1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የፍርድ ዉሳኔና የመብት ተሟጋቾች

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የአሸባሪነት ክስ የተመሠረተባቸዉ 24 ተጠርጣሪዎች ጥፋተኛ ናቸዉ ሲል በይኗል። ከመካከላቸዉ ካለፈዉ መስከረም ወር አንስቶ እስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በተደጋጋሚ ለብይን እየተቀጠረ ዛሬ ላይ ደርሷል።

ብይኑን ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ CPJ ጋዜጠኞችን ጭጭ ለማድረግ ህጉ አጓጉል ሥራ ላይ ዉሏል በማለት ተችቷል። ሂዉማን ራይትስ ዎች በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት በፖለቲካ የተቃኘ ክሱን በአስቸኳይ እንዲያነሳና ነፃ ሃሳብን እና ሰላማዊ ዜጎችን ወንጀለኛ የሚያደርገዉን የአሸባሪነትን ህግ እንዲያሻሽል ጠይቋል። የፍርድ ቤት ዉሳኔዉ በተሰማ በሰዓታት ልዩነት ይፋ የሆነዉ የCPJ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በድጋሚ ተቺና ገለልተኛ የሆኑ ዘገባዎችን ጭጭ ለማድረግ ህግን አጓጉል በመጠቀም ተሳክቶለታል ሲል ተችቷል።

Logo CPJ

Logo CPJ

በድርጅቱ መግለጫ የተጠቀሱት የአፍሪቃ ዘርፍ አስተባባሪ ሞሐመድ ካይታ የእስክንድር ጥፋተኛ መባል ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን ከማሰርም ሆነ ወደስደት እንዲገፉ ከመቅጣት ወደኋላ እንደማትል አመላካች ነዉ ብለዋል። ሂዉማን ራይትስ ዎች በበኩሉ ካለፈዉ መስከረም አንስቶ እስር ላይ የሚገኘዉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 11 ጋዜጠኞች በፀረ ሽብር ህጉ መከሰሳቸዉን ጠቁሟል።

ሁኔታዉም የኢትዮጵያ መንግስት ሌላዉ ቀርቶ የተለሳለሰ ትችትን ሳይቀር እንደማያልፍ እንደሚያመላክትም የድርጅቱ የአፍሪቃ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮ ገልፀዋል። የድርጅቱ የአፍሪቃ ዘርፍ ተመራማሪ ለቲሻ በይዳ ናይሮቢም ይህንኑ ያጠናክራሉ፤

«የዛሬዉ ብይን ኢትዮጵያ ዉስጥ በጣም የተለሳለሱ ትችቶች ወይም የግል አስተያየቶች እንኳ በትዕግስት እንደማይታለፉ የሚያረጋግጥ ማሳያ ነዉ። ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህ እንደተፈለገ የሚተረጎምና ተሳልቆ የተላበሰዉ ፀረ ሽብር ህግ ባስቸኳይ መሻሻል እንደሚኖርበት በግልፅ ያመለክታል። የዚህ ህግ አብዛኞ መጥፎ አንቀፆች በአሁኑ የክስ ሂደት ገቢራዊ ሆነዋል አላግባብም ተጠቅሰዋል። እንደሚመስለኝ የዛሬዉ ብይን በተጨማሪ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነፃ የፍትህ ስርዓት እንደሌለ አመላካች ነዉ።»

ከመስከረም ወር አንስቶ እስር ላይ የቆዩትም ሆኑ በሌሉበት የተከሰሱት ጉዳይ፤ ለብይን በተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ሲሸጋሸግ እዚህ መድረሱን በመጠቆም ለቲሻ በይዳ ድርጅታቸዉ ደጋግሞ የፍርድ መጓተት መኖሩን ማመልከቱንም ገልፀዋል።

Human Rights Watch Logo Flash-Galerie

«ግልፅ የሆነ የፍርድ ሂደት መጓተትና ጥሰት ታይቷል፤ ተከሳሾቹ የፍርድ ሂደታቸዉ ከመታየቱ ሁለት ወራት በፊት ጠበቆቻቸዉን የማግኘት እድል እንደሌላቸዉ ብቻ ሳይሆን በዚህ ላይ ያለንን ስጋት በተለያዩ አጋጣሚዎች ደጋግመን ግልፅ አድርገናል። በዚያ ላይ ሁለቱ ታሳሪዎች እስር ቤት ስለሚደረግባቸዉ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ አቤቱታ አቅርበዋል፤ አቤቱታቸዉ በአግባቡና በበቂ ሁኔታ አልተመረመረም። በተጨማሪም በክሱ ሂደት እስኪፈረድባቸዉ ድረስ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ የመታየታት መብታቸዉ ከኢትዮጵያ መንግስት በሚሰነዘሩ አስተያየቶች እንዲሁም አብዛኞቹ ተከሳሾች በታዩበት አኬልዳማ በተሰኘዉ ዘጋቢ ፊልም ስርጭት በግልፅ ተጥሷል።»

የፕረስ ነፃነት በሚመለከት አመታዊ ዘገባዎችን የሚያወጡ የጋዜጠኛ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ዉስጥ የፕረስ ነፃነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመለክታሉ። እስር ላይ በሚገኘዉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ሆነ እስር ሽሽት በስደት የሚገኙ ጋዜጠኞች ላይ የተላለፈዉ የጥፋተኝነት ብይን በወደፊቱ የሀገሪቱ የፕረስ ይዞታ ላይ ስለሚኖረዉ ተፅዕኖ ለቲሻ በይዳ ሲናገሩ፤

«የፕረስ ይዞታዉ ከችግር በላይ በሚገለፅ ሁኔታ ላይ መሆኑ ይታወቃል። እንደሚመስለኝ መንግስት ማንኛዉንም ስልት ተጠቅሞ ነፃ ፕረስ፤ ነፃ ሃሳብና ነፃ አስተያየትን ለመዝጋት እየጣረ ነዉ። እኛ በተለይ በጥቅሉ ካለፈዉ 2011ዓ,ም መጨረሻ አንስቶ በፀረ ሽብር ህጉ የተከሰሱት 34 ሰዎች ሁኔታ እጅግ ያሳስበናል። ከእነዚህ ዉስጥ ደግሞ 11ዱ ጋዜጠኞች ናቸዉ። እናም በተጨባጭ የዚህ ህግ አገልግሎት ገለልተኛ ዘገባዎችና ትችቶችን ፀጥ ለማድረግ ሥራ ላይ ከሚዉሉት አንዱ መሆኑ ነዉ።»

በኢንተርኔት የድምፅ አገልግሎትን የሚያግድ ህግ መዉጣቱ እና የህትመት መገናኛ ብዙሃንን ለቅድመ ምርመራ በሚጋብዘዉ የአሳታሚ ተቋም መመሪያ ችግር ዉስጥ መሆናቸዉን ከግምት በማስገባት የአገሪቱ የፕረስ ይዞታ ወዴት እያመራ ነዉ ለሚለዉ የሂዉማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ዘርፍ ተመራማሪ ለቲሻ በይዳ እንዲህ ይላሉ፤

«እንደሚመስለኝ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ነፃ ፕረስ እንዴት ሊያድግ እንደሚችል መገመት ያዳግታል። በተደጋጋሚ የተለያዩ መድረኮች፤ ልዩ ልዩ አዳዲስ ሃሳቦችን ሊያንሸራሽሩ የሚችሉ፤ ማኅበራዊ መገናኛዎችን ተጠቅሞ የራስን ሃሳብ የማጋራቱ አጋጣሚዎች ነበሩ ነገር ግን በተጨባጭ እነዚህ መድረኮች መዘጋታቸዉን እናያለን። እናም አሁን ላይ ሆነዉ ሲያዩት የወደፊቱ እጅግ ጨለማ ነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic