የካምፓላው የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ጉባዔ | ኢትዮጵያ | DW | 24.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የካምፓላው የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ጉባዔ

ባለፉት ሁለት ቀናት በዩጋንድ መዲና ካምፓላ ውስጥ በአፍሪቃ ስለሚገኙ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ዕጣ ፈንታ የመከረ በዓይነቱ የመጀመሪያው ዓቢይ ጉባዔ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

default

ሱዳናውያን ስደተኞች በቻድ መጠለያ ጣቢያ

በዚሁ የአፍሪቃ ሕብረት ባዘጋጀው ጉባዔ ላይ ከሀምሳ ሶስቱ አባል ሀገሮች መካከል ከአርባ ስድስቱ የተውጣጡ ፖለቲከኞችና ጠበብት፡ እንዲሁም በርካታ የርዳታ ድርጅቶች ተወካዮች ተካፋዮች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ በተመድ ዘገባ መሰረት፡ አፍሪቃ አስራ ሰባት ሚልዮን ስደተኞችና ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፡ ይህ በዓለም ካሉት ስደተኞች በጠቅላላ አንድ ሶስተኛውን ይሸፍናል።

ጉባዔው በተከፈተበት ስነ ስርዓት የተገኙት የአፍሪቃ ሕብረት ሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ዣን ፒንግ በሚልዮን የሚቆጠሩት ስደተኞችና ተፈናቃዮች ችግር የመላውን አህጉር መረጋጋት እንዳያናጋ ማስጋቱን ገልጸዋል። የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ኮሚሽነር አንቶንዮ ጉተረሽም ለተሰብሳቢዎቹ ባደረጉት ንግግር፡ በዓለም የስደተኞች ቁጥር መቀነሱ የሚያበረታታ መሆኑን ቢገልጹም፡ ዘጠና አምስት ከመቶው ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ አሁንም በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ መኖር መቀጠሉ የስደተኞቹ ችግር ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን በማመልከት የአህጉሩ መንግስታት መሪዎች የስደተኞቹን ስቃይ የሚያበቃበትን ዘዴ እንዲሹ ተማጽነዋል።

Tschad Flüchtlingslager für Flüchtlinge aus Darfur Sudan Kinder

ህዝብ ለሚፈናቀልበት ድርጊት ድርቅን እና ጎርፍን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ተጠያቂዎች መሆናቸውን ጉተረሽ በመጥቀስ የፊታችን ታህሳስ በኮፐንሀገን በሚደረገው የተመ የአየር ጸባይ ተመልካች ጉባዔ ላይ አፍሪቃ የአየር ጸባይ ለውጥ በአፍሪቃ ላይ የደቀነውን ችግር ለመቀነስ የሚያስፈልገውን ርምጃ እንዲያጤነው ሀሳብ ሰንዝረዋል።

የሚሰደደው ህዝብ ቁጥር መብዛት አህጉሩን አብዝቶ መጉዳቱን በጉባዔው ከተሳተፉትና ሰፊ ርዳታ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ የሆነው የዓለም የቀይ መስቀል ማህበር ተወካይ ወይዘሮ ሌና ቤርሌሞም አስታውቀዋል።

« አፍሪቃ በዚህ ችግር ተጎድታለች። በመሆኑንም፡ አሁን በካምፓላ የተካሄደው የስደተኞችን ጉዳይ ያጤነው ጉባዔ ለፓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ድርጅቱ፡ እአአ በ 2008 ዓም በአፍሪቃ ሁለት ነጥብ አራት ሚልዮን ስደተኞችን ረድቶዋል።

ከነዚሁ መካከልም ብዙዎቹ በሱዳን፡ በሶማልያ፡፡በኬንያ እና በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ህዝብ ህልውናውና የደህንነት ዋስትናው በማይከበርበት ጊዜ አካባቢውን ለቆ መሰደድ ይገደዳል። የሲቭሉ ህዝብ የሰብዓዊ መብት የሚከበር ከሆነ ግን አካባቢውን ለቆ የሚፈናቀለው ሰው ቁጥር ይቀንሳል። »

በአፍሪቃ የሚገኙትን የስደተኞቹን ጊዚያዊ ችግር ማቃለል ብቻ ሳይሆን የስደት መንስዔ ናቸው ተብለው ለሚጠቀሱት ጦርነትን እና ክትትልን፡ እንዲሁም፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የአየር ጸባይን ለመሳሰሉት ምክንያቶችም ዘላቂውን መፍትሄ የማፈላለግ ዓላማ ይዞ በተነሳው የካምፓላው ጉባዔ ፍጻሜ ላይ አንድ ሰነድ ተፈርሞዋል። የስደት መንስዔዎች በሚገባ የሚታዩበትና ትክክለኛው የመፍትሄ ሀሳብ የሚቀርብበት አሰራር ወሳኝ መሆኑን ጉባዔውን ያስተናገደችው የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ አስታውቀዋል። ስደተኞች በሚኖሩባቸው ሀገሮች ውስጥ የሚዋሃዱበትና የያሉበትን ሀገር ዜግነትም ማግኘት የሚችሉበት ድርጊት አንድ የመፍትሄ ርምጃ ሊሆን እንደሚችልም ዩጋንዳዊው ፕሬዚደንት አክለው ሀሳብ አቅርበዋል። በትናንቱ ዕለት በካምፓላ የተፈረመው ሰነድ የስደተኞቹ በተለይ ችግር ሊቀረፍበት፡ እንዲሁም፡ በተለይ ለተፈናቃይ ሴቶችና ህጻናትም ከለላ ሊሰጥበት የሚችሉበትን ሀሳቦች አካቶዋል። የዓለም የቀይ መስቀል ማህበር ተወካይ ወይዘሮ ሌና ቤርሌሞ በጉባዔው ፍጻሜ የተፈረመውን ሰነድ ለሰብዓዊ መብት መከበር ትልቅ ድርሻ የሚያበረክት ታሪካዊ ሰነድ ሲሉ አሞግሰዋል።

« የተፈናቃዮጭና የስደተኞች መብት በሚከበርበት ጊዜ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ይዞታ የሚከበርበት ሁኔታ ሊጠናከር ይችላል። ሲቭሉን ህዝብ በውዝግብ፡ በጦርነትና በግጭት ወቅት መከላከል አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የሰብዓዊ መብት በማይከበርበት ጊዜ ሁሉ በመጀመሪያ የሚጎዳው ሲቭሉ ህዝብ ነውና። እና አሁን ሰነዱ መፈረሙ ለኛ ከፍተኛ ትርጓሜ ይዞዋል። »

አፍሪቃውያኑ መሪዎች ይህንኑ ሰነድ ማጽደቃቸውን ያሞገሱት የተመ የሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት ኃላፊ ጆን ሆልምስ፡ በሰነዱ የሰፈሩት ሀሳቦች ተግባራዊ እስካልሆኑ ድረስ ችግሩ ይበልጡን ሊባባስ እንደሚችል ስጋታቸውን እንዲህ እንዲህ ገልጸዋል።

« በተለይ የወደፊቱ ሁኔታ ነው እኛን የሚያሳስበን። ምክንያቱም አሁን የምናየው የተፈጥሮ አደጋ እየተበራከተና እየተጠናከረ መምጣቱን ነው። እኛ ይህንን ለመቋቋም ገና አልተዘጋጀንም። የአየር ጸባይ ለውት ከቀጠለ በውሃ፡ በመሬት፡ በተፈጥሮ ሀብት የተነሳ ውዝግብ ሊነሳ ይችላል። ይህም የብዙ ህዝብ እንቅስቃሴን ያስከትላል። እንደሚባለው፡ እአአ በ 2020 እና 2030 ዓም በነዚሁ ውዝግቦች ሰበብ የተፈናቃዩ ቁትር ወደ ሀምሳ ሚልዮን ይደርሳል። »

በካምዓላው ጉባዔ አርባ ስድስት ሀገሮች ቢወከሉም፡ ከዩጋንዳ ሌላ ሶስት ሀገሮች፡ ማለትም፡ ዚምባብዌ፡ ዛምቢያ እና ሶማልያ ብቻ ነበሩ በመሪዎቻቸው ፡ እንዲሁም ኢኳቶርያል ጊኒና ናሚቢያ ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትሮቻቸው አማካኝነት የተወከሉት።

አርያመ ተክሌ/መስፍን መኮንን

DW/DPA

ተዛማጅ ዘገባዎች