የዳርፉር ስደተኞችና ኦክስፋም | አፍሪቃ | DW | 15.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዳርፉር ስደተኞችና ኦክስፋም

የሱዳን ምዕራባዊ ግዛት የዳርፉር ኗሪዎች ዛሬም ከመፈናቀልና ከስደት አለመላቀቃቸዉን ነዉ በያዝነዉ ሳምንት ኦክስፋም የተሰኘዉ ግብረሰናይ ድርጅት ባወጣዉ መግለጫ ይፋ ያደረገዉ። በአካባቢዉ በሚኖሩ የአረብ ጎሳዎች መካከል በሰሜናዊ ዳርፉር ጀበል አሚር በተባለዉ አካባቢ የተካሄደዉግጭት በሺዎች የሚገመቱ ኗሪዎችን ከቤታቸዉ አፈናቅሏል።

የወርቅ ማዕድን ማዉጫ ሥፍራ መሆኑ በተነገረዉ በዚህ አካባቢ ባለፈዉ ወር ዉጊያዉ ሲካሄድም ቤቶች ፈራርሰዉ ሰብል በእሳት በመጋየቱ የረድኤት ሠራተኞች ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉትን ወገኖች መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት እየታገሉ እንደሚገኙ ኦክስፋም በመግለጫዉ አመልክቷል። የኦክስፋም ባልደረባ ሃሙዳ ካኑ እንደሚሉትም ከግጭቱ ህይወታቸዉን አትርፈዉ የተሰደዱ ወገኖች መቼ ወደፈራረሰዉ መኖሪያ ቤታቸዉና ቀያቸዉ እንደሚመለሱም አይታወቁም።

ኦክስፋም በመግለጫዉ እንዳመለከተዉም የዘንድሮዉ የአየር ሁኔታ እጅግ ቀዝቃዛ መሆኑን በመጥቀስ ለተፈናቃዮቹ የሚሆን በቂ መጠለያ እንደሌለም አመልክቷል። ይህም የበሽታዎች መዛመትና መስፋፋት ሊያስከትል እንደሚችል አሳስቧል። የድርጅቱ የሱዳን ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ኤልፋታህ ዑስማን አደም እንደሚሉትም ተጨማሪ ተፈናቃዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስጋት መኖሩን ማመልከታቸዉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ከኻርቱም ዘግቧል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ኦስማን ስለሁኔታዉ አሳሳቢነት እንዲህ ነዉ ያሉት፤

«የችግሩ መሠረታዊ ምክንያት በሁለት ጎሳዎች መካከል የተነሳ ግጭት ነዉ። በተለይ ደግሞ ጥር ወር መጀመሪያ ላይ በተጠናከረዉ ዉጊያ ምክንያት ሁኔታዉ እጅግ አስቸጋሪ ነበር። አሁን ያለዉ በግጭቱ ለተጎዱት ሰብዓዊ ርዳታ የማቅረቡ ተግዳሮት ነዉ።»

የተመድን በምንጭነት የጠቀሱት በሱዳን የኦክስፋም ዳይሬክተር ኤልፋታህ ዑስማን አደም የተፈናቀሉት አንድ መቶ ሺህ ቤተሰቦች እንደሆኑ አመልክተዋል። ሰዎቹ መፈናቀል የጀመሩትም ካለፈዉ ጥር አንስቶ እንደሆነ እና ተፈናቃዮቹ በዋናነት የምግብ፤ የንፁህ መጠጥ ዉሃና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እጥረት እንዳጋጠማቸዉም ገልፀዋል፤

«ለምሳሌ የዓለም የምግብ ድርጅት የምግብ እርዳታና ዉሃ፤ እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ስልቶችን ያቀረበ ሲሆን፤ የአካባቢ ጥበቃ ዘርፋችን በአካባቢዉ ግድብ በመኖሩ የዉሃ መጠቀሚያ አካባቢዎችን አዘጋጅቶላቸዋል፤ በዚህም በቂ ዉሃና የንፅህና መጠበቂያ ለማመቻቸት ተሞክሯል። ምክንያቱም አንዳንዶቹ ጠባብ ወይም አነስተኛ አካባቢዎች ቢሆኑም ከመጠን በላይ ብዙ ተፈናቃዮች ይገኙባቸዋል። ስለዚህ እንዲህ ባለዉ አካባቢ በቂ ዉሃም ሆነ መጸዳጃ አይገኝም። እናም ያንን ባጠቃላይ ለማሻሻል እየሠራን ነዉ።»

እነዚህ የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖች ለመርዳና የሚያስፈልጓቸዉን መሰረታዊ ነገሮች ለማቅረም ኦክስፋም በቂ አቅም እንደሌለዉም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። ችግሩን ያባባሰዉም ድርጅቱ ቀድሞ ይረዳቸዉ በነበሩ ተፈናቃዮች ላይ አዲስ መጨመራቸዉ ነዉ።

«በአካባቢዉ ከ70 ሺህ በላይ የአሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን እና የአካባቢዉን ኗሪዎች ለመርዳት ዉሃ፤ የንፅህና መጠበቂያ እና የመሳሰሉትን በማደራጀት እየሠራን ነበር። አሁን ደግሞ አዲሱ ቀዉስ ተጨማሪ ተፈናቅይና ተረጂዎችን አስከትሏል፤ ዋናዉ ፈተና ከእኛ አቅም በላይ ሳይሆን እነሱን ለመደገፍ በቂ አቅርቦት እንዴት ይገኛል የሚለዉ ነዉ። ምክንያቱም ቀደም ሲልም የምንደግፋቸዉን ሰዎች ለመርዳት እራሳችንን ዉጥረት ዉስጥ ሳንከት እየታገልን ነዉ። ስለዚህ ዋናዉ ተግዳሮት በቂ የሆነ አቅርቦት ማግኘቱ ነዉ።»

የፈረንሳይ የዜና ወኪል እንደዘገበዉ የተመድ ከ600 መቶ ቶን በላይ ምግብ እና ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለተጎዱት አካባቢዎች አቅርቧል። የድርጅቱ የሰብዓዊ እርዳታ ኮሚሽን 65ሺህ የሚሆኑት አዲስ ተፈናቃይ ወገኖች በሰሜን ዳርፉር ርቃ የምትገኘዉ ኤል ሲርፍ በተባለችዉ ከተማ መስፈራቸዉን ገልጿል። በአካባቢዉ ባለዉ ዉጊያ ምክንያትም የረድኤት ሰራተኞች ወደ ኡል ሲርፍ የግድ በአየር መጓዝ ይኖርባቸዋል፤ ይህም የሚያጓጉዙት የጭነት መጠን እንደሚወስን ተገልጿል። የልማት ተግባር ያልቃኘዉ በምዕራባዊ ሱዳን ግዛት ለዓመታት ከግጭት ያልፀዳዉ የዳርፉር አካባቢ በአረብ ጎሳዎች አመፅ፤ በሽፍቶችና በጎሳዎች ግጭት የሚታመስ ነዉ።

Audios and videos on the topic