1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ባንክና ምንዛሪ ተቋም ዓመታዊ ጉባዔ

የዓለም ባንክ በበኩሉ ከወዲሁ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ዘገባው ለታዳጊ አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት ድሃው ሕዝብ የበለጠ የእኩልነት ዕድል ማግኘቱ ወሣኝ እንደሆነ አመልክቷል። “ፍትሕና ልማት” በሚል ርዕስ በወጣው በባንኩ ዘገባ መሠረት ይህ የሞራል ግዴታ ብቻ ሣይሆን በታዳጊው ዓለም የምጣኔ-ሐብት ዕድገትን ይበልጥ ለማጠናከርም የሚረዳ ነው።

የዓለም ባንክና የምንዛሪው ተቋም ጉባዔ ከስድሥት አሠርተ-ዓመታት በላይ በመንግሥታትና በሲቪሉ ሕብረተሰብ ዘንድ ዓቢይ ክብደት የሚሰጠው ድርጊት ሆኖ ኖሯል። ለዚህም ምክንያቱ የፊናንስ ተቋማቱ ፖሊሲዎች በዓለም መንግሥታት የኤኮኖሚ ይዞታ ላይ ተጽዕኖ ያላቸው መሆኑ ነው።

በፊታችን ቅዳሜና ዕሑድ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የዚህ ዓመቱ ጉባዔም እንዲሁ የተለየ ክብደት ይኖረዋል። G-8 በመባል የሚታወቁት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ ሰባት ቀደምት መንግሥታትና ሩሢያ ባለፈው ሐምሌ ወር ስኮትላንድ ላይ አካሂደውት በነበረ የመሪዎች ጉባዔ ሲበዛ ድሃ ተብለው የተመደቡ 18 ሃገራት በዓለም ባንክ፣ በምንዛሪው ተቋም IMF እና በአፍሪቃ ልማት ባንክ ፊት ያለባቸውን ዕዳ ለመሰረዝ መስማማታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

በሣምንቱ መገባደጃ የሚያካሂደው የገንዘብ ተቋማቱ ጉባዔም በተለይ በዚሁ በ G-8 ሃሣብ ላይ የሚከራከርና በተግባር ላይ መዋል መቻል-አለመቻሉን የሚለይ ይሆናል። በወቅቱ የዕዳ ምሕረቱ ወደፊት ተፈጻሚነት ማግኘቱ በሲቪሉ ማሕበረሰብ፤ ማለት ከመንግሥት ነጻ በሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ባለሙያዎች ዘንድ ብቻ ሣይሆን በገንዘብ ተቋማቱ ውስጥ ሳይቀር ጥርጣሬን ፈጥሮ ነው የሚገኘው።

በዚህ ሣምንት ሾልኮ ሊወጣ የቻለ አንድ የዓለም ባንክ ውስጣዊ ዘገባ እንዳመለከተው አርባ ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጋው የዕዳ ምሕረት የገንዘብ ተቋሙ አካል የሆነውን ዓለምአቀፍ የልማት ማሕበር ግንዘብ እንዳያሟጥጥ ብርቱ ስጋት አለ። ይሄው በአሕጽሮት IDA በመባል የሚታወቀው ዓለምአቀፍ የልማት ማሕበር ለድሆች አገሮች በያመቱ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚያቀርብ የባንኩ ዘርፍ ነው።

ከዚሁ ሌላ ቤልጂግ፣ ኖርዌይ፣ ስዊስንና ኔዘርላንድን የመሳሰሉ የአውሮፓ መንግሥታት ለታዳጊ አገሮች በደፈናው ሙሉ የዕዳ ምሕረት መደረጉን አጥብቀው ይቃወማሉ። ወደፊት በዚህ አቅጣጫ የሚቀርብ የምሕረት ሃሣብ ጥብቅ ከሆኑ ቅድመ-ግዴታዎች ጋር የተሳሰረ ሊሆን ይገባዋል ባዮች ናቸው። ከ G-8 መንግሥታት ሌላ የተቀሩት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ አውሮፓውያን መንግሥታት አስተያየትም በዕዳ ምሕረቱ ገቢርነት ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል ማለት ነው።

እርግጥ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ቶማስ ዶውሰን ከጥቂት ቀናት በፊት በጉዳዩ በሰጡት አስተያየት ልዩነቱን አቃለው ነበር ያቀረቡት። ይሁንና ቅራኔው ከዚህ ጥቂት ከበድ ያለ አንደሆነ ነው የሚገመተው። ዶውሰን በ G-8 ሃሣብ መሠረት ለዕዳ ምሕረት የሚያስፈልገው አብዛኛው ገንዘብ በወቅቱ በምንዛሪው ተቋም እንደሚገኝም ተናግረዋል። ግን የዕዳ ምሕረቱ ዕውን ለመሆኑ እስካሁን ከዓለም ባንክም ሆነ ከምንዛሪው ተቋም በኩል የቀረበ ማረጋገጫ የለም።

ሃሣቡን ወይም ስምምነቱን ለተግባር በማብቃቱ አኳያ ዋና መሰናክል ሆኖ የሚገኘው G-8 መንግሥታት በዓለም ባንክና በምንዛሪው ተቋም ውስጥ ያላቸው የድምጽ ድርሻ ባንድላይ ከ 50 በመቶ ጥቂት በበለጠ የተወሰነ መሆኑ ነው። በሌላ በኩል ይህን መሰሉን ውሣኔ ለማስተላለፍ 85 በመቶ የብዙሃን ድምጽ ድጋፍ ያስፈልጋል። ታዲያ አብዛኛውን ድምጽ ይዘው የሚገኙት አውሮፓውያን መንግሥታት በመሆናቸው G-8 ውስጥ ያልተጠቃለሉት እነዚህ ሃገራት ስምምነቱን ከግቡ በማድለሱ በኩል መሰናክል ሊሆኑ የማይችሉበት ምክንያት የለም።

የዕዳ ምሕረት እንዲደረግ የተስማሙት በ G-8 ስያሜ የተሰባሰቡት ሃገራት ረሢያና ሰባቱ ቀደምት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት፤ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ካናዳና ጃፓን ናቸው። እነዚሁ መንግሥታት ባለፈው ሐምሌ ወር የደረሱበት፤ በጊዜው ታሪካዊ ነው ተብሎ የተወራለት ስምምነት ገቢር ሊሆን ካልበቃ ብርቱ ሃዘን ላይ የሚጥለው የዕዳ ምሕረት ይደረግላችኋል ተብለው በተሥፋ የሚጠባበቁትን 18 አገሮች ብቻ አይደለም።
ከዚያም አልፎ ለሌሎች አብዛኛው ሕዝባቸው ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ የመከራ ኑሮ ለሚገፋባቸው፤ የድሕነት ሰለባ ለሆኑ አገሮች ሁሉ መሪር ነው የሚሆነው። በርካታ ከመንግሥታት ነጻ የሆኑ ድርጅቶችና ገለልተኛ ታዛቢዎች ዕዳን መልሰው መክፈል የሚኖርባቸው ብዙዎች አገሮች አሁን ባለው ሁኔታ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ድህነትና ረሃብን በግማሽ ለመቀነስ በተባበሩት መንግሥታት የተቀመጠውን የሚሌኒየም ዕቅድ ከግቡ ማድረስ መቻላቸውን ሲበዛ አጠያያቂ ያደርጋሉ። የዕዳ ምሕረቱ ገቢር አለመሆን በስኮትላንዱ ጉባዔ ቃል የገቡትን መንግሥታትም በቃል-አጣፊነት የሚያስወቅስ፤ ትዝብት ላይ የሚጥል ነው የሚሆነው።

በሌላ በኩል ከፍተኛ ዕዳ የተጫነባቸው ድሃ አገሮች በሚል ምሕረቱ እንዲደረግላቸው የተመረጡት አገሮች አደላደል ራሱ ብዙ የሚያጠያይቅ ነው። ምዕራባውያኑ መንግሥታት ከዕርዳታው ተገቢነት ይልቅ ከአንዱ ወይም ከሌላው አገር ጋር ያላችውን የፖለቲካ ግንኙነት ቀዳሚ መስፈርት ማድረጋቸው አልቀረም። የዕዳ ምሕረቱ በመሠረቱ ከነዚህ ተረጂ አገሮች በአንጻሩ ከኤኮኖሚ ለውጥ ባሻገር ፍትሃዊ አስተዳደር ዘይቤንና የሰብዓዊ መብትን ከበሬታ የመሳሰሉ ዓቢይ ጉዳዮችን ቅድመ-ግዴታ የሚያደርግ ነው። ግን ይህ እንደተባለው አለመሆኑን የተዘዘሩትን አገሮች ማንነት አንብቦ በቀላሉ መረዳት ,ይቻላል።

ፖለቲካውን በዚሁ ተወት እናድርገውና ሙሉ የዕዳ ምሕረት ይደረግላቸዋል ተብለው ከተውጣጡት 18 አገሮች መካከል 14ቱ ከአፍሪቃ ሲሆኑ የተቀሩት አራቱ ከላቲን አሜሪካና ከካራይብ አካባቢ ናቸው። ድሕነት ያለፈ ታሪክ ይሁን በሚል ስያሜ በሚጠራው የብሪታኒያ ቀስቃሽ ወገን ገለጻ መሠረት ከተባባሩት መንግሥታት የሚሌኒዬም የልማት ግብ ሁሉም እንዲደርስ ከተፈለገ በእርግጥ ቢያንስ 62 አገሮች ተመሳሳይ የዕዳ ምሕረት ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ሃብታም አገሮች የዓለም ባንክና የምንዛሪው ተቋም ገንዘብ እንዳይሟጠጥ ሲሉ የሚሰነዝሩት ስጋት ባለፈው ሐምሌ ወር ስኮትላንድ ላይ ከተገባው ቃል መልሶ ገሸሽ ለማለት የሚሰጥ ምክንያት ሆኖ ነው በብዙዎች የሲቪሉ ሕብረተሰብ ተሟጋች ድርጅቶች የተወሰደው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ግን የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF አንዳች ወሣኝ የፊናንስ ችግር ሳይደርስባቸው ከሰላሣ ለሚበልጡ አገሮች ዕዳን ለመሰረዝ ብቃቱ አላቸው።
ከሆነ ምኑ ላይ ነው ችግሩ? በዕዳ ምሕረት ጉዳይ ላይ አተኩረው የቆዩ የተለያዩ ቡድኖች የመንግሥታቱን ስምምነት በጊዜው አወድሰው ይቀበሉት እንጂ መፈጸሙን ግን ገና ከጅምሩ ነበር በጥርጣሬ የተመለከቱት። አሁን ሁኔታውን ሲመለከቱት እርግጥም ስጋታቸው ያለ ምክንያት አልነበረም።

የሲቪሉ ሕብረተሰብ አካል ድርጅቶች የተገባው ቃል ዕውን እንዲሆን በተለያየ መልክና ደረጃ እስካሁንም ሲገፋፉ፤ የዕዳ ቅነሣውን ዘመቻ ተጨማሪ አገሮች እንዲቀላቀሉትም ሲወተውቱ ነው የቆዩት። አሁንም የገንዘብ ተቋማቱ ለዓመታዊ ጉባዔያቸው በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በአሜሪካና በዓለም ዙሪያ ለሙሉ የዕዳ ስረዛ በፊታችን ቅዳሜ የተለያየ የቅስቀሳ ዘመቻ ሊያካሂዱ በመሰናዶ ላይ ናቸው። ዋሺንግተን ላይም ዋናውን የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ታቅዷል። የኢራቅን ጦርነት ጭምር የሚያነሱት የተቃውሞ ሰልፈኞች የዕለቱንም ዓቢይ ጉዳያቸውን “የኤኮኖሚ ጦርነት” በዓለም ድሆች ላይ ብለውታል።

ዓላማው የዓለም ሕዝብ በጉባዔው ላይ እንዲያተኩር፤ ሃብታሞቹ አገሮችም ከገቡበት ግዴታ መልሰው ገሸሽ እንዳይሉ ለመጫን ነው። ሰሚ ጆሮ ይገኝ ይሆን? ቢሣካ ግሩም በሆነ ነበር። ግን አዲስ ነገር መጠበቁ በጣሙን ያዳግታል።

ለማንኛውም ችግሩን ለመወጣት ቁርጠኝነትና ጭብጥ ዕርምጃ የግድ አስፈላጊ ነው የሚሆነው። የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ፓውል ዎልፎቪትስ የዕድል እኩልነት የሚል የተቋማቸው ፍልስፍና ዘር፣ ጾታ ወይም ማሕበራዊ ሁኔታን ሳይለይ ለሁሉም የሚሠራ መሆኑን አስረድተዋል። ለረጅም ጊዜ ልማት ወሣኝ ጉዳይ መሆኑም ነው በባንኩ ዘገባ የተጠቀሰው።

ይሁን እንጂ የተባለው የልማት ዕርምጃ እንዲከሰት ቃል ተግባር ሲሆን መታየት ይኖርበታል። የዕዳ ስረዛውም ያላንዳች ቆይታና አድልዎ በሌለበት ሁኔታ በሥራ ላይ መዋሉ ግድ ነው። ያለፉት ዓመታት ሁኔታ እንዳሣየው ከሆነ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በጉዳዩ አዘውትሮ ከማውራት ባሻገር በተጨባጭ አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆናቸው ብዙ ያጠያይቃል።

በሌላ በኩልም ዕዳ የሚሰረዝላቸው አገሮች፤ ለምሳሌ G-8 በውጥኑ ቅድሚያ የሰጣቸው 18 አገሮች መንግሥታዊ ይዞታዎችን ወደ ግል ንብረትነት በመለወጡ በኩል ተራምደዋል መባሉ ብቻ አይበቃም። ከዕዳ ስረዛው የሚገኘው ገንዘብ ለልማት ዕርምጃ ሊጠቅም የሚችለው ይሄው በየባለሥልጣናቱ ዕጅ ሳይባክን ለሕዝብ ሊደርስ ሲችል ብቻ ነው። በዚህ በኩል በዙ የተነገረለት በጎ የአስተዳደር ዘይቤ ለዕዳ ምሕረቱ አስፈላጊው መስፈርት ሆኖ ቀርቧል ለማለት አይቻልም።

የታዳጊ አገሮችን ልማት በማፋጥን አያሌ ሚሊዮን ሕዝብን ከረሃብና ከድህነት ለማላቀቅ የሚቻለው አንድ-ወጥ የዴሞክራሲ መስፈርት ሲኖርና ምዕራባውያኑ መንግሥታትም ጉዳዩን ከተለያየ የግል ጥቅማቸው አንጻር መመልከቱን ሲተዉ ብቻ ነው። በወቅቱ ለሃብታም አገሮች ካደላውና በነርሱው ከተጫነው የዓለም ኤኮኖሚ ሥርዓት ስንብት ማድረጉ ግድ ነው የሚሆነው። የበለጸጉት መንግሥታት ገበዮቻቸውን ለታዳጊ አገሮች ምርት ዘግተውና ገድበው፤ የዓለም ኤኮኖሚን በሞኖፖል ይዘው እስከቀጠሉ ድረስ ዓለም በ 21ኛው ክፍለ-ዘመን የምትገኝበት እጅግ የሰፋ የድሃና የሃብታም ልዩነት ሊወገድ ቀርቶ ሊለዝብ እንኳ የሚችል አይሆንም።