የጊኔ ቢሳው ጊዚያዊ ሁኔታ | የጋዜጦች አምድ | DW | 16.10.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የጊኔ ቢሳው ጊዚያዊ ሁኔታ

የቅኝ ገዢዋ ፖርቱጋል መጨረሻ ወታደሮች ከሠላሣ ዓመታት በፊት ጊኔ ቢሳውን ለቀው ወደ ሀገራቸው ባመሩበት ጊዜ፡ ነፃነትዋን ያገኘችው ይህችው ንዑስዋ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ከዚያ በቀጠሉት ዓመታት ወደ አለመረጋጋቱና ወደ ሁከቱ ማጥ ውስጥ ትወድቃለች ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ይሁንና፡ ጀነራል ቬሪሲሞ ኮሬያ ሳብር ከሦስት ሣምንታት በፊት ባለፈው መስከረም ሦስት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ኩምባ ያላን ደም ባላፋሰሰ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ባስወገዱበት ጊዜ በረጅሙ የጊኔ ቢሳው ፖለቲካዊ ቀውስ ታሪክ መጸፍ ውስጥ አንድ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ብቻ ነበር የተከፈተው። አንድ ነጥብ ሦስት ሚልዮን ሕዝብ የሚኖርባት እና በቀድሞዋ የፈረንሣይ ቅኝ ግዛት ሴኔጋልን ጊኔ መካከል የምትገኘዋ ጊኔ ቢሳው እአአ በ 1973 ዓም ነበር ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ተላቃ ነፃ መንግሥት የሆነችው። አሁንም እጅግ ድሆች ከሚባሉት የዓለም ሀገሮች መደዳ የምትቆጠረው ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር በውጭ ዕዳ ላይ ጥገኛ ስትሆን እአአ ከ 1998 እስከ 1999 ዓም ድረስ በተካሄደው የርስበርስ ጦርነት ብርቱ ጉዳት የደረሰበት ኤኮኖሚዋም እስካሁን ገና አላገገመም። ከጥቂት ሣምንታት በፊት በዚችው ሀገር የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት፡ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን ባጠቃላይ ከማውገዝ ወደ ኋላ ብሎ የማያውቀውን ዓለም አቀፉን ኅብረተ ሰብ ቅር ቢያሰኝም፡ የአመራር ችሎታ በተጓደለባትና በምግባረ ብልሹነት በተነከረችው ጊኔ ቢሳው ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት መነሣቱ እንደማይቀር ብዙ የፖለቲካ ታዛቢዎች ተንብየው ስለነበር ይኸው የተጠበቀ ሂደት የሀገሪቱን ነዋሪዎችም ሆነ ሌላውን ዓለም አላስገረመም። የጊኔ ቢሳው ሁኔታ ከብዙ ጊዜ ወዲህ ያሳሰባቸው የፖርቱጋል ቋንቋ ተናጋሪዎቹ ሀገሮች አንጎላ፡ ኬፕ ቬርዴ፡ ብራዚል፡ ጊኔ ቢሳው፡ ሳዎ ቶሜና ፕሪንቺፔ፡ ሞዛምቢክ፡ እንዲሁም ምሥራቅ ቲሞር የሚጠቃለሉበት ማኅበረ ሕዝብ በጊኔ ቢሳው ውስጥ ለውስጥ እየተብላላ የተገኘው ውጥረት ፈንድቶ ወደ መፈንቅለ መንግሥት ከመቀየሩ በፊት መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የምሥራቅ ቲሞር ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ራሞስ ሆርታን ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ በሸምጋይነት ወደዚችው ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ልኮ ነበር።

በፖለቲካው ዓለም አንዳችም ታዋቂነት ያልነበራቸው ኩምባ ያላ እአአ በ 2000 ዓም በጊኔ ቢሳው በተካሄደ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በሀገሪቱ እአአ ከ 1961 እስከ 1973 ዓም ድረስ በፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ አንፃር የብረቱን ትግል ያካሄደውንና በምሕፃሩ ፔአኢዤሴ የሚባለውን ጠንካራውን የጊኔ ቢሳው እና ኬፕ ቬርዴ የመላ አፍሪቃውያን ነፃነት ፓርቲን ዕጩ በማሸነፍ የሀገሪቱን አመራር ያዙ። ኩምባ ያላ እአአ በ 1998 ዓም ያቋቋሙት እና በጊኔ ቢሳው ያለውን የትልቁን የባላንታ ጎሣ ድጋፍ ያገኘውን የ “ሶሻል ረኖቬሽን ፓርቲ “ ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ከመደረጉ ከአንድ ዓመት በፊት በተደረገው ምክር ቤታዊው ምርጫ ላይ ፔአኢዤሴን በማሸነፍ ይኸው ፓርቲ በምክር ቤት ውስጥ ለሀያ ስድስት ዓመት ይዞት የነበረውን የብዙኃኑን ድምፅ አሳጥቶታል። ይሁን እንጂ፡ ኩምባ ያላ ሰባ ሁለት ከመቶ የመራጩን ድምፅ አግኝተው የመሪነቱን ሥልጣን ከያዙ በኋላ፡ በዴሞክራሲያዊው አመራር ፈንታ የጎሣ ፖለቲካን በማራመድና ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን በማስፋፋት ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አራት ጠቅላይ ሚንስትሮችን ቀያየሩ፤ በካቢኔውም ውስጥ በተደጋጋሚ ሹም ሽር አካሄዱ፤ ከፍተኛ የሀገሪቱ ሥልጣን በጠቅላላ ያህሉ በባላንታ ጎሣ አባላት እንዲያዙ በማድረግ ዴሞክራሢያዊውን አሠራር ረግጠዋል። የሀገሪቱን የጦር አዛዥነት ሥልጣን ብቻ ነበር የፓፓል ጎሣ አባል በሆኑት በመጨረሻው መፈንቅለ መንግሥት መሪ ጀነራል ሳብር የተያዘው። ኩምባ ያላ የርሳቸውን አስተሳሰብ ያልደገፉ የላዕላይ ፍርድ ቤት ዳኞችንም ከሥራ አባረሩ፤ የፕሬሱን ነፃነትም አፈኑ። ኩምባ ያላ በጋዜጠኞች አሠራር ላይ ጥጥሩን ቁጥጥር እንዲደረግ ከማዘዛቸው ሌላ የውጭ ሀገር ጋዜጠኞችን ከሀገር አባረዋል፤ በመዲናይቱ ኮናክሪ ያለውን የፖርቱጋል ራድዮና ቴሌቪዥን ጽሕፈት ቤትንም ለሁለት ወራት ዘግተው እንደነበርም ይታወሳል። ኩምባ ያላ ጎረቤት ጋምቢያን ለመውረርና የጊኔ ቢሳው ዋነኛ ገንዘብ አበዳሪ ከሆነችው ከፖርቱጋልም ጋር ያለውን የሀገራቸውን ግንኙነት ለማቋረጥም ዝተው እንደነበር አይዘነጋም።

ከ 2000 እስከ 2003 ዓም ድረስ የታየውን ሂደት በቦታው በመገኘት የታዘቡት እና ኩምባ ያላ ሀገሪቱን ሥርዓተ ዴሞክራሲ በሚፈቅደው መንገድ እንዲያስተዳድሩ ለማግባባት የሞከሩት ራሞስ ሆርታ በሁኔታው መበላሸት ተስፋ ቆርጠው ነበር የተመለሱት። የምሥራቅ ቲሞር ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከጊኔ ቢሳው ከተመለሱ በኋላ ለፖርቱጋልኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገሮች ማኅበረ ሕዝብ ባቀረቡት ዘገባ ላይ ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊው መንግሥት እንደሌለ ነበር ያስታወቁት። የጊኔ ቢሳውን ሁኔታ በቅርብ የሚያውቀው ይኸው ማኅበረ ሕዝብ፡ በምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማኅበር፡ ኤኮዋስና በተ መ ድ አንፃር ያለፈው መስከረም መፈንቅለ መንግሥት ቅር እንዳሰኘው በመግለፅ ድርጊቱን ወዲያውኑ አውግዞዋል። የዓለም ኃይል መንግሥታት አምባገነን መሪዎች የሚያስተዳድሩዋቸውን ለይስሙላ የተቋቋሙትን ዴሞክራሲዎችን እንደሚደግፉ ያመለከቱት አንድ የአንጎላ የታሪክ ምሁር ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ የጊኔ ፕሬዚደንት ኩምባ ያላ በሥልጣናቸው አላግባብ ሲጠቀሙና ሕዝባቸውን ሲጨቁኑ እያየ በቸልታ ያለፈበት ድርጊት፡ ያላ የሀገራቸውን ሕገ መንግሥት እንዲጥሱና ምክር ቤቱንም እንዲበትኑ አበረታቶዋቸዋል ሲሉ ወቅሰዋል። በዚሁ ጊዜ በጊኔ ቢሳው የነበሩት የውጭ ሀገር አምባሳደሮች ርዕሰ ብሔሩ ሕገ መንግውቱን መልሰው እንዲተክሉ ሳያሳስቡ አላለፉም ነበር። ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ሥልጣን ኮርቻ ለመጨበጫ ብቻ እስከዋሉና የኋላ ኋላም ሕዝብን፡ ብሎም፡ የተቃውሞ ቡድኖችን ለመጨቆኛና የፕሬስ ነፃነትን ለማፈኛ እስካገለገሉ ድረስ ሕዝቦች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮላቸውና ብልፅግና አግኝተው የሚኖሩበት ምኞታቸው ምኝ ብቻ ሆኖ ይቀራል ማለት ነው። ካለፉት ሠላሣ ዓመታት ወዲህ ሁከት ተቋርጦ በማያውቅባት ጊኔ ቢሳው ውስጥ እአአ በ 1973 ዓም በአክራሪ የቀኝ ክንፍ የጦር መኮንን አክራሪ የተመራ የቅኝ ገዢዋ ፖሉጋል ባህር ኃይል ቡድን የነፃነት ትግል መሪ የነበሩትን አሚልካር ካብራልን በመዲናይቱ ኮናክሪ ገደለ። በዚያው ዓመት ጊኔ ቢሳው ነፃነትዋን ካገኘች በኋላ የአሚልካር ካብራል ወንድም ሉዊስ ካብራል፡ እአአ በ 1980 ዓም በጀነራል ዦአኦ ቤርናርዶ ቪየራ እስከተወገዱ ድረስ፡ ሀገሪቱን በፕሬዚደንትነት መሩ። ከጥቂት ሣምንታት በፊት በሊዝበን ፖርቱጋል የተሰበሰቡት በውጭ ሀገሮች የሚኖሩ የጊኔ ቢሳው ተወላጆች እንዳስታወቁት፡ በእነዚሁ የሉዊስ ካብራል ሰባት የሥልጣን ዓመታት ብቻ ነበር ጊኔ ቢሳው ውስጥ ሐቀኛው የሰላም ጊዜ የታየው። በምግባረ ብልሹ አመራራቸው ይታወቁ የነበሩት ጀነራል ቪየራ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ምንም እንኳን ፈረንሣይ የፊናንሱን ድጋፍ፡ ሴኔጋል ደግሞ የጦሩን ርዳታ ቢያቀርቡላቸውም፡ በአንሱማኔ ማኔ ከሥልጣን ተወግደው በወቅቱ ፖርቱጋል ውስጥ በግዞት ይኖራሉ። ከሦስት ዓ,መት በፊት የሀገሪቱ ፕሬዚደንትሪ ሆነው የተመረጡት ኩምባ ያላ የቀድሞውን መሪ አንሱማኔን ካስገደሉ በኋላ ነበር አሁን ከሥልጣን ያወረዱዋቸውን ጀነራል ሳብርን የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ አድርገው የሾሙት።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጀነራል ሳብር አሁን ባለተቋሙን ኤንሪኬ ፔርየራ ሮዛን የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት፡ የባላንታ ጎሣ ተወላጁን አርቱር ዛኔን ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው ሠይመዋል። የዛኤን ሹመት ግን የተቃውሞው ወገን የኩምባ ያላ አመራር እንደቀጠለ ነው የተመለከተው። ይሁንና፡ የጊኔ ቢሳው ዜጎች የባላንታ፡ የፓፔል፡ የማንዲንካ ወይም የፉላኒ ጎሣ እያሉ ልዩነት በመፍጠር ፈንታ፡ የሀገራቸውን የወደፊት ዕጣ የሚስተካከልበትን ዘዴ ባንድነት ቢያፈላልጉ መልካም እንደሚሆን የፖለቲካ ታዛቢዎች ጠቁመዋል። ይህ ገሀድ ካልሆነ ግን ጊኔ ቢሳው ውስጥ ምስቅልቅሉ ሁኔታ የሚነሣበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ነው ታኣዛቢዎቹ ያስጠነቀቁት።