣ-ውረድ፣ ሰለ ዓለም ንግድና አጠቃላይ የኤኮኖሚ ዕድገት፤ እንዲሁም ስለ ልማት ዕርዳታ በሰፊው ተወርቷል። አንዲት ወዳጃቸውን ዕድገት በመስጠት ሥልጣናችውን ያላግባብ በመጠቀማችው የተወቀሱት የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት የፓውል ዎልፎቪትስ ዕጣም እንዲሁ ማነጋገሩ አልቀረም።

የዓለም ኤኮኖሚ ምንም እንኳ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ውጣ-ውረድ ችግር ፈጥሮ እንደቀጠለ ቢሆንም በወቅቱ ቀጣይ በሆነ የዕድገት ሂደት ላይ መሆኑ ነው የተነገረው። ለዕድገቱ በተለይ የእሢያ የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ወሣኝ ድርሻ እንዳለውም ተመልክቷል። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF እንደሚገምተው ወይም እንደሚተነብየው ከሆነ የዓለም ኤኮኖሚ በያዝነውና በሚቀጥለው 2008 ዓ.ምም. 5 በመቶ ዕድገት ይታይበታል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። እርግጥ በዓለም የንግድ ግንኙነትና የምንዛሪ ገበያ ይዞታ ላይ ያልተጠበቀ ችግር ካልተከሰተ!
የበለጸጉት መንግሥታት የነዳጅ ዘይት ዋጋን መናር ምክንያት በማድረግ፤ ሩሢያን በመሳሰሉ አገሮች የነዳጅ ዘይትና የጋዝ አቅርቦት ላይ ያለባቸውን ጥገኝነትም ለመቀነስ የአቶም ኤነርጂን ይበልጥ ለመጠቀም ተስማምተዋል። ጀርመንን የመሳሰሉት አደገኛ የሆኑትን የአቶም ሃይል ጣቢያዎች ቀስ በቀስ ለመዝጋትና የታዳሽ ኤነርጂ አጠቃቀምን ለማዳበር የተነሱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህን ሃሣብ ሲቃወሙት ቆይተዋል። ሆኖም የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር እዚህም ጸረ-አቶሙን አቋም ለዘብ እያደረገው መሄዱ አልቀረም።

የሰባቱ በኢንዱስትሪ ልማት ቀደምት የሆኑ መንግሥታት የገንዘብ ሚኒስትሮች በዓለም ባንክና በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በ IMF የዓመቱ የመጀመሪያ ስብሰባ ዋዜማ ባለፈው አርብ ዋሺንግተን ላይ ተገናኝተው ባካሄዱት ንግግር የዓለም ንግድ ድርጅት ከስምምነት እንዳይደረስ መሰናክል የሆኑትን ችግሮች እንዲያስወግድም ጥሪ አድርገዋል። ሚኒስትሮቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳስገነዘቡት በዶሃ የልማት ዙር የተንቀሳቀሰው ፍትሃዊ ንግድን የማስፈን ጥረት ከግቡ መድረሱ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው።

G-7 በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ ቻይናን የመሳሰሉት መንግሥታት የምንዛሪ ንግድ ደምቦቻቸውን እንዲያለዝቡም ጠይቋል። በሚኒስትሮቹ ስብሰባ ላይ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዕድገትም እንዲሁ አንዱ ዓቢይ የአጀንዳ ርዕስ ነበር። እርግጥ አፍሪቃን በተመለከተ ሃቁ ለጋሽ አገሮች ዕርዳታቸውን በዕጥፍ ለማሳደግ ከሁለት ዓመታት በፊት በ G-8 መንግሥታት ጉባዔ ላይ የገቡትን ቃል አሁንም የሚያሟሉ መስለው አለመታየታቸው ነው።

የዓለም ባንክ ባለሥልጣናት በዚሁ የተነሣ በተለይ የድሃ ድሃ ለሆኑት አገሮች ወደፊት ብድር በማቅረቡ ረገድ ሃሣብ ላይ መውደቃቸው አልቀረም። በዋሺንግተኑ ስብሰባ መጨረሻ ባለፈው ዕሑድ ጋዜጣዊ ጉባዔ ያካሄዱት የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ፓውል ዎልፎቪትስና የምንዛሪው ተቋም አስተዳዳሪ ሮድሪጎ ራቶ የበለጸገው ዓለም በተለይ ለአፍሪቃ ዕርዳታውን ለማሳደግ የገባውን ቃል ዕውን እንዲያደርግ በጋራ ጠይቀዋል። የቀድሞው የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣን ፓውል ዎልፎቪትስ የዓለም ባንክ አስተዳዳሪ ከሆኑ ወዲህ በተለይ የአፍሪቃን ልማት ማተኮሪያቸው አድርገው መቆየታቸው የሚታወቅ ነው። ሙስናን የማስወገድ ጥረትንም አንቀሳቅሰዋል።
ይሁንና የግል ወዳጃቸውን ለመጥቀም ሥልጣናቸውን ያላግባብ መጠቀማቸው ግን አሁን የሞራል ልዕልናን ሳያሳጣቸው አልቀረም። የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን የዎልፎቪትስ ድርጊት ከባንኩ ጋር ባለው ትብብር ችግር እንዳይፈጥር ስጋቱን ገልጿል። ዎልፎቪትስ ከሁለት ዓመት በፊት እንደተሾሙ በጊዜው በዓለም ባንክ ውስጥ ትሰራ የነበረች ወዳጃቸው ሻሃ ሪዛ ከፍተኛ የደሞዝ ክፍያና የማዕረግ ዕድገት እንድታገኝ ማድረጋቸው ከዚህም አልፎ ከመንግሥት ነጻ በሆኑ ድርጅቶች በኩል ሥልጣን ይልቀቁ የሚል ግፊትን እስከማስከተል ነው የደረሰው። ዎልፎቪትስ እርግጥ ስህተት መስራቴን አምናለሁ ቢሉም ሥልጣን እንዲለቁ የቀረበውን ጥሪ ግን አልተቀበሉም።

“በዚህ ድርጅት ተልዕኮ አምናለሁ። እንደምወጣውም አልጠራጠርም። በመግለጫችን ወደተስማማንበት ጉዳይ ልመለስና አሁን ቦርዱ ጉዳዩን እየተመለከተ ነው። እና ሥራውን እንዲያጠናቅቅ ልንጠብቅ ይገባል”

በእርግጥም የዎልፎቪትስ የወደፊት ዕጣ በዓለም ባንክ 24 የቦርድ ዓባላት ውሣኔ ላይ ጥገኛ ሆኖ ይቀጥላል። ከሁሉም በላይ አሰቸጋሪው ነገር ግን መልሰው ዓመኔታ ማግኘት መቻላቸው ነው። ዎልፎቪትስ ዋናው ነገር አሁን በሥራዬ መቀጠሌ ነው ቢሉም ብዙዎች የባንኩና የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ዓባላት ግን የወቅቱን ሁኔታ በስጋት ነው የሚመለከቱት። የመንግሥታቱ ተጠሪዎችም ጉዳዩን ለማካረር አይፈልጉ እንጂ ጉዳዩ መጣራቱን አጥብቀው ይሻሉ። የብሪታኒያው ፊናንስ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን እንዳሉት የዎልፎቪትስን ዕጣ የሚወስነው በጉዳዩ የሚካሄደው ምርመራ ነው።

“ዎልፎቪትስ መግለጫቸውን ሰጥተዋል። ይቅርታም ጠይቀዋል። የዓለም ባንክም ጉዳዩን የሚመለከቱትን ገጾች በሙሉ አውጥቷል። እንግዲህ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን መርምሮ ዘገባውን እስኪያቀርብ መጠበቁ ተገቢ ይመስለኛል። ከዚህ በላይ የምጨምረው ነገር የለም”

የበለጸጉት የኢንዱስትሪ መንግሥታት ተጠሪዎች ወደ ዋሺንግተን ያመሩት በመሠረቱ በዓለም የኤኮኖሚ ሁኔታ ላይ ለመምከር ቢሆንም ስብሰባው ከጅምር እስከ መጨረሻው የዎልፎቪትስ ችግር የጋረደው ነበር ለማለት ይቻላል።

ናይጄሪያ በነዳጅ ዘይት የታደለች አገር ስትሆን ይሄው ሃብቷ በአንድ በኩል ዋነኛ የገቢ ምንጯ በሌላም የብዙዎቹ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ችግሮቿ ምንጭ ሆኖ ነው የሚገኘው። ናይጄሪያ በአፍሪቃ ታላቋ ነዳጅ ዘይት አምራች ስትሆን በዚሁ ንግድም በዓለም ላይ ስድሥተኛዋ ናት። በናይጀር-ዴልታ አካባቢ በየቀኑ የሚወጣው ጥሬ ዘይት ሁለት ሚሊዮን ተኩል በርሚል ገደማ ይደርሳል።

ይሁን እንጂ የነዳጅ ዘይት ሃብት መገኘት የተቀረው የናይጄሪያ የኤኮኖሚ ዘርፍ ችላ ተብሎ እንዲተው ማድረጉ አልቀረም። ከነዳጅ ዘይት በሚገኝ የገንዘብ ጥቅም የተሳከሩት ተከታታይ መንግሥታት የዕርሻና የአምራቹን ዘርፍ ከናካቴው ረስተውት አልፈዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ታዲያ የነዳጅ ዘይት ምርት እያደገ ሲሄድ ሌላው የኤኮኖሚ ዘርፍ ማቆልቆሉ አገሪቱ ከውጭ በሚገቡ የዕርሻ ምርቶችና ሌሎች የኢንዱስትሪ ሸቀጦች ላይ ጥገኛ እንድትሆን ነው ያደረገው።

እርግጥ እንደ አንድ ታላቅ ነዳጅ ዘይት አምራች አገር የናይጄሪያ ችግር ገና ዛሬ አይደለም የጀመረው። በ 1956 ሃብቱ ከተገኘ ጀምሮ ያለ ነው። ናይጄሪያ በዚሁ ነዳጅ ዘይት ሽያጭ እስከዛሬ 400 ቢሊዮን ዶላር አስገብታለች። ግን ሃብቱ በልማት ተንጸባርቋል ወይ? አልሆነም። ሃብቱ በባለሥልጣናት ሲዘረፍ መኖሩ ነው መሪሩ ሃቅ። በነዳጅ ሃብት በታደለው የናይጀር-ዴልታ አካባቢ የጋራው ሃብት ያላግባብ በመመዝበሩ ሰፊው ሕዝብ ዛሬም ድህነትና ተሥፋ መቁረጥ ተጭኖት ነው የሚገኘው። እንደ ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ አስከፊ የዕለት ኑሮውን ከመግፋት አልተላቀቀም።

በናይጄሪያ አንዴ የነዳጅ ዘይቱ መገኘት የአዲስ ትንሣዔን ያህል ነበር። ይሄው ያስከተለው ጸጋ መዓት ፔትሮ ዶላር ግን ለሕዝቡ ወይም ለዕድገቱ አልደረሰም። የሩቁን እንተወውና ፕሬዚደንት ኦሉሼጉን ኦባሣንጆ ከ 16 ዓመታት ወታደራዊ አገዛዝ በኋላ በትረ-መንግሥቱን ከጨበጡ ከ 1999 ወዲህ እንኳ በተለይ የጥሬ ዘይት ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ መናር ባስከተለው አመቺ ሁኔታ ናይጄሪያ ብዙ ገንዘብ ነው ያስገባችው። በዚህም 45 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ለማከማቸት በቅታለች። ግን ገንዘቡ አሁንም ለትምሕርት፣ ለጤና ጥበቃ፣ ወይም ለአጠቃላይ መዋቅራዊ ግንባታ አልዋለም። እንደተመደው ተዘረፈ እንጂ!

ብዙዎች ጥናቶች ባለፈው ዓመት ቀርቦ የነበረ ነጻ መረጃን ጨምሮ በናይጄሪያ የፔትሮ ዶላር አጠቃቀም ረገድ አስከፊ ምዝበራ መኖሩን አረጋግጣጠዋል። ከመንግሥታዊው ምዝበራ ባሻገር ሃብቱን በመከፋፈሉ ረገድ ብዙዎች ማሕበራዊ ውዝግቦች ሲፈጠሩ በተለይ በናይጀር-ዴልታ ብርቱ ዓመጽ መከተሉም አልቀረም። ሕዝብ ከአካባቢው አየር መበከል አልፎ ከሌሎች ነዳጅ ዘይት ከማያመርቱ ክፍለ-ሐገራት የተለየ ድርሻ የለውም። ቁጣው እያየለ መሄዱ ደግሞ ዓመጽን ነው ያጠናከረው። ይህም በመንግሥትና በውጭ ኩባንያዎች ላይ ያለው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ካለፈው ዓመት ወዲህ ባየለው ዓመጽ ሳቢያ ናይጄሪያ የምታወጣው ነዳጅ ዘይት መጠን በሩብ ነው የቀነሰው።

ታጣቂ ቡድኖች በነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪው ላይ ዘመቻቸውን ሲያጠናክሩ ጥያቄያቸውን ለማሰማት ወይም የገንዘብ ካሣ ለማግኘት ከመቶ የማያንሱ የውጭ ሠራተኞችን ጠልፈዋል። በናይጀር-ዴልታ ተቃውሞው ለነገሩ አዲስ ነገር አይደለም። የአካባቢውን ብከላ በመቃወም ታዋቂው የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋች ኬን-ሣሮ-ዊዋ ከስምንት የኦጎኒ ማሕበረሰብ መሰሎቻቸው ጋር በጊዜው ወታደራዊ መንግሥት ከተገደሉ 12 ዓመት አለፋቸው። ችግሩ በኦባሣንጆ የሥልጣን ዘመንም ማሰሪያ ሊያገኝ አልቻለም፤ ቀጥሏል።

ናይጄሪያ ውስጥ በፊታችን ቅዳሜ እንደታቀደው ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ከተካሄደ የኦባሣንጆ ዘመን ያበቃል። አዲሱ መስተዳድር ችግሩ ቀጣይ ቅርስና ፈተናም እንዳይሆንበት ከፈለገ ለጉዳዩ ዓቢይ ክብደት መስጠቱ ግድ ነው። ችግሩ ያስከተለው የገንዘብ ክስረት ራሱ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ናይጄሪያ በዓመጹ ሳቢያ ባለፈው ዓመት ብቻ በምርት መሰናከል የተነሣ ያጣችው ገቢ 4,4 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። መፍትሄው አገሪቱ በታደለችው ጸጋ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ በሚገባ ማሻሻል፤ ሃብቱን ለሕብረተሰብ ዕድገት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል ብቻ ነው።