የክሪምያ ባለስልጣናት ህዝበ ውሳኔው ለሩስያ ማድላቱን ይፋ አደረጉ | ዓለም | DW | 16.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የክሪምያ ባለስልጣናት ህዝበ ውሳኔው ለሩስያ ማድላቱን ይፋ አደረጉ

የምዕራብ ሀገራት ያወገዙት በዩክሬን ክሪምያ ልሳነ ምድር ህዝበ ውሳኔ ተጠናቀቀ። ለሞስኮ መንግስት የሚያደላዉ የክርምያ አስተዳደር ባለስልጣናት የህዝበ ዉሳኔዉ ዉጤት ከሩስያ ጋር ለመቀላቀል ማረጋገጫ የሰጠ መሆኑን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ። ከክሪሚያ አስተዳደር በወጣዉ መግለጫ መሰረት 93 በመቶ መራጭ፤

የክሪምያ ልሳነ ምድር ከዩክሪይን እንዲገነጠል ወስኖአል። ዛሪ በተካሄደዉ ህዝበ ዉሳኔ 1,8 ሚሊዮን የሚሆነው የክሪምያ ነዋሪ ለምርጫ ጥሪ የቀረበለት ሲሆን እንደ ሀገሪቱ አቆጣጠር እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ ህዝቡ ድምፁን ሲሰጥ ዉሎአል። የህዝበ ውሳኔው ይፋዊ እና የመጨረሻ ውጤት ዛሬ ሌሊት እስከ ሰኞ አጥቢያ ድረስ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል። የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ቅዳሜ ከቀትር በኃላ ባካሄደዉ ልዩ ስብሰባ፤ ዛሬ በክሪምያ የተደረገዉ ህዝበ ዉሳኔ ህገ-ወጥ ነዉ ሲል፤ ለማሳለፍ ያዘጋጀዉን ረቂቅ ዉሳኔ ሩስያ በፀጥታ ምክር ቤቱ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብትዋን ተጠቅማ ዉድቅ ማድረግዋ ይታወቃል። የዛሬውን ምርጫ የአውሮጳ ህብረት እና ዮናይትድ ስቴትስ ህገ-ወጥ እንደሆነ በመግለፅ ሩሲያ ላይ የበለጠ ማዕቀብ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል። ቀጣዩ ማዕቀብ ምን እንደሚመስል ነገ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ ዜና ፕሬዚዳንት ፑቲን እና የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዛሬ ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ የጋራ ነጥብ ላይ መድረስ እንዳልቻሉ የሜርክል ቃል አቀባይ ገልፀዋል። ፕሬዚዳንት ፑቲን የክራምያን የህዝበ ውሳኔ ውጤት እንደሚያከብሩ በመግለፅ ምርጫው በተባበሩት መንግሥታት አንቀፅ ላይ የሰፈረውን የህዝብ በራስ የመወሰን መብት የጣሰ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ሜርክል በበኩላቸው ወደ አካባቢው የበለጠ ታዛቢ ኃይል እንዲላክ አሳስበዋል። በሌላ በኩል የዮክራይን የመከላከያ ሚኒስትር ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ይገባሉ ብለው እንደማያምኑ፤ ይህ ከሆነ ግን ምንም እንኳን ሩሲያ ጠንካራ ኃይል ቢኖራትም፤ የሀገራቸው ጦር ድንበሩን ለማስከበር ዝግጁ እንደሆነ ገልፀዋል።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ