1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካታሎኒያ ሕዝበ ዉሳኔ ዉዝግብ 

ዓርብ፣ መስከረም 19 2010

ስጳኝ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1970ዎቹ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከመሠረተች ወዲሕ የዘንድሮዉን ያክል ፖለቲካዊ ቀዉስ ገጥሟት አያዉቅም።ካታሎኒያ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አላት።ከስጳኝ ምጣኔ ሐብት አንድ አምስተኛዉን ትይዛለች።

https://p.dw.com/p/2kzsm
PK der katalanischen Regierung in Barcelona
ምስል Reuters/J. Medina

የካታሎንያ ህዝበ ውሳኔ


የሰሜን ምሥራቅ ስጳኝ ራስ-ገዝ መስተዳድርን የወደፊት አስተዳደር ለመወሰን የፊታችን ዕሁድ ይደረጋል የተባለዉ ሕዝበ-ዉሳኔ የግዛቲቱን መሪዎች ከስጳኝ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እያወዛገበ ነዉ።የካታሎኒያ ሕዝብ ግዛቱ ከማድሪድ ማዕከላዊ መንግሥት ተገንጥላ ነፃነት እንድታዉጅ  አለያም የስጳኝ ግማደ ግዛት እንደሆነች እንድትቀጥል የፊታችን ዕሁድ በድምፁ እንዲወስን የግዛቲቱ መሪዎች ጠይቀዋል።የስጳኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕዝበ-ዉሳኔዉን «ሕገ-ወጥ» በማለት ዉቅድ አድርጎታል።የሐገሪቱ መንግሥትም ሕዝበ-ዉሳኔዉ እንዳይደረግ ለመከልከል በርካታ ፖሊስ በግዛቲቱ አስፍሯል።ነፃነትን የሚደግፉት  የግዛቲቱ  ባለሥልጣናት ግን ለዕሁዱ ሕዝበ-ዉሳኔ ከ2300 በላይ ድምፅ መስጪያ ጣቢዎች መዘጋጀታቸዉን አስታዉቀዋል።የማድሪድ መንግስት ሕዝበ ዉሳኔዉ እንዳይደረግ ካገደ ግዛቲቱ በቀጥታ ነፃነት እንደምታዉጅ የሚያስጠነቅቁም አሉ።።የካታሎኒያ ፕሬዝደንት ካርሌስ ፑግዴሞንት እንደሚሉት ግን ነፃነት ማወጅ ሕዝበ-ዉሳኔዉን አይተካም።
 

«ጉዳዩን ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ።ሕዝበ-ዉሳኔዉ (ቢታገድ) በተናጥል ነፃነት ማወጅ አማራጭ ሊሆን አይችልም።እነሱ (የስጳኝ ባለሥልጣናት) ሕዝበ ዉሳኔዉ እንዲደረግ ሥለማይፈቅዱ በቀጥታ ነፃነት እናዉጅ የሚል አስተያየት አለ።ይሁንና ለሕዝበ ዉሳኔዉ ምትክ የለም።ሕዝበ-ዉሳኔዉ መሠረታችን ነዉ።ከዚያ ተነስተን፤ ዉጤቱ ነፃነትን የሚደግፍ ከሆነ ነፃነት ለማወጅ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ እርምጃዎችን እንወስዳለን።ሕዝበ-ዉሳኔ ማድረጉ አስቸጋሪ ቢሆንም ሕዝበ-ዉሳኔን በቀጥታ ነፃነት በማወጅ አንለዉጠዉም።»
የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት ሕዝበ-ዉሳኔዉ ቢደረግ አብዛኛዉ የግዛቲቱ ሕዝብ ነፃነትን ይመርጣል።ይሁንና ፖሊስ የድምፅ መስጪያ ካርድና ኮሮጆዎችን ጨምሮ ለዕሁዱ ሕዝበ-ዉሳኔ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን እየለቀመ ነዉ።ስጳኝ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1970ዎቹ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከመሠረተች ወዲሕ የዘንድሮዉን ያክል ፖለቲካዊ ቀዉስ ገጥሟት አያዉቅም።ካታሎኒያ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አላት።ከስጳኝ ምጣኔ ሐብት አንድ አምስተኛዉን ትይዛለች።

Spanien - Unterstützer für das katalanische Referendum in Madrid
ምስል Pedro Casas

ነጋሽ መሐመድ

ገበያው ንጉሴ
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ