የጀርመን መከላከያ ሠራዊት የውጊያ ተሳትፎ በአፍጋኒስታን፣ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.07.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን መከላከያ ሠራዊት የውጊያ ተሳትፎ በአፍጋኒስታን፣

የጀርመን የመከላከያ ጦር ኃይል (ቡንደስቬር)300 ወታደሮችን በማሠለፍ፣ በሰሜናዊው አፍጋኒስታን፣ ከሰሞኑ በተፋፋመ ውጊያ መሳተፍ መጀመሩ ተነግሮአል።

default

የጀርመን ወታደሮች፣ አፍጋኒስታን ውስጥ፣ በ«ፉክስ» ፈጣን ታንክ ሲጓዙ፤

በተጠቀሰው ብርቱ ውጊያ ከ300 ው ጀርመናውያን ወታደሮች ጋር ፣ 900 የአፍጋኒስታን መንግሥት ጦር ሠራዊት አባላትም መሰለፋቸው ነው የተነገረው። ጀርመንን ፣ ወደ አፍጋኒስታን ጦር እስከማዝመት ያደረሳት ምክንያት ምንድን ነው?

መስከረም 1 ቀን 1994 ዓ ም፣ አሸባሪዎች አሜሪካ ውስጥ የኒውዮርክን ሰማይ ጠቀስ መንትያ ህንጻዎች በህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላኖች በማንጎድ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ካጠፉ፣ እንዲሁም በመከላከያ ሚንስቴሩ ህንጻ (ፔንታገን) ላይ መጠነኛ ጉዳት ካደረሱ በኋላ፣ የአሸባሪዎቹን ማሰልጠኛ ጣቢያም ሆነ መሸሸጊያ ዋሻቸውን ለማውደም ዝታ የተነሣችው ዩናይትድ ስቴትስ የበቀል ክንዷን በማሳየት አፍጋኒስታንን መደብደብ ጀመረች። ተጓዳኞቹ ሁሉ መተባበር ጀመሩ። የያኔው የጀርመን መራኄ-መንግሥት ጌርሃርት ሽሮዖደር፣ አገራቸው ያለአንዳች ገደብ፣ ለትብብር ከአሜሪካ ጎን መቆሟን አስታወቁ። የህዝብ እንደራሴዎቹ ም/ቤትም(ቡንደስታኽ)፣ የጀርመን ወታደሮች፣ በሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ሥር ወደ አፍጋኒስታን እንዲዘምቱ ወሰነ። የወታደሮቹ ሥምሪት የሆነው ሆኖ፣ በህዝብ የተመረጠውን የአፍጋኒስታን መንግሥት በመደገፍ፣ የመልሶ ግንባታ ተግባር በማካሄድና ዴሞክራሲያዊ መዋቅሮችን በመዘርጋት ላይ ነበረ አትኮሮ የቆየው። የጀርመን ወታደሮች(ISAF)በሚል ምኅጻር የታወቀው ፣ የዓለም አቀፍ ደኅንነት ረዳት ኃይል( International Security Assistance Force)የተሰኘው የዘመቻ ቡድን አካል በመሆን ሲሳተፉ፣ የወታደር ቆብ ሳይደፉ የጥበቃ ቁጥጥር ያካሂዱ ነበር የያኔው የመከላከያ ሚንስትር ፔተር እሽትሩክ እንዳሉት፣ አንድን አገር በኃይል እንደተቆጣጠረ ጦር ሳይሆን እንደ ወዳጆች ለመታየት ነበረ ጥረታቸው።

«ወሳኙ ጉዳይ፣ አሜሪካውያን፣ በታሊባንና ኧል ቓኢዳ ላይ የዘመተውን ልዩ ጦር መምራታቸው ሲሆን ፣ እኛ ደግሞ፣ ሰላማዊ ተግባራት ከሚያከናወኑ የጦር አባላት ጋር ነው የምናሳተፈው።»

ይሁንና አፍጋኒስታን ውስጥ ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሂደቶች ለውጥ ማሳየታቸው፣ የጀርመንን የመሳሰሉ በመልሶ ግንባታ ላይ ተሠማርተው የነበሩ ኃይሎችም እንደ ሁኔታው የሚያስፈልጉ ተግባራትን ማከናወን ግድ ሳይሆንባቸው አልቀረም።

እ ጎ አ በ2005 ዓ ም፣ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት፣ በአፍጋኒስታን የተሠማሩትን ወታደሮች ቁጥር ወደ 3.000 ከፍ ለማድረግ መገደዱ አልቀረም። 4 ዓመታት ያህል ከሞላ ጎደል ጸጥታ ሰፍኖበት በነበረው ሰሜናዊው አፍጋኒስታን ፣ የጀርመን ወታደሮች ተደጋጋሚ ጥቃት ይሠነዘርባቸው ጀመር። ከሶሺያል ዴሞክራቱ ፓርቲ ወጥተው ፣ለማኅበራዊ ፍትኅ አማራጭ ተግባር የሚል ፓርቲ ያቋቋሙት ኦስካር ላፎንቴን ያኔ እንዲህ ነበረ ያሉት--

«ወደ መጨረሻው አካባቢ፣ አሜሪካውያን በጅምላ መደብደብ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ ብዙዎች አፍጋኒስታናውያን ቤተሰቦቻቸውን በሙሉ ያጡበት ሁኔታ ነው ያጋጠመው። እናም የበቀል እርምጃ የመውሰድ ግዴታ እንዳላባቸው ሳይሰማቸው አልቀረም። በዚህም ምክንያት ፣ ለጀርመን የመከላከያ ሠራዊት አባላት አፍጋኒስታን ውስጥ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚሠማሩበት ቅድመ-ግዴታ እንደሌለ የታወቀ ነው።»

እ ጎ አ በ2007 ዓ ም፣« ቡንደስታኽ፣» 6 ቃኚ ቶርኔዶ የጦር አኤሮፕላኖች እንዲላኩ ወሰነ። የህዝብ ነቀፌታ ጨመረ። «ቡንድስቬር፣» የመከላከያ ሠራዊቱ፣ ወሃ ለማውጣት ጉድጓድ መቆፈርና የአፍጋኒስታንን ፖሊስ ማሠልጠን ብቻ ሳይሆን በጦርነት እየተሳተፈ ነው የሚል ወቀሳም አየለ። የአሁኑ የመከላከያ ሚንስትር ፍራንትዝ ዮሰፍ ዩንግ ያኔ ያሰሙት መልእክት--

«ሰዎቹ፣ እንዲወዱን ማድረግ አለብን ይህ ነው ወሳኙ ጉዳይ። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል፣ 650 ፕሮጀክቶችን አጠናቀናል። ከንጹህ የሚጠጣ ውሃ አቅርቦት አንስቶ እስከ መንገድ፣ ሆስፒታልና መዋዕለ ኅጻናት ሥራ ያጠቃልላል። ይህ ትክክለኛ መንገድ ነው። ይህን ስልታዊ አያያዝ እንገፋበታለን። »

የሆነው ሆኖ፣ ውጊያው አየሰፋ መጥቶ ፣ ጀርመናውያኑ አልፎ -አልፎ ከታሊባኖች ጋር ተኩስ መለዋወጥ የማያመልጡት ጣጣ ሆኖ ፣ የመከላከያ ሚንስትሩ ወጊያ የሚለውን ቃል መጠቀም ግድ ሆኖባቸዋል። የጀርመናውያን ወታደሮች የመገደል ዜና ከተሰማ በኋላ፣ ዩንግ፣

የጀርመናውያኑ «የማረጋጋት ተግባር፣ መከላከልን ፣ መርዳትን ማስታረቅን እንዲሁም መዋጋትን ያጠቃልላል »ነበረ ያሉት።

በያዝነው ሐምሌ ወር፣ የጀርመን የመከላከያ ሠራዊት (ቡንድስቬር» አፍጋኒስታን ውስጥ ከመከላከል አልፎ፣ በታላባኖች ላይ የማጥቃት ዘመቻ ነው የከፈተው። አብዛኞቹ የጀርመን ፖለቲከኞች፣ ወታደሮቻቸው ከአፍጋኒስታን እንዲውጡ አይፈልጉም። ኀላፊነት የጎደለው አሠራር ይሆናል ብለው ስለሚያምኑ። ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ-ቫልተር እሽታይንማዬር---

«አፍጋኒስታን የሚያልቅላት ፣ እና ትተናት ከወጣን ነው።»

ተክሌ የኋላ/አርያም ተክሌ