የዚካ ተሐዋሲ ግስጋሴ፤ የዓለም ስጋት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 10.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የዚካ ተሐዋሲ ግስጋሴ፤ የዓለም ስጋት

የዩጋንዳ ዚካ ጫካ ውስጥ ነው የተገኘው። ስያሜውንም በዚያው ይዞ ዚካ ተሐዋሲ ተብሏል። እንደ ዓለም አቀፉ ጤና ጥበቃ ድርጅት ከኾነ ይኽ ቫይረስ ወይንም ተሐዋሲ ዛሬ ዓለማችን ላይ ስጋት ደቅኗል። በተለይ ብራዚልን ጨምሮ በደቡብ እና ሰሜን አሜሪካ ሃገራት ተሐዋሲው ግስጋሴውን ቀጥሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:34
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:34 ደቂቃ

ዚካ የዓለም ስጋት?

ከሰባት ዐሥርት ዓመታት በፊት ተገኘ በተባለባት አፍሪቃም አንዳንድ ቦታዎች መዛመት ጀምሯል። ለአብነት ያኽል በምዕራብ አፍሪቃ የባሕር ጠረፍ አቅጣጫ፤ በደሴታማዋ የኬፕ ቬርዴ ሪፐብሊክ ከ7000 በላይ ሰዎች በዚካ ተሐዋሲ መያዛቸው ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገ ጥናት ከሁለት ዓመት በፊት ሁለት ሰዎች በተሐዋሲው ተይዘው እንደነበር የደም ናሙናቸው አመላክቷል። ለመሆኑ ዚካ ቫይረስ ምንድን ነው?

በዋናነት ደም መጣጭ በሆነች ትንኝ ይተላለፋል። በተለይ ነፍሰ-ጡር ሴቶችን እና ሕፃናትን ያጠቃል። ዚካ። ይኽ ተሐዋሲ፤ ሕፃናት፤ ሚጢጢ የራስ ቅል እና የተጎዳ አንጎል ይዘው እንዲወለዱ የማድረግም ተጽዕኖ አለው። ከመደበኛው እጅግ ባነሰ መልኩ የራስ ቅል መዛባት ክስተትን ተመራማሪዎች ማይክሮከፈሊ (Microcephaly) ይሉታል።

የሕፃናት የራስ ቅል መዛባት

ከኅዳር እስከ ጥር ድረስ ባሉት ሦስት ወራት ብቻ ብራዚል ውስጥ ከአራት ሺህ በላይ ጨቅላዎች ይኽቺን ዓለም በዚህ መልኩ ተቀላቅለዋል። ዚካ የሕፃናት ጤናማ የአዕምሮ ብልጽግና በተገቢው ጊዜ እንዳይኖር እክል የሚፈጥር አደገኛ ተሐዋሲ እንደሆነ ይነገርለታል።

ዶክተር መርዓዊ አራጋው በጤና ጥበቃ ሚንስቴር የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች አማካሪ ናቸው። ስለ ዚካ ተሐዋሲ ምንነት ያብራራሉ።

«ቫይረሱ በትንኝ የሚተላለፍ ነው። እንግዲህ ይኼ ትንኝ ደግሞ ትሮፒካል በሚባለው ሞቃታማው የአየር ንብረት ክልል ውስጥ የሚገኝ ትንኝ ነው። ሌሎችንም ተመሳሳይ በሽታዎችን የሚያስተላልፍ ትንኝ ነው። የቢጫ ወባ የምንለውን፤ እንዲሁም የደንጊ ትኩሳት (የቆላ ንዳድ) የሚባሉትን በሽታዎች ያስተላልፋል።»

ዚካ በአፍሪቃ

ልክ እንደ ቢጫ ወባ እና ዴንጊ ትኩሣት ማለትም የቆላ ንዳድ ተሐዋሲያን ሁሉ ዚካም በምድራችን መከሰት ከጀመረ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል። በእርግጥ ቀደም ሲል እንደ አሁኑ በወረርሽኝ ደረጃ ባይዛመትም፤ በ1968 ተሐዋሲው ከአንድ ናይጄሪያዊ ደም ውስጥ ተለይቶ ለምርምር እንደተወሰደ በተሐዋሲያን ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ። ከዚያ ቀደም ሲል ተሐዋሲው ይገኝ የነበረው የቢጫ ወባ ምንነትን ለማጥናት ቤተ-ሙከራ ውስጥ ተይዘው በተቀመጡ ጦጣዎች ላይ ነበር። በ1950 ግን የዚካ ተሐዋሲን ለመፋለም የተፈጠሩ የሰውነት በሽታ ተከላካዮች የሰው ደም ውስጥ መገኘታቸውን ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በሰዎች የደም ናሙና ላይ የተሐዋሲው አመላካች ቅሪቶች ተገኝተው እንደነበር ዶክተር መርዓዊ አራጋው ይናገራሉ።

«የዛሬ ሁለት ዓመት ባደረግነው ዳሠሣ ሁለት ሦስት ቦታዎች ላይ የዚካ ቫይረስን ምልክት (አይተናል) እንግዲህ ቀደም ብሎ በዚህ በሽታ የተያዘ ግለሰብ ሰውነቱ ላይ ትቶ የሚያልፈውን ምልክት አግኝተነው ነበር። ይኼ ማለት ምንድን ነው? በአኹኑ ወቅት እየተዘዋወረ የሚገኝ የበሽታው ስርጭት መኖሩን አያመለክትም። የዛሬ ሁለት ዓመት ነው ቅኝቱን ያኪያሄድነው። ከሰበሰብናቸው ናሙናዎች በጣም ጥቂት የሚባሉ ሁለት ሦስት እንደዚህ አይነት ውጤቶችን አግኝተን ነበር።»

ዩጋንዳ ዚካ ጫካ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተገኘ የሚነገርለት ይኽ ተሐዋሲ ቀደም ሲል በሰው ልጆች ደም ውስጥ አልነበረም። ተሐዋሲው ከቤተ-ሙከራ ጦጣዎች ተነጥሎ ወደ አይጦች ተወስዶ ግን ምርምር ይደረግበት ነበር። ያኔ በወቅቱ የዚካ ተሐዋሲን በደማቸው ውስጥ የተወጉ የቤተ-ሙከራ አይጦች በሙሉ በሽተኛ መኾናቸው ተመዝግቧል። ከነዚህ በዚካ ተሐዋሲ የተያዙ አይጦች አንጎል በሣይንሳዊ ምርምር ተነጥሎ የተወሰደው ተሐዋሲ ነበር የዚካ ተሐዋሲ የተባለው።
በእርግጥ ዚካ ከአይጦች ወደ ሰዎች አለያም ከጦጣዎች ወደ ሰው ልጆች እንዴት አፈትልኮ እንደገባ የቀረበ ተጨባጭ ጥናት የለም። ሆኖም ዚካ በአሁኑ ወቅት በአፍሪቃ በተለይ በምዕራብ አፍሪቃ መከሰቱ እየተዘገበ ነው።

125,000 ነዋሪ ባላት የደሴታማዋ ኬፕ ቬርዴ መዲና ፕራየ ውስጥ በተሐዋሲው የተያዙት ሰዎች ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የኬፕ ቬርዴ የጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ቶማስ ቫልዴዝ በሀገራቸው ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች በዚካ ተሐዋሲ መያዛቸውን ገልጠዋል።

«እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ 7164 በዚካ የተያዙ ሰዎችን መዝግበናል። አብዛኞቹ በዚካ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች የሚገኙት በመዲናይቱ ፕራየ ነው። እዚያ በቫይረሱ የተያዙ ወደ 4800 ሰዎች ይገኛሉ።»

ኃላፊው ይኽን ያስታወቁት ባለፈው ሣምንት ነበር። ኬፕ ቬርዴ ተሐዋሲው በብዛት እየተሰራጨ የሚገኝበት ላቲን አሜሪካን፤ ምዕራብ አፍሪቃን ብሎም አውሮጳን የምታገናኝ ማዕከል ናት።

ከአጠቃላይ የኬፕቬርዴ ዘጠኝ ደሴቶች ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ የሚተዳደሩት ከአገር ጎብኚዎች በሚገኝ ገቢ ነው። ኬፕቬርዴ የዚካ ተሐዋሲ ሥርጭትን ለመግታት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገች ነው። በጥር ወር በአንድ ሣምንት ውስጥ 800 በዚካ ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበው ነበር። አኹን አዲስ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር 83 ብቻ ናቸው ተብሎዋል። ለዚህ ስኬትም ሀገሪቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረጓ እንደኾነ ተጠቅሷል።

ዶክተር መርዓዊ አራጋው በበኩላቸው ጥንቃቄ መደረጉ ባይቀርም፤ የዚካ ተሐዋሲ ኢትዮጵያ ውስጥ በአኹኑ ወቅት በተለየ የሚታይበት ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል።

«ከዚህ ቀደም ኢቦላ ላይ እንደሠራነው ሀገር ውስጥ በመግቢያ ድንበሮች ላይ እንደዚህ አይነት ክትትሎችን አኹን ለዚህ በሽታ በተለየ አናደርግም። እንደዚህ አይነት አሠራርም አን,ጥርም። በሽታውም ብዙዎቹ ላይ በምልክት ደረጃ የማይለይ በመኾኑ ማለት ነው። ነገር ግን እንደዚህ አይነት ሰዎች በተለይ ከመጡ የምንከታተልበት ሥርዓት አለ። በዚያ አይነት መልኩ እንከታተላቸዋለን።»

ዚካ ገና በሚወለዱ ጨቅላዎች ላይ የራስ ቅል መዛባት ከመፍጠሩም ባሻገር፤ የጽንስ ጭንገፋ የሚያስከትል ተሐዋሲ ነው ተብሏል። ያም በመኾኑ ነፍሰ-ጡር ሴቶች አለያም ልጅ የመውለድ ዕቅድ ያላቸው ሴቶች በአጠቃላይ ተሐዋሲው ወደ ተዛመተባቸው የዓለም ክፍሎች እንዳይጓዙ የጤና ባለሙያዎች ምክራቸውን ለግሰዋል።

ኬንያ የዚካ ቫይረስ በፈጠረባት ስጋት የተነሳ የበጋ ኦሎምፒክ ወደሚኪያሄድባት የብራዚሏ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ከተማ አትሌቶቿን ላትልክ እንደምትችል ከወዲሁ አስጠንቅቃለች።በብራዚል ብቻ በሦስት ወራት ውስጥ 4,700 ጨቅላዎች የራስ ቅላቸው ተዛብቶ መወለዳቸው ተዘግቧል። ሀገሪቱ ውስጥ ለአራት ዓመታት የተከናወነ ጥናት እንደሚያመለክተው ከኾነ ደግሞ ገና የተወለዱ ከ100,000 በላይ ጨቅላዎች ላይ የራስ ቅል መዛባቱ እንደነበር ተገልጧል።

የዚካ ተሐዋሲ ብራዚል ውስጥ መዛመት የጀመረው ካለፈው ጥቅምት ወር አንስቶ በመኾኑ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ጨቅላዎቹ የራስ ቅል መዛባት ቀደም ሲል መከሰቱ ከዚካ ተሐዋሲ ጋር ግንኙነት ይኑረው ወይ ሌላ ምክንያት መቶ በመቶ አልተረጋገጠም። የዓለም የጤና ድርጅት ግን መዛባቱ ከዚካ ተሐዋሲ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው እንደሚያምን አስታውቋል። ቁርኝት ይኑር አይኑር ለመለየት ብራዚል መጠነ ሰፊ ምርምር እያከናወነች ነው። ይኽን አደገኛ ተሐዋሲ በተመለከተ በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በፊት ጥናት የተደረገው ለምን ነበር?

«ሰውነታችን በሽታ ሲከላከል የሚያወጣቸው ምልክቶች አሉ፤ ልክ አኹን ሰው ሲቆስል የቆሰለው ቦታ ላይ ለምጥ ኹኖ እንደሚቀረው የሰውነት ተከላካዮቻችንም ተሐዋሲ ወይንም ሌላ ቫይረስ ወይንም ባክቴሪያ ሲያጋጥመው ያንን የተከላከለበት የሚተወው ምልክት አለ። እና በቤተ-ሙከራ ምርመራ ምን ምን አይነት ቫይረሶች አሉ የሚል ጥናት አልፎ አልፎ እናደርጋለን።ይኽንን ነገር ስንመለከት አኹን እየተላለፈ የሚገኝ የበሽታው ስርጭት አለ ይኾን የሚል ጥናትም ለማድረግ ሞክረን ነበር። እና በወቅቱ እንደዚህ አይነት ነገር የለም፤ ከዚያ በኋላም እንደዚህ አይነት ነገሮችን አላገነንም።»

የዚካ ተሐዋሲ መለያ

በዚካ ተሐዋሲ የተያዙ አብዛኞቹ ሰዎች በተሐዋሲው ስለመያዛቸው እጅግ መጠነኛ አለያም አንዳችም ምልክት አያሳዩም። በተሐዋሲው ከተያዙ ሰዎች ሩብ ያኽሉ ብቻ ምልክቶችን የሚያሳዩት ከ2-10 ባሉት ቀናት ውስጥ ነው። በተሐዋሲው የተያዘ ግለሰብ በሰውነቱ ላይ እንደ ኩፍኝ ያለ ሽፍታ ይፈስበታል። የሰውነቱ ትኩሳት ይጨምራል። የመገጣጠሚያ አካላቱ ኅመም ያይላል። ዓይኖች ይቀላሉ። ከፍተኛ ራስ ምታትም ይከሰታል። የዚካ ተሐዋሲ በወሲብ ሊተላለፍ ይችላል ተብሏል። ተሐዋሲው ምራቅ እና ሽንት ውስጥ እንደሚገኝም ተዘግቧል።

ተሐዋሲው በቀላሉ የማይለይ በመኾኑ፤ መድሐኒት አለያም ክትባት ስላልተገኘለት የዓለም ጤና ድርጅት ተሐዋሲው የዓለም ስጋት ነው ሲል አውጇል። ሃገራትም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል።

«አኹን እየተላለፈ ያለ፤ በወቅቱም የተላለፈ ሥርጭት አልተገኘም። በዚያም ጊዜ አኹንም ቢሆን እንደዚህ አይነት ሥጋት የለም። ያው ነገር ግን የዓለም ሥጋት እየሆነ ለዚያም ነው የዓለም ጤና ድርጅት እንደዚያ አይነት ውሳኔ ያስተላለፈው። እንጂ አኹን ባለንበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነት ሥጋት ወይንም እንደዚህ አይነት የሚተላለፍ፤ የተያዘም ሰው፤ እንዲዚህ አይነት ሥጋት የለም።»

በዚካ ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት ዩናይትድ ስቴትስ ቫይረሱ በሞቃታማ ወቅቶች በስፋት ሊሰራጭባት ስለሚችል አፋጣኝ የክትባት እና የመድሐኒት ምርምር እንዲደረግ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አሳስበዋል። በተለያዩ የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ሣይንቲስቶች የዚካ ቫይረስ ስርጭትን መከላከል የሚችል ክትባት በጊዜ ለመፈብረክ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መኾኑ ተሰምቷል። ምናልባት ያኔ ይኽ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ስጋት የደቀነው ተሐዋሲ የስርጭት ግስጋሴው ዕልባት ያገኝ ይኾናል። ለጊዜው ግን የወባ ትንኞች ስርጭትን መከላከል ወሳኝ ነው ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic