1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የደቡብ ሱዳን ግጭትና የሽምግልናዉ ጥረት

ዓለም ሲያሳስብ፥ ሲያጠነቅቅ፥ ለዲፕሎማሲ ሲጠራራ፥ አፍሪቃ ጁባ ሲመላለስ፥ጁባ አስከሬኖቻን ቆጥራ፥ቀብራ ደሟን አድርቃ ሳታበቃ ቦር ተደገማለች። ድፍን የዩኒቲ ግዛት ቀጠለች። ጃግሌዬም አሰልሳለች።

የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች የቀሰቀሱትን ግጭትና ዉዝግብ በድርድር ለመፍታት የሚደረገዉ ጥረት ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።የኢትዮጵያ እና የኬንያ መሪዎች የተቀናቃኝ ሐይላት መሪዎችን ለማነጋገር ዛሬ ጠዋት ርዕሠ-ከተማ ጁባ ገብተዋል።መሪዎቹ ከጁባ እንደተመለሱ የሌሎች የምሥራቅ አፍሪቃ ሐገራት አቻዎቻቸዉን አክለዉ ናይሮቢ-ኬንያ ዉስጥ በጉዳዩ ላይ ይነጋገራሉ። ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ተፋላሚ ሐይላት ግጭቱን በድርድር እንዲፈቱ እያሳሰቡ ነዉ። ቻይና በበኩሏ የአፍሪቃ ጉዳይ ልዩ ዲፕሎማትዋን ወደ ጁባ ለመላክ መዘጋጀትዋን አስታዉቃለች። ዲፕሎማሲያዊዉ ጥረት ቢጠናከርም ተፋላሚ ሐይላት በዉጊያዉ አዉድ የበላይነትን ለመያዝ የሚያደርጉትን ዝግጅት እስካሁን ማስቆም አልቻለም።

አዲሲቱን አፍሪቃዊት ሐገር ለዘመናት ካነደደዉ የሥልጣን ሽኩቻ፥ የፖለቲካ እና የጎሳ ግጭት፥ ዉጊያ፥ ጦርነት የዶለዉን ጠብ፥ ዉዝግብ ለማስወገድ አፍሪቃዉያን ዲፕሎማቶች ሽቅብ፥ ቁልቁል ማለት የጀመሩት ጠቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነዉ። ዛሬ አስራ-ሁለተኛ ቀኑ። ቀጥሏልም።

አሜሪካኖችም በአካልም፥ በስልክም ከጁባ አልጠፉም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአዉሮጳ ሕብረት ዲፕሎማቶችም እንዲሁ።ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ጁባ ባይሔዱም ተፋላሚዎች ለድርድር እንዲገዙ መጎትጎታቸዉንም አላቋረጡም።«ልዩነቱ ምንም ሆነ ምን ወጣት ሐገራቸዉን የሚያነደዉ ሁከት በምንም መንገድ ትክክል ነዉ ሊባል አይገባም።እነሱ (የተፋላሚ ሐይላት መሪዎች) ተከታዮቻቸዉ መልዕክቱን በግልፅ እና በጉሉሕ መስማታቸዉ ለማረጋገጥ የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ አለባቸዉ።የጎሳም ሆነ ሌላ ግጭት መቀጠሉ ፍፁም ተቀባይነት የለዉም።»

ከዲንካ ጎሳ የሚወለዱት ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር፥ ከኑዌር የሚወለዱትን ምክትላቸዉን ሪክ ማ ማቼርን ባለፈዉ ሐምሌ ከሥልጣን ሲያስወግዱ በቋፍ-ድግፍግፍ ያለዉ የአዲሲቱ ሐገር ፖለቲካዊ፥ ጎሳዊ፥ አካባቢዊ ሠላም-አንድነት እንደሚናድ ከአዲስ አበባ እስከ ኒዮርክ፥ ከጅቡቲ እስከ ብራስልስ ያሉ መሪ-ዲፕሎማቶች ቢያቁ፥ ጠበኞችን ቢሸመግሉ በርግጥ በዘየዱ ነበር።

ጁባዎች ለጥፋት ከፈጠኑ ዓለም ጥፋቱን ለማስቀረት ዘግይቷል።እርግጥ ነዉ ኪርም፥ ማቼርም ለመደራደር ፈቃደኛ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።በደቡብ ሱዳን የኔዘርላንዱ ካቶሊካዊ የርዳታ ድርጅት አማካሪ ማርቲን ፔትርይ እንደሚሉት ግን ሁለቱም ሥልጣን ይፈልጋሉ፥ ለዚሕ ግባቸዉ ስኬት ለተጨማሪ ዉጊያ ይዘጋጃሉ።

«ድርድሩ በተጨባጭ እንዴት እንደሚጀመር በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።እንደ እዉነቱ ከሆነ ሳልቫ ኪር የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ መቀጠል ይሻሉ።ሪክ ማቼርም ሥልጣን መያዝ ይፈልጋሉ።በዚሕ ረገድ ጨዋታዉ ደርቷል።እና ድርድሩ መቼና እንዴት እንደሚጀመር አይታወቅም።እስካሁን ሁለቱም ወገኖች በድርድሩ ጠንካራ አቋም ለመያዝ ወታደራዊ ሐይላቸዉን እያጠናከሩ ነዉ።»

የአፍሪቃ ሕብረትና የኢጋድን የሊቀመንበርነት ሥልጣን የያዘችዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሐይለ ማርያም ደሳለኝ እና የኬንያዉ ፕሬዝዳት ኡሑሩ ኬንያታ ዛሬ ወደ ጁባ የተጓዙት ሚንስትሮቻቸዉ፥ ተፋላሚዎችን ለማደራደር እስካሁን ያደረጉት ሙከራ-ከዲፕሎማሲዉ ሽንገላ ባለፍ ተጨባጭ ዉጤት አለማምጣቱን መስካሪ ነዉ።

ከዚሁ ጋር ዩጋንዳ እንደ አደራዳሪ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯን አስቀድማ፥ እንደ ሳልቫ ኪር ደጋፊ ጁባን የሚጠብቅ ልዩ ጦሯን ማዝመቷ ሙከራዉን አወሳስቦታል።ያም ሆኖ የኬንያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት የኢትዮጵያና የኬንያ መሪዎች ጁባ የሐዱት ፕሬዝዳት ኪር ነገ ናይሮቢ ኬንያ በሚደረገዉ የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ለማግባባት ነዉ።ቻይናም ለድርድሩ ስምረት የአፍሪቃ ጉዳይ ታላቅ ዲፕሎማቷን ወደ ጁባ ለመላክ አቅዳለች።

ፔትርይ እንደሚሉት ድርድሩ መስመር አለበት።የነዳጅ ሐብታሚቱ ግን ዳሐይቱ፥ አዲሲቱ ግን ባሮጌ ዉዝግብ ጠብ የተተበተበቺቱ ሐገር ከድርድር ሌላ-ያላት አማራጭ ሁሉ ጥፋት ነዉ።

«ዞሮ ዞሮ ድርድር መደረግ አለበት።ሌላ ምርጫ የለም።ሐገሪቱ በጥልቀት ተከፋፍላለች።አሁን የሚታየዉ ግጭት የዲንካ እና የኑዌር ብቻ ይመስላል።ግን ሌሎች በርካታ የልዩነት ምክንያቶች አሉ።በሌሎች ጉሶችን መሠረት ያደረገ ጠብም አለ።»

እስከዚያዉ ግን ዓለም ሲያሳስብ፥ ሲያጠነቅቅ፥ ለዲፕሎማሲ ሲጠራራ፥ አፍሪቃ ጁባ ሲመላለስ፥ጁባ አስከሬኖቻን ቆጥራ፥ቀብራ ደሟን አድርቃ ሳታበቃ ቦር ተደገማለች።ድፍን የዩኒቲ ግዛት ቀጠለች።ጃግሌዬም አሰልሳለች።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለስ

Audios and videos on the topic