የገና ዛፍ እና የገና አባት ታሪክ | ባህል | DW | 27.12.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ባህል

የገና ዛፍ እና የገና አባት ታሪክ

በጀርመናዉያን ዘንድ የቤተሰብ በዓል የሚባለዉ እና እጅግ ተወዳጁ የልደት በዓል፤ የገና ገበያን ይዞ የገና ዛፍን አስከትሎ የገና አባትን ስጦታ አሸክሞ በመምጣቱ ነዉ የሚታወቀዉ።

default

በኑረንበርግ የኢትዮጳያዉያን ማህበር

የጎርጎረሳዉያኑን ቀመር በሚከተሉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የልደት በዓል ካሳለፍነዉ ሰኞ ምሽት ጀምሮ እስከ ረቡዕ 26 12 2012 ደረስ በደማቅ ሁኔታ ተክብሮ በቀጣይ የጎርጎረሳዉያኑን 2013 አዲስ ዓመት ለመቀበል ሽርጉዱ ቀጥሎአል። በአብዛኛዉ የዓለም ክፍል በተለይም በምዕራባዉያኑ ዘንድ የገናን በዓል ለመቀበል ዝግጅቱ የሚጀምረዉ ከወራት ጀምሮ ነዉ። በተለይ በጀርመናዉያን ዘንድ የቤተሰብ በዓል የሚባለዉ እና እጅግ ተወዳጁ የልደት በዓል፤ የገና ገበያን ይዞ የገና ዛፍን አስከትሎ የገና አባትን ስጦታ አሸክሞ በመምጣቱ ነዉ የሚታወቀዉ። በእለቱ መሰናዶአችን የገና ዛፍ አመጣጡን የገና አባትንንና የጀርመናዉያንን የገና በዓል አከባበር እንቃኛለን።

በምዕራቡ ዓለም በልደት በዓል ሃብታምም ሆነ ደሃዉ ወዳጅ ዘመዱን የሚያስታዉስበት ስጦታ በመሰጣታት ፍቅሩን የሚለዋወጥበት እና የሚገላለጽበት ትልቅ ዓዉዳመት ነዉ። በጀርመን በዓሉ የሚከበረዉ በአዉሮጳዉያኑ ታህሳስ 24 ምሽት ጀምሮ ሲሆን፤ በነጋታዉ ታህሳስ 24 ቀዳማዊ ገና ታህሳስ 25 ቀንን ደግሞ ዳግማዊ ገና ሲሉ በተከታታይ ቀናት ከቤተሰብ ጋር በጋራና በእርጋታ ያከብሩታል። ጀርመናዉያን በገና በዓል አከባበር ከሌሎች አዉሮጳዉያን የሚለዩት ደግሞ፤ ያዉ ከአራት ሳምንታት ጀምሮ በዓሉ እስከሚከበርበት እስከ ታህሳስ 24 ቀን ድረስ፤ በሚያቆሙት በገና ገበያቸዉ እና፤ በቀረፋ በቅርንፉድ በተቀመመዉ በተፈላዉ በወይን መጠጣቸዉ ነዉ።

ቀይ ልብስ የለበሰዉ ባለ ነጭ ሪዛሙ እና ወፍራሙ የገና አባትም በአጋዘን በሚጎተተዉ የበረዶ ጋሪ ተሳፍሮ በጢስ ማዉጫ በኩል ወደቤት ዘልቆ በጆንያ ሙሉ የተሸከመዉን ስጦታ አሰቀምጦ መሄዱ በመነገሩም፤ በተለይ ህጻናት የልደትን መምጣት እጅግ በጉጉት ነዉ የሚጠብቁት። እዚህ በኑርንበርግ የኢትዮጳያዉያን የባህል ማህበር ኢትዮጳያዉያን ህጻናት የሀገሪዉን ባህል እንዲተዋወቁ ልዩ ዝግጅት እንደሚያደርጉ በዝያዉ በኑረንበርግ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሱ ለገሰ ገልጸዉልናል።

ግዜዉ እየተጣደፈ ቀናት ቀናትን እየገፈታተሩ፤ የዓመቱ መጨረሻ እየተቃረበ ሲሄድ፤ ጀርመናዉያን፣ ልጅ ለአባት፤ አባት ለሚስት፤ ሚስት ለወንድም ለእህት፤ ለልደት በዓል የሚሰጠዉን ስጦታ ለመግዛት በየመደብሩ ሲሯሯጡ ግዜ፤ የሌለዉም በኤሌክትሮኒክሱ መገናኛ በኢንተርኔት በመደገፍ የሚፈለገዉን እቃ በስሙ እቤቱ ድረስ እንዲመጣለት በማዘዝ ለበዓሉ ይዘጋጃሉ። የእቃ መሸጫ መደብሮችም፤ ከታህሳስ መጀመርያ ጀምሮ በገብያተኞች ተጨናንቀዉ ነዉ የሚታዩት። ዓመቱን ሙሉ በስራ ሌት ከቀን ፊቱ ሳይፈታ ሲሮጥ የከረመዉ ጀርመናዊ ሁሉ የገና በዓል ጥሩ ምኞትን ሲቸር ፈገግታን ሲለግስ ደግነት ሲያበዛ ሲያጋጥም ምነዉ ሁሌ ልደት በሆነ ያሰኛል። በበርሊን ከ 2o ዓመት በላይ ነዋሪ የሆኑት አቶ መስፍን አማረ ዘንድሮ የልደትን በዓል ያከበሩት ከቤተሰቦቻቸዉና ከአሜሪካ ለጉብኝት ከመጣዉጓደኛቸዉ ጋር ነዉ።

በሀገራችን ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ እንደሚባለዉ ጀርመናዉያንም ለገና ያልሆነ ብለዉ ባላቸዉ ነገር ሁሉ በበዓሉ ወቅት ይቸራሉ። በጋራ በፍቅር ማዕድ ይቀርባሉ፤ አብዛኞች ወደ አምላካቸዉ ጸሎትን ያደርሳሉ፤ ቤተስክያን ይሳለማሉ። በምዕራባዉያኑ በተለይም በጀርመን የልደት በዓልን ዋንኛ አድማቂዉ የገና ዛፍ ነዉ። እንደ ገና ገበያዉ ሁሉ ክብረ በዓሉ ከመቃረቡ ከሶስት አራት ሳምንት ጀምሮ በየትላልቅ አደባባዮች እና መደብሮች እንዲሁም በመኖርያ ቤቶች የገና ዛፍ ማልት በልዩ ልዩ ህብረ ቀለሞች የሸበረቁ የጥድ ዛፎች ይቆማሉ። ታድያ ስለ ገና ዛፍ በወጣዉ የመረጃ ማሰባሰብያ፤ በየዓመቱ ጀርመናዉያን በገና በዓል 16 ሚሊዮን የጥድ ዛፍ ለገና በዓል ማሸብረቅያ ይጠቀማሉ። የገና ዛፍ ባህል መነሻዉ ከዚሁ ከአዉሮጳ በተለይም ጀርመን እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። በዛፉ ላይም የሚሰቀለዉ መብራትና ልዪ ልዩ ቀለማትን ያዘለዉ ብልጭልጭ ማጋጌጫም የክረምቱን ድብርት ለማባረር እንደሆነ ነዉ፤ በአፈ ታሪክ የሚነገረዉ።

Weihnachtsfeier 2012 Äthiopische Gemeinde Nürnberg

በኑረንበርግ የኢትዮጳያዉያን ማህበር

ይህ ሶስት ማዕዘን ቅርፅ ያለዉ አረንጓዴዉ ዛፍ፤ በጥንት ግዜ ጀርመናዉያን ያመልኩበት እንደነበረ እና፤ ቅዱስ ቢኒፋሴ የተባሉ ቄስ ነገሩን ለማስተዉ በስላሴ ተምሳሌነት ይጠቀሙበት እንደነበረ፤ መረጃዎች ያሳያሉ። በዓመት ዉስጥ አረንጓዴነቱን ሳይለቅ የሚቆየዉን፤ የጥድ ዛፍ ጀርመናዉያን ለጌጥነት ለመጀመርያ ግዜ ጥቅም ላይ ያዋሉት በ1419 ዓም በፍርይቡርግ ከተማ አደባባይ ላይ እንደሆነ እና፤ በዛፉ ላይ ብስኩት እና ለዉዝ ተሰቅሎ እንደነበር ተዘግቦአል። ከዝያም እጎአ 1539 ዓ,ም በሽስትራስ ቡርግ በሚገኝ ካቴድራል ፊት ለፊት ፖም ማለትም ቱፋ ፍሪዎች እና ከወረቀጥ የተሰሩ ማስጌጫዎች የሸበረቀ የገና ዛፍ መታየቱም ተዘግቦአል። የገና ዛፍን በለዉዝ እና በፖም ማሸብረቅ አቅሙ ያልፈቀደልት፤ አንድ ጀርመናዊ የመስታዎት ስራ አዋቂ፤ በጎአ1847 ዓ,ም በፖም ቅርፅ ስስ መስታዎትን ሰርቶ ከሰቀለ በኃላ፤ በተለያዩ ቀለማት የሸበረቀዉ ድብልብል ጌጥ እንደ ገና ዛፍ ማጌጫ መዛመቱም ይነገራል። ይህ በገና በዓል የገና ዛፍን የማሸብረቁ ልማድ በጀርመን ጀምሮ፤ በሌሎች አዉሮጳ አገራት ተዛምቶ፤ በዩናይትድ ስቴትስም የገናን በዓል አድማቂዉ ተወዳጁ ባህል የጥድ ዛፍ ሆንዋል። የኢትዮጵያዉያን የባህል ማህበር በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ የጀርመናዉያን ገና በዓል ከገና አባት ጋር ስናከብር፤ በምናገኘዉ ግዜ ልጆቻችንን ለማስተዋወቅ ለማግባባት እንዲሁም ቤተስብንም ለማቀራብ የምናደርገዉ አጋጣሚ ነዉ ሲሉ ገልጸዉልናል።

በዘንድሮዉ ገና እዚህ አዉሮጳ በተለይ ጀርመን ከብርዱ በስተቀር፤ በረዶም ብዙም አልጣለ። ጀርመናዉያን ባሸበረቁት አረንጓዴዉ የገና ዛፍ፤ ማለት ጥድ ላይ፤ ነጭ በረዶ ዘንቦበት ሲያዩ የተሳካለት አየር ፀባይ፣ ነጩ የገና በዓል ሲሉ ይደሰታሉ። አሁን አሁን ደግሞ እዚህ በጀርመን በፍራንክፈርት ከተማ፤ በየዓመቱ በዓለም እጅግ ግዙፉ የገና ዛፍ ማሸብረቅያ ቁሳቁስ አዉደ ርዕይ መካሄድም ጀምሮአል። ጀርመናዉያን ስጦታ ከመሰጣጣት ባለፈ ወላጅ የሌላቸዉ ህጻናትን የሚረዱበት የታመመን የሚጠይቁበት የታረዙን የሚያለብሱበት የተራበን የሚያበሉበትም በዓላቸዉ ነዉ። እዚህ በሙኒክ ከተማ ነዋሪ የሆኑት በረከተአብ ስለ ገና አባት ማለት ሳንታ ክላዉስ ለህፃናት የሚነገረዉን ተረት ተረት እጅግ ከእዉነት የራቀ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። በሌላ በኩል አቶ በረከተ አብ በገና በዓል የመልካም ምኞት መግለጫ ካርዶች ላይ ባለማስተዋል የሚፃፉት የመልካም ምኞት መግለጫዎች ልናጤናቸዉ ይገባል ባይ ናቸዉ። ይኸዉም Merry Christmas ብሎ ከመፃፍ ፈንታ Merry X-mas መባሉን ስህተት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።

በገና ወቅት ስራ እና ትምህርት ቤት ስለሚዘጋ በማህበር የተደራጁ ተማሪዎች የገና አባት የሚለብሰዉን ልብስ አድርገዉ የገና አባት የሚሰራዉን አይነት ለህፃናት ስጦታ በመስጠት እንደ ስራ ይሰማራሉ። ያም ሆኖ ይህን አይነት የገና አባት እቤት ድረስ እንዲመጣ እና ህጻናትን እንዲያዝናና ከሳምንታት በፊት ቀጠሮ መያዝ እና መመዝግብ ያስፈልጋል። የገና አባት ለህጻናቱ የሚያበረክተዉን ስጦታም፤ የህጻናቱ ቤተሰቦች እንደልጆቻቸዉ ምኞት ገዝተዉ ቀደም ብለዉ ለገና አባት ይሰጣሉ።

Weihnachtsmarkt in Stuttgart

የጀርመኑ የገና ገበያ

ሌላዉ በ18 ኛዉ ክፍለ ዘመን በጀርመን የገና በዓል ማስዋብያ ሆኖ በእጅጉ እንደተስፋፋ የሚነገርለት የጥድ ዛፍ በአሁኑ ወቅት ምርቱ ለበርካታ አዉሮጳዉያን አገራት ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ ሆንዋል። ከ 20 እስከ 120 ይሮ የሚያወጣዉ አንድ ለገና በዓል ማስዋብያ የሚዉለዉ የጥድ ዛፍ፤ በተለይ ዴንማርክ እና ጀርመን በአዉሮጳ ከፍተኛ አምራች እና ለዉጭ ንግድ አቅራቢ መሆናቸዉ ተዘግቦአል። ዓመት ዓመት ያድርሰን እያልኩ የለቱን ቅንብሪን በማጠቃለል፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩትን ባህላዊ የገና አከባበር የምታዉቁትን እንድታካፍሉን በመጠየቅ እሰናበታችሁ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 27.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/179bW
 • ቀን 27.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/179bW