የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ለደቡብ አፍሪቃዊቷ | አፍሪቃ | DW | 26.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ለደቡብ አፍሪቃዊቷ

ለብዙዎች መከታ ሆነው ቆይተዋል። በርካቶች ያገራቸው ሰዎች ከልብ ያፈቅሯቸዋል።  ለሕገ-መንግሥቱ ጠበቃ ሆነው በመሟገት ሙስናን አጥብቀው ታግለዋል፤ ደቡብ አፍሪቃዊቷ ዳኛ ቱሊሲሊ ማዶንሲላ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:21

የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ለደቡብ አፍሪቃዊቷ

ቱሊሲሊ ማዶንሲላ ለሰው ልጆች መብት በመሟገት ላበረከቱት አስተዋጽዖ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ሽልማቶች በቅተዋል። ረቡዕ ኅዳር 14 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. የጀርመን አፍሪቃ ተቋም የዘንድሮ ሽልማት የተሰጠውም ለእኚሁ የ54 ዓመቷ ደቡብ አፍሪቃዊት ነው። ቱሊ ማዶንሲላ በደቡብ አፍሪቃ «የሕዝብ ጥበቃ» የተሰኘውን የእምባ ጠባቂ ተቋም እስከ ባለፈው ወር ድረስ ሲመሩ ቆይተዋል። ተቋሙን ለሰባት ዓመታት መርተዋል።

በጠላቶቻቸው ዘንድ የአሜሪካው «ሲ አይ ኤ ሠላይ» ተብለው ተወርፈዋል። «ሴትዮዋ ለዝና ሟች ናቸው» ሲሉም የሚተቿቸው አሉ። «አስቀያሚ ደፍጣጣ» እያሉ የስድብ ናዳ የሚያወርዱባቸው ባለሥልጣናትም አልታጡም። ሴትዮዋ ግን እንደ ብረት የጠነከሩ፣ ከአቋማቸው ውልፊት የማይሉ፣ ታታሪ ናቸው። የደቡብ አፍሪቃን ሕገ-መንግሥት ለማስተግበር ምንም ይምጣ ምን ይጋፈጣሉ። ሙስናን አጥብቀው ይታገላሉ።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2009 ዓም በያኔው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ  የሕዝብ እንባ ጠባቂ ከተሰኙበት ጊዜ አንስቶ በራቸው ለማንኛውም የደቡብ አፍሪቃ ዜጋ ክፍት ነው። ለዚህ የዓመታት ተጋድሎዋቸውም የጀርመን አፍሪቃ ተቋም የዘንድሮ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። ፎልከር ፋይግል የሽልማት ተቋሙ የዳኞች ሊቀመንበር ናቸው። ቱሊሲሊ ማዶንሲላን  እንዲህ ያወድሷቸዋል።

«ቱሊሲሊ ማዶንሲላ እንዲያ ጫና እና ዛቻ እየደረሰባቸው እንኳ ደቡብ አፍሪቃውያን ዜጎች በድኅረ-አፓርታይድያረቀቁትን ሕገ-መንግሥት ከማስጠበቅ ተግባራቸው ማንም ሊያስተጓጉላቸው አልቻለም።  የሁሉም የጋራ የሆነች፤ ነፃ እና መድልዎ የሌለባት ደቡብ አፍሪቃን በማስጠበቅ ልዩ እና ድንቅ የሆኑ ታታሪ ግለሰብ ናቸው።»

ለሰባት ዓመታት የእንባ ጥበቃ ሥራቸው ቱሊሲሊ ማዶንሲላን ደቡብ አፍሪቃውያን የሀገራቸው ብሔራዊ ጀግና ሲሉ ያሞካሿቸዋል። የቀድሞ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማን እና ከፍተኛ ባለሥላናቶቻቸውን ሲመረምሩ ፈጽሞ የማይታክቱ ነበሩ። ፕሬዚዳንቱ ከሕዝቡ የተሰበሰበውን የግብር ገንዘብ ለግል ቪላቸው መገንቢያ ተጠቅመውበታል ሲሉ ከሰዋቸዋል። ሴትዮዋ ማንንም ቢሆን ፈጽሞ የሚፈሩ አይደሉም። የሀገሪቱ ከፍተኛ የፖሊስ አመራር ሳይቀሩ ጉዳያቸው እሳቸው ጽ/ቤት ቀርቦ ታይቷል። በጄኮብ ዙማ እና እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆነው የናጠጠው የጉፕታኦፈን ኩባንያ ቤተሰብ መካከል ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረ የሚገልጥ ሠነድም ለአደባባይ አብቅተዋል።

የቀድሞውን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በተደጋጋሚ በአደባባይ ሞግተዋል። የኩባንያው የአንድ ቤተሰብ አባላት የሚንስቴር ሥልጣንን በመቆናጠጥ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ሳይጠቀሙ እንዳልቀሩም ጠቁመዋል። የጀርመን የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኖርበርት ላሜርት

«በጀርመን ታሪክ እንኳ ዲሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት ብቻውን ሙስናን ለማስወገድ እና በሥልጣን መባለግን ለማስቀረት ዋስትና ሊሆን እንደማይችል ዕናውቃለን። ያንን በንቃት መከታተል፣ መቆጣጠር የሚቻለው በሌሎች መሥሪያ ቤቶች እና ተቋማት ነው። ቢቻል የሲቪል ማኅበረሰቡን ማጠናከር እጅግ ወሳኝ ነው። ለዚያ ደግሞ ብዙዎች በሌሉበት ወይዘሮ ቱሊሲሊ ማዶንሲላ መልካም ተምሳሌት ናቸው።»

ብዙዎች በሌሉበት ቱሊሲሊ ማዶንሲላ በድፍረት ሙስናን ታግለዋል። በድፍረት ባለሥልጣናቱን ሕግ ፉት አቅርበዋል። በብዙ የአፍሪቃ ሃገራት ስም ብቻ ሆኖ የቀረ የይስሙላ ሳይሆን የምር «እምባ ጠባቂነታቸውን» አስመስክረዋል። ይኽ ድፍረታቸውም ነው በመላው ዓለም ለበርካታ ሽልማት ያበቃቸው።

ሽልማት በአጠቃላይ ለቱሊ ማዶንሲላ የዕለት ተዕለት ክስተት ይመስላል። የዩናይትድ ስቴትሱ የንግድ መጽሄት ፎርቢስ ያለፈው ዓመት  ተጽዕኖ ፈጣሪ የዓመቱ ሰው ሲል ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቱሊሲሊን ሸልሟል። «በፍትሕ ስም  ለፈጸሙት ተግባራቸው» ሲልም ነው ፎርቢስ ደቡብ አፍሪቃዊቷን የሸለመው።

ቱሊሲሊ ማዶንሲላን የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ተቋም የሰጣቸው ሽልማት ለሳቸው ብዙ ትርጉም እንዳለው ገልጠዋል። «ከምንም በላይ ግንይላሉ።

«ሽልማቱ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው። ከምንም በላይ ግን የጀርመን ሕዝብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚሆነው ነገር ቁብ እንዳለው ማሳያ ነው። የሰው ልጅ እርስ በእርሱ የተጣመረ መሆኑን ተረድተዋል። አንድ ቦታ ፍትሕ ሲዛባ ሌላ ቦታ ሠላም ሊኖር አይችልመም። አፍሪቃ ውስጥ ችግር ካለ፤ ይህ ችግር የጀርመን ሕዝብን ሊጎዳ ይችላል»

የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚንሥት ቫልተር ሽታይንማየር ደቡብ አፍሪቃዊቷ የፍትኅ ተሟጋች ቱሊሲሊ ማዶንሲላን በጽሑፍ መልእክታቸው አወድሰዋል። «ውሳኔ የመስጠት የተረጋጋ ብቃታቸው ተዓማኒነትን ፈጥሯል፤ ብዙዎችንም አጀግኗል። ደፋር በመሆናቸውም በዚህ የሥራ ድርሻ የመጀመሪያ ሴት ሆነው ብዙዎች የሚያንገራግሩትን ተጋፍጠው አጋልጠዋል። ለእያንዳንዱ ግለሰብም ድምጽ ሆነዋል። የድሆች ጠበቃም ነበሩ»  ሲሉ በደቡብ አፍሪቃ «የህዝብ እንባ ጠባቂነት» ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋጽዖ አድናቆታቸውን ገልጠዋል።

ቱሊሲሊ ማዶንሲላ በጀርመን አፍሪቃ ተቋም የተሰጣቸው ሽልማት ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሥራ ባልደረቦቻቸውም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

«በተለይ አብረውኝ ለሚሠሩት ባልደረቦቼ  ሽልማቱ የጀርመን ሕዝብ እና የጀርመን አፍሪቃ ተቋም ትጋታችንን በመገንዘብ የመልካም አስተዳደር ዕጦት በሚኖርበት ጊዜ  የሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ለመልካም አስተዳደር ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን በማስገንዘብ ዕውቅና እንደሰጠን ማሳያ ነው።»

ደቡብ አፍሪቃዊቷ የፍትሕ ተቆርቋሪ ቱሊሲሊ ማዶንሲላ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2018 በኋላ በደቡብ አፍሪቃ ምዕራባዊ ግዛት በሚገኘው ሽቴለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተግባራቸውን ይጀምራሉ። እዛም የማኅበረሰብ ፍትሕ ማዕከል ውስጥ ሥራ ይጀምራሉ። «የሕገ-መንግሥታችንን ህልም ዕውን ማድረግ እንሻለን» ያሉት ቱሊ ማዶንሲላ ያ ዕውን የሚሆነው «ሁሉንም ያቀፈ ማኅበረሰብ ሲፈጠር» መሆኑን ተናግረዋል። ግላዊነት እና ወገንተኝነት በበዛበት የአፍሪቃ አህጉር ለፍትሕ የሚያደርጉት ተጋድሎ ደቡብ አፍሪቃዊቷን የምንጊዜም ተወዳጅ አድርጓቸዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 

          

Audios and videos on the topic