የየመን ቀውስና የኢትዮጵያውያ ስደኞች ጉዳይ | ኢትዮጵያ | DW | 08.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የየመን ቀውስና የኢትዮጵያውያ ስደኞች ጉዳይ

በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተመላሽነት ለመመዝገብ ፓስፖርት ወይም መታወቂያ ያስፈልጋል ተባለ። ኢትዮጵያ በየመን የሚገኙ ዜጎቿን ለመመለስ የምታደርገው ጥረት ግን አዝጋሚ ነው ተብሏል።

ሕንድ በየመን የሚገኙ ከ4,000 በላይ ዜጎቿን ለመታደግ የምታደርገው ጥረት ዘገምተኛ ነው የሚል ትችት በርትቶበታል። ቢሆንም ዛሬ ከ 1, 000 በላይ ህንዳውያን በአውሮፕላን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ቻይና የርስ በርስ ጦርነት በሚያናውዛት የመን የሚገኙ ዜጎቿን አጉዛ ጨርሳለች ። የምዕራባውያን ዜጎችና እና የአለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞች የመንን ጥለው የወጡት ሳዑዲ አረቢያ በየመን ላይ የአየር ጥቃት ለመሰንዘር የአካባቢውን አገራት ማስተባበር ስትጀምር ነበር። ኢትዮጵያም በየመን የሚገኙ ዜጎቿን ለመመለስ ጥረት ከጀመረች ሰነባበተች። የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም «የመጀመሪያዎቹ 30 ተመላሽ ወገኖች ከኤደን፣የመን ጅቡቲ ደርሰው የጅቡቲ አምባሳደራችን ተቀብሏቸዋል፡፡ለመመለስ የተመዘገቡት ቁጥር ከ2000 በላይ ሲሆን የጦርነቱ መባባስ የመመለስ ስራችንን አስቸጋሪ አድርጐታል፡፡» በማለት በፌስ ቡክ ማህበራዊ ድረ-ገጻቸው አስፍረዋል። የመን ዋና ከተማ ሰነዓ የሚገኘው ግሩም ተክለ ሐይማኖት ግን ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሀገር የመመለሱ ጥረት ዘገምተኛ ነው ሲል ተችቷል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው የአየር ድብደባ ዛሬ ደግሞ የሑቲ አማጽያንን የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘን እና የቀድሞውን ፕሬዝዳንት የአሊ አብደላ ሳላህ የትውልድ አካባቢን ኢላማው ማድረጉን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ከዋና ከተማዋ ሰንዓ በስተደቡብ 160 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ልብ(Ibb) ከተማ በአምስት ቦምቦች በተፈጸመ ድብደባ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸውን በሑቲ አማጽያን ቁጥጥር ስር የሚገኘው መከላከያ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ አስፍሯል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(The International Organization for Migration) በየመን የሚገኙ ከ11,000 በላይ የውጭ ዜጎችን ወደ አገሮቻቸው ለመመለስ የአስር ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ እርዳታ ጠይቋል። ድርጅቱ በየመን እየተባባሰ የመጣውን ቀውስ የሚሸሹ ስደተኞች በተለያየ መንገድ ወደ ጅቡቲና ሶማሊያ በመሻገር ላይ መሆናቸውንም ገልጿል። ግሩም ተ/ሐይማኖት በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መታወቂያ አሊያም ፓስፖርት የሌላቸውን ስደተኞች ያገለለ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሆነ ይናገራል።

«የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምዝገባ የኤሊ ጉዞ ነው። ምክንያቱም ሁለት ሰዎች ናቸው ተቀምጠው የሚመዘግቡት። ፓስፖርትና መታወቂያ ነው መስፈርቱ። ፓስፖርትና መታወቂያ የሌለው ስደተኛ ወደ አገሩ መመለስ ቢፈልግ መታወቂያ ከየት ነው የሚያመጣው? ስለዚህ ከባህር ተርፎ ዛሬ ጥይት ሊበላው ነው ማለት ነው።»

የመን የተሻለ የስራ እድል እና የኑሮ ሁኔታ ፍለጋ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እና ወደ ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለመጓዝ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሸጋገሪያ ነች። በህገ ወጥ የሰዎች አሸጋጋሪዎች አማካኝነት ከጅቡቲ ተነስተው የቀይ ባህርን በጀልባ በማቋረጥ የመን የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብዙ ጊዜ ሃሳባቸው አይሳካም። ከጥቂት ወራት በፊት 70 የምስራቅ አፍሪቃ አብዛኞቹ ደግሞ ከኢትዮጵያ የሆኑ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ ከየመን አልማካ የወደብ ከተማ አቅራቢያ መስጠሟ ይታወሳል። መታገት፤አካላዊ ስቃይ እና መከራ የመንን አቋርጠው መካከለኛው ምስራቅ አገራት ለመድረስ ያለሙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አጣ ፈንታ ነው። በየመን ለረጅም ጊዜ የኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ስራ በአሁኑ ቀውስ መስተጓጎሉን ግሩም ተ/ሐይማኖት ተናግሯል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic