የዶይቼ ቬለ የአማርኛው ስርጭት መታፈን | ኢትዮጵያ | DW | 29.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የዶይቼ ቬለ የአማርኛው ስርጭት መታፈን

የዶይቼ ቬለ የአማርኛ ስርጭት ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ  ሆን ተብሎ እየታፈነ ወይም እየታወከ መሆኑ  ተገለጸ። የመሥሪያ ቤቱ የቴክኒክ ባለሙያዎች እንደረሱበት፣ ስርጭቱ የሚታወክበት ቦታ እና የጊዜ ርዝመት የተለያየ መልክ አለው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:44
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:44 ደቂቃ

የስርጭት መታወክ

 ስርጭቱ ቀደም ባሉ ዓመታት ተመሳሳይ እወካ ደርሶበት የነበረ ሲሆን፣ የመብት ተሟጋቾች እወካውን የሚፈጽመው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው በሚል መክሰሳቸው አይዘነጋም። ዶይቸ ቬለ ይህን ችግር በተመለከተ ቅሬታውን ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያቀርብ ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
የዶይቼ ቬለ የአማርኛ ስርጭት ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ  የድምፅ መታፈን/መታወክ ወይም ጃሚንግ እንዳገጠመው የቴክኒክ ክፍል ኃላፊዎች አስታውቀዋል። እወካው መኖሩንም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አድማጮቻችንም በሚልኩልን መልዕክቶች አረጋግጠውልናል። የአማርኛዉ ዝግጅት በሚሰራጩባቸዉ የአጭር ሞገድ መስመሮች ላይ እየደረሰ ያለው መታወክ ወይም ጃሚንጉ ሆን ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን እንዳልቀረ የስርጭቱን ጥራት እና ሽፋንን የሚከታተሉት የዶይቸ ቬለ የቴክኒክ ባለሙያው ሁበርት ቻያ ገልጸዋል። 
«  ከተሞክሮ ለመናገር የምንችለው፣ ይህ ረባሽ ድምፅ ወይም እወካ በተወሰነ የስርጭቱ ወቅት ስለሆነ የሚሰማው፣ ሆን ተብሎ የሚደረግ ነው ብለን እናስባለን። ይህ እወካ በተለይ፣ ለምሳሌ ዜናን ወይም እንዲሰሙ የማይፈለጉ ዘገባዎችን ይመለከታል። »
የእወካው ዓይነት የተለያየ መልክ እንዳለው ብሎም ፣ አንዳንዴ ሙሉ በሙሉ፣ ሌላ ጊዜ አለፍ አለፍ ብሎ እንደሚቋረጥ ወይም ስርጭቱን የሚረብሽ ድምፅ እንደሚሰማበት ነው ባለሙያው ያስታወቁት። ለዚህም ባለሙያው የሚሰጡት ምክንያት፣
« የሚያውክው ወገን ስርጭቱን በጠቅላላ ወይም የተወሰነውን ክፍሉን ማወክ የሚያስችለው በቂ አቅም የለውም። ስለዚህ በርግጠኝነት ውጤታማ ለመሆን የተወሰኑ ይዘቶችን ለተወሰኑ ደቂቃዎች እየመረጠ  ያውካል። » 
የመታፈን ወይም የመታወክ እጣ ሲገጥመው የመጀመሪያው ጊዜ ያልሆነው የዶይቸ ቬለ የአማርኛው ስርጭት ካሁን ቀደም ለገጠመው አፈና ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን እንዳልቀረ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት  «ሂውመን ራይትስ ዎች» ያወጣቸው ዘገባዎችም ይህንኑ  ይጠቁማሉ።

ለተወሰነ ጊዜ ከአፈና ነፃ ሆኖ ከቆየው በኋላ አሁን  እንደገና ለገጠመው የመታፈን ችግር  ለስርጭቱ መታፈኑ ምክንያቱ በርግጠኝነት ይህ ነው ብሎ ለመናገር ባይቻልም፣  እንደ ዶይቸ ቬለ የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ ሚስተር ክላውስ ሽቴከር ግምት፣ ከጥቂት ወራት ወዲህ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተነሳው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ምክንያት ሊሆን ይችላል። 
« የኢትዮጵያ ባለስልጣን መሥሪያ ቤት ስርጭቱን እንዲያፍን ያነሳሳውን ምክንያት በተመለከተ ግምት ብቻ ነው ልንሰጥ የምንችለው። ይሁንና፣ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ከተነሳው እና ከ400 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወት ካለፈበት ግጭት በኋላ የጃሚንግ እና ሆን ተብሎ የሚደረገው የማወክ ተግባር ጨምሮዋል። እና  የስርጭቱ መታወክ በመንግሥት ጭቆና ፣ እንዲሁም፣ ተጓድሎ በሚገኘው ፖለቲካዊ ተሀድሶ ሰበብ በተለይ በወጣቱ ዘንድ ስለሚታየው ቅሬታ ከምናቀርባቸው ዘገባዎች ጋር የተያያዘ ነው ብለን እንጠረጥራለን። መንግሥት በዘገባዎቹ ደስተኛ አይደለም። ነገር ግን ይህ ሚዛናዊ የሆነ የዘገባ አቀራረብ ሥራችን አንድ አካል ነው። »
ዶይቸ ቬለ የሰሞኑን የስርጭት መታወክ/ ጃሚንግን በተመለከተ፣ ካሁን ቀደም ተመሳሳይ ችግር ሲገጥመው እንዳደረገው ሁሉ፣ አሁንም ቅሬታውን  ለኢትዮጵያ መንግሥት የማቅረብ እቅድ እንዳለው ሚስተር ክላውስ ሽቴከር ገልጸዋል። 
« በአዲስ አበባ የጀርመን አምባሳደር በተገኙበት አንድ ስብሰባ ወቅት የስርጭት አፈና ጃሚንግ ድጋሚ ሥራ ላይ እንደማይውል ከኮሚኒኬሽን ጉዳይ ሚንስቴር ዋስትና አግኝተን ነበር። እኔ እስከማውቀው ድረስ ስለ ጃሚንግ እንዲህ በግልጽ ሲነገር ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር። እና በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ የሚሰራበት ዘዴ በዚሁ አብቅቷል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ግን ይህ ቃላቸው/ዋስት አለመከበሩን ነው አሁን ያየነው። በዚህም የተነሳ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት፣ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በቅርቡ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝታቸው ወቅት ስለዚሁ ጉዳይ  ከከፍተኞቹ ባለስልጣናት ጋር አንስተው እንዲወያዩበት የመራሒተ መንግሥቷን ጽሕፈት ቤት እንጠይቃለን። የስርጭት አፈና/እወካ ከጊዜው ጋር የሚሄድ አይደለም። እኛ የኢትዮጵያንም መንግሥት ሆነ ሕዝብ ለመጉዳት አንፈልግም። ሚዛናዊ  የሆነ መረጃ ማቅረብ ብቻ ነው የምንፈልገው። እና በዚሁ ሥራችንም ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደፊት እንደማያውከን ተስፋ እናደርጋለን። »

 

አርያም ተክሌ 

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic