የጀርመን የቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ በአይቮሪኮስት | የጋዜጦች አምድ | DW | 07.02.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የጀርመን የቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ በአይቮሪኮስት

እ.አ.አ. መስከረም 2002 ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ወዲህ አይቮሪኮስት ያጋጠማት የፖለቲካ ቀውስ ካስከተላቸው ችግሮች አንዱ የምግብ እጥረት ነው።

በምግብ እጥረት ምክንያት አይቮሪኮስት ሩዝ ከውጭ ማስገባት ጀምራ ነበር።ያም ሆኖ ገበሬው ቤተሰቡን መመገብ እከማይችልበት ደረጃ ላይ ነበር የደረሰው።
አሁን ግን በምህፃሩ ጂ.ቲ.ዜድ እየተባለ በሚጠራው የጀርመን የቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት እገዛ የአይቮሪኮስት ገበሬዎች በዘመናዊ መንገድ ሩዝ ማምረት መጀመራቸው ችግራቸውን እያቃለለላቸው ነው።ገበሬዎቹ ባገኙት የቴክኒክ ድጋፍ በአመት ሁለት ጊዜ የሩዝ ምርት ያስገባሉ።በዚህም ቤተሰባቸውን ከመመገብ አልፈው ቀሪውን ምርት ለገበያ እያቀረቡም ተጠቃሚም ሆነዋል።የጥጥ ምርት ዋጋ የወረደባቸው አብዛኛዎቹ የጥጥ አምራቾችም አሁን ፊታቸውን ወደ ሩዝ እያዞሩ ነው።ይህ ሁኔታም በሀገሪቱ ያንዣበበውን ረሀብ ለመቅዋቅዋም እንዲሁም በገፍ ይገባ የነብረው የውጭ ሩዝ መጠን እንዲቀንስ ትልቅ እገዛ አድርጎዋል።
አንድ በሩዝ ምርት የተለየ እውቀት ያላቸው ምሁር እንዳስረዱት በአይቮሪኮስት ሀያ ስምንት ዐይነት ሩዝ ይመረታል። ከአይቮሪኮስት ግዛት አጠቃላይ የሩዝ ምርትም ምእራባዊው ተራራማ ክፍል ሀምሳ አንድ ነጥብ አራት በመቶ የሩዝ ምርት ድርሻ አለው።በሰሜኑ ክፍል ሀያ ነጥብ አምስት በመቶ በመሀል አገር አስራ አምስት ነጥብ ሶስት በመቶ፣በደቡብ ዘጠኝ ነጥብ አምስት እንዲሁም በምስራቅ ሶስት ነጥብ ሁለት በመትኦ ሩዝ ይመረታል።
በአይቮሪኮስት እንዲህ በስፋት የሚገኘው ሩዝ በዘላቂነት በብዛትና በጥራት እንዳይመረት እንቅፋት የሆኑ በርካታ ችግሮች አሉ።ከመካከላቸው የሞቃታማው አካባቢ ረሀብ፣ የተራራማው ክፍል የአፈር መሽርሸር ፣እንዲሁም አረም ዋነኞቹ ናቸው።ከዚህ ሌላ የዘር አቅርቦት እጥረት፣እንዲሁም የሩዝ አመራረትን የተመለከተ ግልፅ ፖሊሲ አለመኖሩና አምራቾቹም በሚገባ አለመደራጀታቸው ችግሩን አባብሶታል።
በነዚህ የተለያዩ ችግሮች የተተበተበውን የአይቮሪኮስት ኋላቀር አመራረት በዘመናዊና በቀላል ዘዴ ለመተካት ጂ.ቲ.ዜድ የሰጠው የቴክኒክ ድጋፍ ግን አሁን የአብዛኛውን የሩዝ አምራች ገበሬ ችግር አቃሎታል።ድርጅቱ በመካከለኛውና በሰሜን አይቮሪኮስት መልሰው ለተቅዋቅዋሙ በመስኖ ለሚለሙ የሩዝ እርሻዎች ውሀ ለሚያቀርቡ ሀያ አምስት ጣቢያዎች የሰጠው ጥገና ተጨባጭ ለውጥ አምጥቶዋል።እንዲሁም በነዚህ አካባቢዎች ጂ.ቲ.ዜድ ያሰራቸው መጋዘኖችም ያበረከቱት አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም።ከዚህ ቀደም በአማፅያን ይዞታ ስር የነበሩት በሰሜንና በምእራብ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙት እርሻዎች በጂ.ቲ.ዜድ እገዛ መልሰው መቅዋቅዋም ችለዋል።ይህምለገበሬው ትልቅ እፎይታ ነው።ባለፉት ሶስት ዐመታት በድርጅቱ የቴክኒክ አማካሪዎች ጥረት በተለይ ድህነት የሚያጠቃው ህዝብ በሚያመዝንባት ሰሜናዊ አይቮሪኮስት ከሶስት ሺህ ሄክታር በላይ እርሻ መልሶ ለምቶዋል።በነዚህ አካባቢዎች የጂ.ቲ.ዜድ የቴክኒክ እገዛ ፍሬ እየታየ ነው።እንደ አይቮሪኮስት የልማት ትብብር ስልጠና ቢሮ የሩዝ አመራረት ዘዴ በመሻሻሉ የሰሜን አይቮሪኮስት ገበሬ ከመስኖ እርሻ በአመት ሁለት ጊዜ ሃያ ሰባት ሺህ ቶን ሩዝ ያስገባል።ገበሬውን ካንዣበበበት የረሀብ አደጋ ያወጣው የጂቲዜድ እገዛ ለአንዳንድ የአይቮሪኮስት ገበሬዎች እፎይታ ቢሰጥም አሁንም ቢሆን በዚህ መስክ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው አጥኝዎች የሚመክሩት።