የደን ምርምር ጉባኤ | ጤና እና አካባቢ | DW | 03.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የደን ምርምር ጉባኤ

የደን ሃብት ይዞታ በተለይ አፍሪቃ ዉስጥ ከህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ጋ በተገናኘ እያደር ለከፋ ሁኔታ መጋለጡን ነዉ የዘርፉ ተመራማሪዎች የሚያመለክቱት። የዓለም ዓቀፍ የደን ምርምር ድርጅት ኅብረትና ከሰሃራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ ሀገሮች

የደን ምርምር ጥምረት በጋራ ናይሮቢ ኬንያ ላይ የአካባቢዉን ደን ምርምር ጉባኤ ባለፈዉ ሳምንት አካሂደዋል። ወደ300 የዘርፉ ተመራማሪዎች የተገኙበት ይህ ጉባኤ የየመንግስታቱ ህግ አዉጭዎችና ፖሊሲ አርቃቂዎች ተስማሚ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ በማዉጣት የአየር ንብረት ለዉጥና መዘዞቹን ለመግታት እንዲተባበሩ ጠይቋል። በሌላ በኩል ጋምቤላ ዉስጥ ለሻይ ቅጠል ልማት ለዉጭ ባለሃብት የተሰጠ የተፈጥሮ ደን የተሸፈ መሬት ጣዉላ እየመረተበት እንደሆነ ይነገራል። ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ አንስቶ እስከ ዓርብ ዕለት ናይሮቢ ኬንያ የተካሄደዉ ደኖችና ዛፎች የአፍሪቃን ህዝብና ዓለምን ያገለግላሉ የሚል መልዕክቱን አስተላልፏል።

ናይሮቢ ኬንያ ላይ ለአራት ቀናት የተካሄደዉ ጉባኤ የደን ምርምር ባለሙያዎችንና ከመንግስት በኩል ደግሞ ዘርፉን የሚመለከቱ ህጎችን የሚያረቁ የፖለቲካዉን ወገን አቀራርቦ እንዳወያየ ነዉ የአፍሪቃ የደን መድረክ፣ AFF ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር ጎድዊን ኮዌሮ የገለፁት፤

«ጉባኤዉ በአንድ ወገን አብዛኞቹ በዘርፉ በርካታ ጥናት ያካሄዱና እያካሄዱ የሚገኙ ተመራማሪዎችና ምሁራን የተካተቱበት ስብስብ ሲኖረዉ፤ በሌላ በኩል የደን መርሆ ዕለት ደግሞ ደንና ከደንና የተገናኘ ህግ አዉጪዎችንና አስፈፃሚዎችን ወደጉባኤዉ አምጥቷል። አጋጣሚዉም የፖለቲካዉ ሰዎች ከተመራማሪዎች ጋ እንዲነጋገሩና ሳይንስ በፖሊስ ቀረፃዉም ሆነ ደንን የሚመለከቱ ተግባራዊ ሥራዎችን እንዴት እንደሚመለከት በጋራ እንዲያዩ አድርጓል።»

በዚህ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአርባ በላይ ከሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት የተዉጣጡ የደን ምርምር ባለሙያዎችና የዘርፉ ምሁራን ተገኝተዋል። አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሀገሮች ዉስጥ የሚገኝ የደን ሃብት ከጊዜ ወደጊዜ ለእርሻ መሬት ፍለጋ ሲባል ለምንጣሮና ጭፍጨፋ እንደሚጋለጥ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። የኢትዮጵያ የደን ይዞታ ደግሞ ለባሰ አደጋ መጋለጡ ይነገራል። በጉባኤዉ ወቅት የዘርፉ ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተዉት እንደሆን የተጠየኳቸዉ ፕሮፌሰር ኮዌሮ ችግሩ የኢትዮጵያ ብቻ እንዳልሆነ ነዉ የሚያመለክቱት። የደን መመናመንና መራቆት ጉዳይ የአብዛኛዉ የአፍሪቃ ሀገሮች ችግር እንደሆነ፤ ይህን ለመግታትም ትኩረት ሰጥተዉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አካላት እንዳሉ የገለፁት የዘርፉ ባለሙያ የደን መመናመን ችግር መንስኤዉ መሠረታዊ መፍትሄ እንደሚፈልግ ገልፀዋል፤

«ጉዳዩን ስንመለከተዉ ሰፊና የማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ልማትን የሚያካትት ነዉ፤ መነሻዉም በዋናነት ከእርሻ እንቅስቃሴዎች ጋ ይገናኝል። እናም እርሻዉ ዉጤታማ ባለመሆኑ እስከቀጠለ ድረስ ሰዎች ኑሯቸዉን ለማሸነፍም ሆነ ለእርሻ የሚሆናቸዉ ተጨማሪ መሬት ለማግኘት በደን ላይ ጥገኛ መሆናቸዉ አይቀርም። እናም በቀላሉ ደንን በይዞታነት የሚጠቀሙ አሁኑኑ ያቁሙ ማለት የሚቻልበት ነገር አይደለም ይልቁንም ከመሬትና ደንጋ የተገናኘ የኤኮኖሚ መርሆና እቅድ የሚነድፉትን ይመለከታል። በተለይም የእርሻና የከብት ርባታ ልማት፤ በጥቅሉም የመሬት ጉዳይ የሚመለከታቸዉን ማለት ነዉ። እነሱ ዉጤታማ መሆን ይኖርባቸዋል።»

እሳቸዉ እንደሚሉት በተለያዩ አካባቢዎች የደን መመናመን መኖሩ እየታየና እየተባባሱ መሆኑ ግልፅ ቢሆንም በየእርሻ ቦታቸዉ ዛፎችን በመትከል ለአካባቢያቸዉ የተሻለ ተግባራትን የሚያከናዉኑ እንዳሉ ያመለክታሉ፤ ያ ግን ደኖች በሲጠፉበት ስፍራ የአካባቢዉን የተፈጥሮ ሁኔታ ይመልሳል ማለት አይደለም፤ ፕሮፌሰር ጎድዊን ኮዌሮ፤

«በሌላ በኩል ሰዎች በእርሻ ቦታቸዉ ዛፎችን ሲተክሉ ይታያል፤ በርካታ የደን ሃብቶች ሲጠፉ በእርሻ ቦታዎች ደግሞ ዛፎች እየወጡ ነዉ። በዚህም የማገዶ እና የቤት ሥራ፤ ፍላጎታቸዉን ያሳካሉ፤ ሆኖም ግን ይህ የተፈጥሮ ደን እንደሚያደርገዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታዉን ይመልሳል ማለት አይደለም። ችግሩን በዚህ መልኩ ነዉ ማየት የሚኖርብን፤ እኛ አኳያ ካየነዉ ይህ የመላ አፍሪቃ ችግር ነዉ፤ በተጨማሪም እስያም ሆነ ላቲን አሜሪካ ዉስጥ ያለ የሚያጋጥም ችግር ነዉ።»

በተለያዩ ጊዜያት የየሀገሮችን የደን ሃብት ይዞታ የሚያሳይ የጥናት ዉጤት ይፋ ይደረጋል፤ ፕሮፌሰር ኮዌሮ እንደገለጹት ከጊዜ ወደጊዜ ይዞታዉ እቀነሰ መሄዱንም ጥናቶቹ ያሳያሉ። አንድ ጥናት ኢትዮጵያን የደን ይዞታ በሚመለከት የመረጃ እጥረት በመኖሩ ግምት ላይ የተመሠረቱ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ በትክክል ይህ ነዉ ብሎ የደኑን ይዞታ ለመግለፅ በማስቸገሩ፤ ከአጎራባች ሀገሮች ጋ በማነፃጸር ለመጥቀስ መገደዱን ይጠቁማል። ጥናቶች መጠናታቸዉ መልካም ሆኖ እያለ የተጠኑ ጥናቶች የሚያመላክቷቸዉ ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ ማገዣ ካላገኘ የጥናቱ ፋይዳ ምን ይሆን ለሚለዉ ባለሙያዉ፤ ለምርምር ተግባር መንግስታት ገንዘብ የመመደብ ልማዱ እንደሌላቸዉ፤ እነሱም ሆኑ የግሉ ዘርፍ ለዚህ ትኩረት እንደማይሰጥ በመጠቆም በሌሎች ርዳታ የተሠሩ ጥናት ዉጤትታቸዉ ቢታወቅም አስፈላጊዉ ርምጃ አይወሰድም ይላሉ፤

«ዉጤቶቹ ይታወቃሉ፤ አሁን ስለምንነጋገርባቸዉ ነገሮች እያንዳንዱ መንግስት ያዉቃል። ምስጢር አይደለም፤ ሌላዉ ቀርቶ ተራ የሚባለዉ ሰዉ ሁሉ ያዉቃል። ሁላችንም ከገጠር አካባቢዎች ነዉ የወጣነዉ፤ ከዚህ ችግር ጋ ነዉ አብረን የምንኖረዉ፤ አፍሪቃ ዉስጥ አብዛኞቹ የመንግስት ምክር ቤት አባላት ከገጠር ነዉ የሚወጡት። ዘመዶች፤ ቤተሰቦች አሏቸዉ እነሱ ራሳቸዉ እንጨት እየተቆረጠ ማገዶ በሚሆንበት በገጠሩ ምድር ነዉ የሚኖሩት። ስለዚህ ይህን ችግር ምርምርም ባይደረግ ያዉቁታል። ራሴን፤ እነዚህ ወደምክር ቤት የሚገቡ ሰዎች ለሌሎች ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ገንዘብ ሲመድቡ ይህን ችግር ለመፍታት ለምን በቂ በጀት አይመድቡም ስል እጠይቃለሁ። አፍሪቃ ዉስጥ የምናገኘዉ ችግር ይህ ነዉ። ሁሉም ሰዉ ምግብ አስፈላጊ መሆኑን ያዉቃል፤ ሆኖም ምግብን በሚመለከት አፍሪቃ ሁል ጊዜ ኪሳራ ላይ ናት። ሌሎች ሰዎችም ተመሳሳይ ጥያቄ ሊጠይቁ ይችላሉ፤ ለምንድነዉ እነዚህ የምክር ቤት አባላት የምግብ እህል ምርትን ለማሻሻል በቂ ገንዘብ የማይመድቡትና በደን ላይ ያለንን ችግር የማይቀርፉት? እናም እነዚህና መሰል ነገሮች በበርካታ ሀገሮች በጣም የታወቁ ናቸዉ።»

የደን ሃብትን ለመጠበቅ ይበጃል ያሉትን ፕሮፌሰር ኮዌሮ ሲገልፁ፤

«እርግጥ ነዉ እነዚህ ሀገሮች በሙሉ እነሱን ለመጠበቅ መመሪያዎችና ህጎች አሏቸዉ። ሆኖም እነዚህ የደን ጭፍጨፋን የሚያስቆሙ ምክንያቶች ባልተወገዱበት በአግባቡ ሊሠሩ አይችሉም። ሰዎች በድህነት መኖራቸዉ እስከጠለ ድረስ፤ ኋላ ቀር የእርሻ ስልቶችን መጠቀማቸዉን ይቀጥላሉ። እነዚህ ስልቶች ደግሞ ምርታማነት ለማሳደግ አይረዱም፤ የአፈሩን ለምነት ማሟጠጣቸዉን ይቀጥላሉ፤ ከዚያም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሰዎች ለእርሻ ሲሉ ወደሌላ አካባቢዎች ይፈልሳሉ። ምክንያቱም እነሱ የነበሩባቸዉ አካባቢዎች ሊጣበቡ እና ለምነታቸዉ ሊቀንስ ይችላል። በዚህ ሁኔታ ደግሞ አሁንም ሰዎች ደኖች ላይ ሰፍረዉ ይገኛሉ። ስለዚህ አንደኛዉ ነገር ድህነትን ማጥፋት ሲሆን በዚያዉም የእርሻ ምርታማነትን ማሳደግ፤ በተጨማሪም ለግጦሽ ከሚሆነዉ መሬት ይዞታጋ በሚመጣጠንበት ሁኔታ የከብት ርባታ ስልቱን ማሻሻል፤ አለበለዚያ በተለመደዉ ስልት መቀጠል ይሆናል። ያም የተፈጥሮ ሃብትን ማመናመንና የመሬቱን ለምነት መቀነስ ማለት ነዉ። እነዚህ ናቸዉ ችግሩን ሊቀንሱ የሚችሉት፤ ህግ ብቻዉን የሚያደርገዉ አይኖርም። ድሃ ሰዉና የተራበ ሰዉ ምግብ ያለበትን ቦታ ነዉ የሚፈልገዉ፤ ለችግሩ መፍትሄ ዛፍ መቁረጥ ከሆነ ያ ሰዉ ዛፉን ቆርጦ ለእርሱና ለቤተሰቡ የሚሆነዉን ለማምረት ወደኋላ አይልም።»

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic