የጣልያን ሕዝበ ዉሳኔና ጠቅላይ ሚኒስትሩ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 05.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጣልያን ሕዝበ ዉሳኔና ጠቅላይ ሚኒስትሩ

የኢጣልያ መንግሥት የሃገሪቱ ሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ተሃድሶ እንዲደረግ ባቀረበዉ ሕዝበ ዉሳኔ ሕዝብ ማሻሻያ አለመፈለጉን ገለፀ። የሕዝበ ዉሳኔዉን ዉጤት ተከትሎ የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማትዮ ሬንዚ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስልጣን እንደሚለቁ በይፋ አስታዉቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:03

የጣልያን ሕዝበ ዉሳኔ 

 

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዎ ሬንዚ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ ሥልጣናቸዉን ሊለቁ ነዉ። በሕዝበ ዉሳኔው ሬንዚ ያቀረቡትን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ 59 ከመቶ የሚሆነዉ የሀገሪቱ ዜጋ እንዳልተቀበለዉ፤ 41 ከመቶዉ ብቻ እንደደገፈዉ የጣሊያን የሀገር ዉስጥ ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ ያደረገዉ ዉጤት አመልክቷል። ሬንዚ ዉጤቱን አስመልክተዉ ትናንት ማምሻዉን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  «ስትሸነፍ ምንም እንዳልተፈጠረ ማስመሰል አያስፈልግም፤ የመንግሥቴ ህልዉና እዚህ ላይ ያከትማል» ማለታቸዉ ተዘግቧል።

«ከጣሊያን ፖለቲካ ዉስጥ በጣም ብዙ ስልጣኖችን ለመሰረዝ ፈልጌ ነበር፤ ሴኔት፣ ክፍለ ሀገር፣ ብሄራዊ ምክር ቤት የመሳሰሉትን። አልተሳካልኝም። ስለዚህ ስልጣኔን መልቀቅ ይኖርብኛል። ነገ ከሰዓት በኋላ ካቢኔዉን

ሰብስቤ እጅግ ግሩም፣ የተስማማ እና ጠንካራ የነበሩ የሥራ ባልደረቦቼን አመሰግናለሁ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መንግሥቱ በመሄድ ለሪፑብሊኩ ፕሬዝደንት መልቀቂያዬን አቀርባለሁ።»

የሬንዚ ስልጣን መልቀቅ በዩሮ ሸርፍ ተጠቃሚዉ ጎራ ስጋት መፍጠሩ ቢነገርም የአዉሮጳ ኅብረት የኤኮኖሚ እና የፋይናንስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፒየር ሞስኮቪች ግን ከቁጥጥር ዉጭ አይሆንም ማለታቸዉ ተዘግቧል። የተለያዩ ዘገባዎች ግን የሬንዚ ርምጃ ጣሊያን እና የዩሮዉን ቀጣና ጥያቄ ላይ እንደሚጥል ያመለክታሉ። ከጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሬንዚ ጋር በቅርበት ሲሰሩ የቆዩት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በዉሳኔያቸዉ ማዘናቸዉን ቃል አቀባያቸዉ ሽቴፈን ዛይበርት ዛሬ ገልፀዋል፤

«መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዎ ሬንዚን ከስልጣን የመልቀቅ ዉሳኔ በሃዘን ተቀብለዋል። ከማቴዎ ሬንዚ ጋር በመተማመን በጥሩ ሁኔታ አብረዉ ሠርተዋል። ሆኖም ግን የጣሊያን ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ዉሳኔ ደግሞ መከበር አለበት።»

ትናንት በተካሄደዉ ሕዝበ ዉሳኔ 47 ሚሊየን የተመዘገቡ የሀገሪቱ ዜጎች ድምፃቸዉን ሰጥተዋል።

የሕዝበ ዉሳኔዉን ዉጤት ተከትሎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስልጣን እንደሚለቁ በይፋ ያሳወቁት የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማትዮ ሬንዚ ፤ በጎርጎረሳዉያኑ 2014 ዓ,ም ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን ስልጣናቸዉን በጎርጎረሳዉያኑ 2018 ዓ,ም እንደሚጠቃለልነበር የሚታወቀዉ። ጣልያን የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ ካካሄደችዉ ሕዝበ ዉሳኔ ዉጤት በኋላ ምን ይጠብቃታል? የአዉሮጳ ሃገራት ምላሽስ ምን ይመስላል? በሌላ በኩል በሳምንቱ መጨረሻ የኦስትርያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫስ ዉጤትስ ምን ይመስላል የሚሉትን ነጥቦች በተመለከተ የሮሙን ወኪላችንን በስልክ ጠይቀነዉ ነበር።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic