የወጣቶች መድረክ | ባህል | DW | 20.04.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የወጣቶች መድረክ

ኤርትራዊ ወጣት የቀድሞ ስደተኛ ከ400 በላይ ለሚሆኑ የጀርመን የፌዴራል ፖሊስ አካዳሚ ተማሪዎች በጀርመንኛ ስላሳተመው መፅሐፉ ገለፃ አድርጓል። ወጣቱ ከፖሊሶች ጋር እንዲወያይ መድረኩን ካመቻቹለትና በስደተኞች ጉዳይ ዙሪያ ከሚንቀሳቀሱት የ Deutschlandstiftung Integration ሰራተኞች ጋርም ተወያይተናል።

የጀርመን ፖሊስ በባቡር ጣቢያ

የጀርመን ፖሊስ በባቡር ጣቢያ

ዘካሪያስ ክብረአብ ይባላል፤ ነዋሪነቱ በበርሊን ከተማ ነው። ጀርመን ሀገር መኖር ከጀመረ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሯል። እንዲህ እንደ አሁኑ የተለያዩ የመገናኛ ዘርፎች መነጋገሪያ ከመሆኑ አስቀድሞ በስደተኝነት በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ተንከራቷል። እዚህ ጀርመን እንኳን ያለ ፈቃድ ሲንቀሳቀስ ባቡር ውስጥ ተይዞ ለወራት ዘብጥያ ቆይቷል። ያም ነበር የመፅሀፉ ማሟሺያ።

ዘካሪያስ የስደት ውጣ ውረዱንና በኤርትራ ውስጥ ብዙዎች ያሳልፉታል ያለውን መከራ የሚጠቁመው መፅሐፉ ለንባብ ከበቃ በኋላ፤ ሁኔታው ከብዙ ሰዎች ጋር እንዲገናኝ እድል ፈጥሮለታል። መፅሀፉ ዘካሪያስ አሁን ከሚሰራበት ተቋም አመራሮች አንስቶ እስከ ጀርመኗ መራሂተ-መንግስት ድረስ ተገናኝቶ እንዲወያይ መንገዱን ጠርጎለታልሐፍe። በአንድ ዝግጅት ላይ ያዩት የ Deutschland Stiftung Integration ስራ አስኪያጅም አነጋግረውት ተቋማቸው ውስጥ እንዲሰራ እድል እንደሰጡት ገልጿል። ተቋሙ በጀርመን ሀገር የሚገኙ ስደተኞችን መረጃ በመስጠት ለማገልገል የተቋቋመ ነው።

የጀርመንኛ ቋንቋ

የጀርመንኛ ቋንቋ

«ይህ ተቋም በመፅሄት አሳታሚዎች ማኅበራት በ2008 ነው የተመሰረተው። አሳታሚ ማኅበራቱ የእኔ ተቋምን ሲመሰርቱ ከውጭ ሀገራት የመጡ ሰዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ተስማምተውና ተዋህደው መኖር የሚችሉበት ጉዳይ ላይ ሀላፊነት ለመውሰድ በመፈለጋቸው ነው። ያ የፈለጉት ነገር አሁን በመገናኛ ብዙኃን በደንብ እየታየ ነው። ማኅበራቱ ከዚያም በላይ መስራት ስለፈለጉ ነው ተቋሙን የመሰረትነው። »

ተቋሙ በተለይም ጀርመንኛ ቋንቋ ላይ አተኩሮ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ሰፋ ባለ መልኩ የሚያሰራጨው የማስታወቂያ ዘመቻ አለው። raus mit der Sprache, rein ins Leben ይሰኛል የማስታወቂያ መፈክሩ። «ተናገር፥ ኑሮውን ተቀላቀል» እንደማለት ያለ ነው። ቋንቋ የሁሉም ነገር ቁልፉ ነው፤ የሚል አፅንኦት ለመስጠት ነው የማስታወቂያ ዘመቻው ያስፈለገው። ስመ ጥር የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ሞዴሎች፣ ስፖርተኞች፣ እንዲሁም የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች በዚህ ማስታወቂያ ላይ ይሳተፋሉ። ተቋሙ ከዚያም ባሻገር በጀርመን ጥገኝነት ጠያቂዎች መረጃ ከማጣት የተነሳ መጉላላት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊውን መረጃ የማቀበል እና የውይይት መድረክ የማዘጋጀት ተግባርም እንዳለው ተጠቅሷል።

«በጣም በቅርቡ ለምሳሌ፤ በጀርመን ፌዴራል ፖሊስ አካዳሚ ውስጥ የተደረገው ውይይት አለ። ከኤርትራ የተሰደደው ባልደረባችን ዘካሪያስ ክብረአብ ስለስደት ህይወቱ እና በጀርመን ፌዴራል ፖሊስ ስለታሰረበት ሁኔታ ከፖሊስ አካዳሚው ተማሪዎች ጋር ተወያይቷል። ይህ የሀሳብ ልውውጥ ተቋሙ ከተለያዩ አንፃሮች መረጃን ለማዳረስ ከተነሳበት ዓላማ ጋር ይጣጣማል።»

ከኅብረተሰቡ ጋር መቀላቀል

ከኅብረተሰቡ ጋር መቀላቀል

የስደተኞችን ጉዳይ አስመልክቶ በተመሰረተው ተቋም ውስጥ ስራ አስኪያጅ እንደሆኑት ፌሪ ፓውሽ ገለጻ፤ ጀርመንኛ ቋንቋን አስመልክቶ የተጀመረውን የማስታወቂያ ዘመቻ ወደ ሰማንያ ሚሊዮን የሚጠጋ የጀርመን ነዋሪ ተመልክቶታል። ተቋሙ በጀርመን ሐገር የስራ፣ የትምህርት እና የማኅበራዊ ኑሮ ሂደት ውስጥ ዘልቆ ለመግባት ከምንም በላይ የጀርመንኛ ቋንቋን በአግባቡ መማር ወሳኝ ነው በማለት በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው። በእርግጥም ከስምንት ዓመታት በፊት ጀርመን ሀገር በሕገ ወጥ ስደተኝነት የገባው ወጣት ዘካሪያስ የተለያዩ የዜና አውታሮችን የሳበው የህይወት ውጣውረዱን በጀርመንኛ ቋንቋ በመፃፉ ነው።

ጀርመን ሐገር ለ8 ዓመታት የቆየው ወጣት ዘካሪያስ ለንባብ ያበቃው መፅሐ,ፍ Hoffnung im Herzen, Freiheit im Sinn ይሰኛል። ነፃነትን ፍለጋ ከልብ ያደረ ተስፋ የሚለው የአማርኛ ፍቺ የሚስማማው ይመስለናል። መፅሐፉን ዘካሪያስ በመጀመሪያ በትግርኛ ቋንቋ ነበር የፃፈው። ከዚያም ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ ተርጉሞ በኋላ ላይ ማሪነ ሞይዝላ ለተባለች ጋዜጠኛ እንዳሳያት ጠቅሷል። ጋዜጠኛዋ ከዘካርያስ ጋር ሱዳን ድረስ በመሄድ የስደት ጉዞውን ከተመለከተች በኋላ መፅሐፉን ለሁለት በድጋሚ ፅፈውት ለህትመት እንደበቃ ገልፆልናል። በእርግጥም ወጣት ዘካሪያስ ነፃነትን ፍለጋ በልቡ ተስፋውን ሰንቆ ያደረገው የህይወት ውጣ ውረድ ከስኬት ላይ ሳያደርሰው አልቀረም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic