የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ የ100 ቀናት አመራር | ኢትዮጵያ | DW | 06.01.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ የ100 ቀናት አመራር

ከጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት በኋላ ባለፈዉ መስከረም ወር አጋማሽ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን ሲይዙ ፤ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ላቀፈችዉ ኢትዮጵያ የፖለቲካ አስታራቂ እና ጥሩ መፍትሄን ያስገኛሉ የሚል ተስፋን አሰንቆ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ከያዙ በኋላ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ፤ የመሪ ለዉጡን ተከትሎ በአገሪቱ የሚኖረዉ ፖለቲካዊ እርምጃ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽሎ የመናገር ነፃነት ይኖራል፤ በሲቪል ማህበራት ላይ እና በብዙሃን መገናኛዎች ላይ የሚደረገዉ ጫና ይቆማል፤ የሚል ተስፋ ነበራቸዉ። ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ከያዙ መቶ ቀናት አለፋቸዉ፤ በዚህ ግዜ ዉስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ የአገሪቱ ፖለቲካዊ እርምጃ ምን ይመስላል? ሉድገር ሻዶምሲኪ ያጠናቀረዉ ዘገባ እንደሚከተለዉ ተቀናብሯል።
ከመነሻዉ ተስፋ ሰጪ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ መሃላ ከመፈጸማቸዉ አስቀድሞ፤ በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ወቅት፤ መንግስት ለ2,000 እስረኞች ምህረት አድርጎ ከእስር በነፃ ለቀቀ። በተመሳሳይ ወቅት፤ መንግስት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀዉ ቡድን፤ ከኦጋዴኑ ብሄራዊ ነፃ አዉጭ ግንባር- ኦብነግ ጋር፤ ኬንያ ዉስጥ ለድርድር ተቀምጦአል። ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ አልጃዚራ፤ በተሰኘዉ የቴሌቭዥን ጣብያ ቀርበዉ፤ ከኤርትራ ጋር ለማንኛዉም የሰላም ዉይይት ዝግጁነታቸዉን ሲናገሩ፤ ሃሳቡ ብሩህ ተስፋን ፈጥቆ፤ የብዙዎች ምኞት እንደሚሳካ እምነት አሳድሯል።

Johan Persson schwedische Journalisten in Äthiopien zu elf Jahren Haft verurteilt

በአሸባሪነት የተፈረጀዉና ይቅርታ የተደረገለት ስዊድናዊ ጋዜጠኛ

በደቡብ ኢትዮጵያ ከወላይታ ብሄር ተወላጅ የሆኑት፤ የዉሃ ምህንድስና ምሁር፤ አቶ ኃይለማርያም፤ በእርግጥም የፖለቲካ እና የስልጣን ሽኩቻ፤ እንደሚፈጠር በሚገመትበት ወቅት፤ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣኑን መያዛቸዉ፤ ተምሳሌቱ ትልቅ ነዉ ያሉት፤ ከመንግስት ነፃ የሆነዉ፤ ዓለማቀፍ ፖለቲካ ጉዳዮችን የሚከታተለዉ ቢሮ በለንደን፤ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ምሁሩ ጃሰን ሞስሊ እንዲህ ይገልፃሉ፤ « እንደ ወላይታ ካለ አነስተኛ ከሆነ ጎሳ የመጣ ሰዉ ስልጣን መያዙ በመሰረቱ ተምሳሌቱ ትልቅ ትርጉም አለዉ። ሆኖም ተግራባዊነቱ መስራትም ይኖርበታል። የሶስት ሴት ልጆች አባት የሆኑት፤ የ 47 ዓመቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከ1997 ዓመተ ምህረቱ ደም አፋሳሽ ምርጫ በኋላ፤ ከግዜ ወደ ግዜ አንባገነን እየሆኑ ከመጡት ከሟቹ ከመለስ ዜናዊ ጋር ሲነፃፀሩ በርግጥም በፖለቲካዉ ረገድ ግርማ ሞገሳቸዉ እንብዛም አይታይም። ኃይለማርያም በመለስ ዘመን፣የክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ ፤ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዋል። ሆኖም ኃይለማርያም ደሳለኝ በትጥቅ ትግሉ ከኢህአዴግ ጋር አብረዉ ባይኖሩም በትምህርቱ በተሻለ መልኩ በመግፋታቸዉ በርካቶች የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን እንዲይዙ ፈልገዉ ነበር። ስልጣኑን ከያዙ በኋላ ግን በአገሪቱ አንዳችም ፖለቲካዊ ለዉጥ አላደረጉም ሲሉ ብዙዎች ቅሪታቸዉን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳዮች ምሁሩ ጃሰን ሞስሊም ይህንኑ ነዉ የሚናገሩት «የአሁኑን መንግስት የፖለቲካ ስራዎች ካለፈዉ አስተዳደር ጋር ስናነፃጽረዉ፤ በእዉነቱ ምንም አይነት ለዉጥ አይታይበትም። በቅርቡ በካቢኔ አንድ አነስተኛ ለዉጥ ተደርጎአል፤ ግን ይህ ለዉጥ ትልቅ የሚባል እና የፖለቲካዉን አካሄድ የሚቀይረዉ አይደለም።

ከጎረቤት ሶማልያ ጋር ያለዉ የፖለቲካ ሁኔታ፤ የዓባይን ዉሃ አያያዝ በተመለከተ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር የነበረዉ አቋም አሁንም አልተቀየረም። በመጠኑ በጥያቄ የሚታይ ነገር ቢኖር፤ በሰሜን አጎራባች ከሆነችዉ ከኤርትራ ጋር ያለዉን ግንኙነት ለማሻሻል የሚደረግ እንቅስቃሴ የመኖር አለመኖሩ ጉዳይ ነዉ። ስለዚህ ያለዉ ሁኔታ የድሮዉን መቀጠል ነዉ።» መንግስት እንደተለወጠ የሀገሪቱ የልማት ትብብር አጋሮች ለለዉጥ የነበራቸዉ ጉጉት እየከሰመ መጣ። ምዕራባዉያን ዲፕሎማቶች፤ ጋዜጠኞችን በተመለከተ የፍርድ ቤት ችሎት ላይ፤ አንድም ቀን በታዛቢነት ሳይገኙ የዋሉበት ቀን የለም። እንደ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት፤ CPJ ገለጻ፤ በጸረ - ሽብሩ ህግ በአሸባሪነት ከተከሰሱት አስራ አንድ ጋዜጠኞች መካከል «እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም መጨረሻ» ስድስቱም በእስር ላይ ሲሆኑ ከነዚህ መካከል ታዋቂዉ ተሸላሚ ዓምደኛ እስክንድር ነጋ ይገኝበታል። ይኸዉ የፀረ-ሽብር ህግን ተመልክቶ 29 ሙስሊም ጋዜጠኞች፤ ሙስሊም የሃይማኖት አባቶች፤ መብት ተቆርቋሪዎች፤ በአሸባሪነት ተፈርጀዋል። ለበርካታ ግዜያት ይህንኑ በመቃወም፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ቅሪታቸዉን በማሰማት ላይ ሲሆኑ፤ ዘወትር ዓርብ በአዲስ አበባዉ አንዋር መስጊድ መንግስት ላይ የተቃዉሞዉ ድምጻቸዉን ማሰማታቸዉን ቀጥለዋል። በጎርጎረሳዉያኑ 2012 መጠናቀቅያ ላይ፤ 16 የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነት ይከበር ሲሉ በይፋ በላኩት ደብዳቤ መጠየቃቸዉ ይታወሳል። ይህን ደብዳቤ ከላኩት መካከል፤ ጀርመናዊዉ አሌክሳንደር ግራፍ ላምስዶርፍ ይገኙበታል። ላምስዶርፍ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፤ «አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ግልፅ የፖለቲካ አካሄድ የሚከተሉ ከሆነ ሀገራቸዉን ወደፊት ለማራመድ እድሉ አላቸዉ። የማኅበረሰቡን ግልፅነት፤ ትችትና ነጻ ሃሳቦችን ለማስተናገድ ከፈቀዱ፤ ከጎረቤቶቻቸዉ ጋ ያላቸዉን ግንኙነት ካሻሻሉ፤ ለምሳሌ አሥመራን ለመጎብኘት ቢሄዱ ለሰላም ላላቸዉ ቁርጠኝነት ዋና አመላካች ነዉ። ይህም ለኢትዮጵያዉያንና ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ላላት ሁኔታ ፍፁም አስተማማኝ እና መሰረታዉ ጉዳይ ነዉ።» በስልታዊ አቀማመጥዋ የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ በሆነችዉ በአፍሪቃ መዲና - ኢትዮጵያ ከባድ ተግዳሮቶች ተደቅነዋል። በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ያለዉ የህዝቧ ቁጥር ከአፍሪቃ ሁለተኛ ደረጃን እንድትይዝ ቢያደርጋትም፤ አሁንም እድገቱ አልተገታም። በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን ያቀፈችዉ ሀገር፤ ብሄራዊ አንድነትን ከመገንባት አኳያ፤ ትግል ይዛለች። ምንም እንኳ የሀገሪቱ ኤኮኖሚ በሁለት አሃዝ ማደጉ ቢነገርም፤ የዚህ ተጠቃሚዉ በጣም ጥቂቱ፤ መካከለኛ ገቢ ያለዉ የከተማዉ ነዋሪ ነዉ። ከፀጥታ አኳያ፤ በዓለም ጸረ-ሽብርተኝነትን ከሚዋጉት ሀገራት መካከል፤ ኢትዮጵያ በሶማልያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ቀዳሚዉን ስፍራ ይዛለች።

እንግዲህ እነዚህ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአዲሱ ከካቤኔያቸዉ ጋ በመሆን፤ ባፋጣኝ ምላሽ ሊሰጧቸዉ የሚገቧቸዉ ጉዳዮች መሆናቸዉ ነዉ። ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሹመታቸዉን ከተቀበሉበት ቀን ማግስት አንስተዉ በተደጋጋሚ፤ በፓለቲካዉ ከእሳቸዉ ቀድመዉ ስልጣን ላይ የነበሩትን የመለስ ዜናዊን ጅምሮች፤ ሳይበርዙ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ጋዜጠኞች እና ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችን የማሳደዱ ርምጃ መቀጠሉን፤ የፀጥታ አስከባሪዎችም ለተቃዉሞ ሰለፍ በሚወጡ ሙስሊሞች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት፤ የተመለከቱ ታዛቢዎች ስልጣን ከያዙ 100 ቀናት የሆናቸዉ አዲሱ የአፍሪቃዉ ቀንድ ጠንካራ ሀገር መሪ፤ ቃል በቃል የተናገሩትን መተግበራቸዉ ነዉ ሲሉ፤ ፍርሃታቸዉን እየገለፁ ነዉ። ከመንግስት ነፃ የሆነዉና ተቀማጭነቱን በለንደን ያደረገዉ ዓለማቀፍ ፖለቲካ ጉዳዮችን በሚከታተለዉ ቢሮ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ምሁር ጃሰን ሞስሊም ይህንኑ አስከትሉዉ እንዲህ ይላሉ « የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት መለየት በኢትዮጵያ የፖለቲካዉን ሁኔታ አልቀየረዉም። ለምሳሌ ሃሳብን በነጻ መግለፅ ሆነ ምርጫን በሚመለከት፤ የተሻለ ነገር አላመጣም። ይህ ፖለቲካዊ አካሄድ ከ1997 ዓ,ም ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ነዉ። አመራሩን ጠበቅ እያደረገ ተቃዉሞ ሲበዛበት ደግሞ በትንሹ ለቀቅ በማድረግ፤ ሁኔታዉን እያረጋጋ አስተዳደሩን ቀጥሎአል። ይህ ዘዴ አሁንም ሳይለወጥ እየተሰራበት ነዉ»

አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 06.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/17Etk
 • ቀን 06.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/17Etk