የደ/ሱዳን የረሃብ አደጋና ስጋቱ | አፍሪቃ | DW | 27.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የደ/ሱዳን የረሃብ አደጋና ስጋቱ

በርስ በርስ ጦርነት በተመሰቃቀለችዉ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ በሚሊዮኖች የሚገመቱ ዜጎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸዉ ተገለጸ። የተመድ የዝናቡ ወቅት እየቀረበ በመጣበት በዚህ ወቅት ለእርሻ መዘጋጀት በማይታሰበብት ሁኔታ የገጠመዉ የምግብ እጥረት የከፋ ቀዉስ እንዳያስከትል አስጠንቅቋል።

የተመድ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ በጦርነትና ግጭቱ መዘዝ የተፈናቀሉ ወገኖች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸዉን ማስጠንቀቅ የጀመረዉ የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች ወደጦርነት ከገቡበት ወቅት ጀምሮ ነዉ። ከታህሳስ ወር አንስቶም ከ700,000 በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋ። በተለያዩ አካባቢዎች ለሠፈሩ ወገኖች የምግብ ርዳታ ለማድረስም ዉጊያዉ እንቅፋት እንደሆነበትም ድርጅቱ ሲያመለክት ቆይቷል። የድርጅቱ የሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ OCHA የዘመቻ ዘርፍ ኃላፊ ጆን ጊንግ የተፈናቀሉት ወገኖች በአሁኑ ወቅት ለጠኔ ተጋልጠዋል ማለት ባይቻልም ለአስከፊ የምግብ እጥረት መጋለጣቸዉን ገልጸዋል።ጊንግ አምስት ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉም አመልክተዋል። የምግብ ርዳታዉ ማስጠንቀቂያ አስቀድሞ መሰጠቱን ያመለከቱት ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የምስራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ተንታኝ አንድሩዉ አታ አሳሞሃ ምክንያቱን እንዲህ ያስረዳሉ፤

«ምክንያቱ ግጭቱ መሬቱን የማረሻዋዉን እና ለእርሻ የሚደረገዉን የዝግጅት ወቅት ማዛባቱን በማስተዋል ነዉ። እናም ከዚህ ቀደም የምግብ እጥረት የመኖሩ እዉነታን በማሰብ በግጭቱ ምክንያት በርካቶች ከቤት ንብረታቸዉ ስለተፈናቀሉ ችግሩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል በመገመት ነዉ። በአሁኑ ጊዜም በብዛት ከዩጋንዳ ይመጣ የነበረዉ የምግብ አቅርቦትም የንግድ እንቅስቃሴዉ በመስተጓጎሎ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።»

ከመንግስታቱ ድርጅት በተጨማሪም ለጉብኝት ደቡብ ሱዳን የሚገኙት የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ለወራት የቀጠለዉ ግጭት ሰብዓዊ ቀዉስ እንዳያስከትል ስጋታቸዉን ገልጸዋል። አንድሩዉ አታ አሳሞሃ ችግሩ ሳይባባስ አሁን ባለበት ደረጃ የሚሰነዘረዉ ማሳሰቢያ አዎንታዊ ነዉ ይላሉ። ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ሊያደርገዉ የሚችለዉን አስመልክተዉ ደግሞ፤

«የማምረቱ ሂደት በተስተጓጎለበት በዚህ ወቅት ሊያደርጉ የሚችሉት የእርዳታ ጥሪ ማስተላለፍና አስቀድሞ ማቀድ ነዉ።የተመድ ተቋማትም ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ርዳታዉን ለማዳረስ ግፊት ያደርጋሉ። መልካሙ ነገር ይህ የሚደረገዉ አስቀድሞ መሆኑን አዉቀናል። እናም በዚህ ተግባር የሚሳተፉት ሁሉ ዝግጅት እንዲያደርጉ በበቂ ሁኔታ አስቀድሞ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነዉ ብዬ አስባለሁ።»

በዚህም ዓለም ዓቀፉ ኅብረተብ በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት የሚታየዉን ችግር ለመቅረፍ አቅም እንዲኖረዉ ድጋፋቸዉን ሊሰጡ እንደሚገባም አመልክተዋል። ለችግሩ መፈጠርና መባባስ ምክንያት የሆነዉ የቀጠለዉ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ኃይሎች ዉጊያ መሆኑ ግልፅ ነዉ። በእነዚህ ወገኖች መካከልም የተጀመረዉ የሰላምድ ድርድር በያዝነዉ ሳምንት ዳግም ተጀምሯል። እስካሁን በተካሄደዉ ድርድር የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ማለትም IGAD ሰላም ለማዉረድም ሆነ አዲሲቱን ሀገር ለማረጋጋት ያከናወነዉ እንዴት ይገመገማል? አንድሪዉ አታ አሳሞሃ ሂደቱን በሁለት ደረጃ ከፍለዉ ይመለከቱታል፤

«እስካሁን ያለዉን በሁለት ደረጃ ከፍሎ መመልከት ይቻላል። የመጀመሪያዉ አካሄዱን ይመለከታል ተገቢዉን ሰዎች ይዘዋል ወይ የሚለዉ ነዉ። በሁለተኛዉ የማየዉ ጥቅል መፍትሄዉን ነዉም ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት የሆነ ማዕቀፍ ማየት ነበረብን። አፈፃፀሙን ስንቃኝ ድብልቅ ነገሮች ነዉ የምናገኘዉ። በአንድ ወገን ለዉጤት የሚጠቅሙ ሰዎች ይዟል በሌላ ወገን ደግሞ ዉሳኔዉን የማስፈፀም አቅም አይታይም። እናም IGAD እንደጠንካራ የአካባቢዉ ቡድን ተዋናዮቹ የተስማሙበትን እንዲያከብሩ የመግፋት አቅሙን አልተጠቀመም።»

ከIGAD አባል ድርጅቶች አንዷ ዩጋንዳ መሆኗ ግልፅ ነዉ። ሆኖም ካምፓላ የፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርን ለመደገፍ ጦሯን እዚያ ካሰማራች ሰንብታለች። የካምፓላ ወታደራዊ ኃይል እዚያ መገኘት ድርጅቱ ሰላም ለማዉረድ የሚያካሂደዉን ጥረት የማደናቀፉ ሁኔታ እንዴት ይታያል?

«እንደማስበዉ IGAD ከገጠሙት ተግዳሮቶች አንዱ ያ ነዉ። እዉነታዉ ዩጋንዳ IGAD ዉስጥ ቁልፍ ሚና አላት በዚያዉ መጠን ደግሞ በግልፅ በማጥቃት በኩል ወገን ይዛ የሳልቫኪርን አስተዳደር ለመታደግ ድጋፍ እየሰጠች ነዉ። እናም እንደሚመስለኝ ይህ የIGADን ሕጋዊነት ዝቅ የሚያደርግ ነዉ። ምክንያቱም ከማን ወገን ነዉ በሚል ከSPLM በኩል ጥያቄዎችን ያስነሳል።»

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic