የኦብነግና የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነትና ልዩነቱ | ኢትዮጵያ | DW | 06.07.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኦብነግና የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነትና ልዩነቱ

ኢትዮጵያ ከኦጋዴን ነፃ አዉጪ ግንባር ኦብነግ አንድ አንጃ ጋር የሠላም ዉል ለመፈራረም መስማማቷን አስታወቀች።ኦብነግ የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ጉዳይ ተጠሪ አቶ ሐሰን አብዱላሒ ግን ሥምምነት ተደረገ መባሉን አልተቀበሉትም።

default

Flagge Fahne Äthiopien

05 07 10

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈዉ ሳምንት እንዳስታወቀዉ ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦብነግ) አንድ አንጃ ጋር የሠላም ዉል ለመፈራረም መስማማቱን አስታዉቋል።የኦብነግ መሪዎች ግን ሥምምነቱን-አንዳዶቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ፕሮፓጋንዳ ሲሉት ሌሎቹ ደግሞ ከግለሰብ ጋር የተደረገ በማለት አጣጥለዉታል።ተስማማ የተባለዉ አንጃ መሪዎች ግን እስከ ዛሬ በይፋ ያስታወቁት ነገር የለም።ለምን?-የስምምነቱ መደረግ-አለመደረግ እየጠየቅን ሥለ አካባቢዉ ሠላም ከአካባቢዉ ፖለቲካዊ ሁኔታ አዋቂ ጋር ላፍታ እንወያያለን-አብራችሁኝ ቆዩ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ይደገፋል ከሚለዉ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር ኦብነግ አንድ አንጃ ጋር እየተደራደረ መሆን ካስታወቀ-ወር በለጠዉ።የድርድሩ ዜና ከአዲስ አበባ ከመሰማቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ግን በድንበር ግዛት ይገባኛል ሠበብ የሚወዛገቡ-የሚጋጩ፥የሚካሰሱት ኤርትራና ጅቡቲ ደም ያፋሰሰዉን ዉዝግብ በሰላም ለመፍታት በቀጠር ሸምጋይነት እየተደራደሩ መሆናቸዉ ከወደ ዶሐ ሽዉ ብሎ ነበር።በመሐሉ ኢትዮጵያ መረጠች።ኤርትራ ደግሞ ከጅቡቲ ጋር የሰላም ዉል ፈረመች።

አከታትላ ኢትዮጵያ ከኦጋዴን ነፃ አዉጪ ግንባር ኦብነግ አንድ አንጃ ጋር የሠላም ዉል ለመፈራረም መስማማቷን አስታወቀች።ኦብነግ የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ጉዳይ ተጠሪ አቶ ሐሰን አብዱላሒ ግን ሥምምነት ተደረገ መባሉን አልተቀበሉትም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሥለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀን ነበር።እስካሁን አልተሳካልንም።ሮይተር ዜና አገልግሎት የፌደራል ጉዳዮች ሚንስትር አቶ አባይ ፀሐዬን ጠቅሶ ባለፈዉ ሳምንት እንደዘገበዉ ግን ስምምነቱ የተደረገዉ እዚሕ ጀርመን ዉስጥ እና ሰላሐዲን ማኦ ከሚመሩት የኦብነግ አንጃ ጋር ነዉ።በሮይተር ዘገባ መሠረት ስምምነቱ ከተደረገ ሰወስተኛ ሳምንቱ-ዜናዉ ይፋ ከወጣ ደግሞ ሳምንት አለፈዉ።
የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ አዋቂ አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የስምምነቱ ዝር ዝር ይዘት፥ የተሰማሚዎቹ ማንነት ግን ዛሬም በዉል አይታወቅም።
የኤርትራና የጅቡቲ የሰላም ዉል፥ የኦብነግ አንድ አንጃም ቢሆን እና የኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነት-በርግጥ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ ነዉ ሊባል አይችልም።

ሶማሊያ ግን ያዉ ሃያ-አመት እንደኖረችበት እየተተረማመሰች ነዉ።ከሶማሊያ ትርምስ በፊት የኢትዮጵያዉ የኦጋዴን ግዛት ግጭት ቁርቁስ ነበር።ከኤርትሮ-ጅቡቲ ግጭት በፊት ደግሞ መቶ ሺዎችን ያፈሰሰዉ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ዉዝግብ ባለበት እደረገጠ-አስረኛ አመቱን ደፈነ።ሶማሌዎች-ከሶማሌዎች አልታረቁም።

የኦጋዴን ኢትዮጵያዉን ከኢትዮጵያዉያን ጋር አልተስማሙም።ሊያስማማቸዉ የሞከረዉም ጥቂት ያዉም ባለፍ አገደም ነዉ።ጅቡቲና ኤርትራ ግን እነሱም ለመስማት ፈቀዱ-አስማሚ ሸምጋይም አገኙ።አስደናቂዉ ግን የኤርትራ መንግሥት ስምምነቱን በይፋ መናገሩን አልፈቀደም።

ብቻ በዚሑ መሐል ሶማሊ ላንድም በሰላማዊ ምርጫ የመሪ ለዉጥ አደረገች።የኢኤርትራ-ጅቡቲ ከፊል ድብቅ ዉል፥ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦብነግ አወዛጋቢ ሥምምነት እና አለም የማያዉቃት የሶማሊላንድ ምርጫ ሰላም ለማያዉቀዉ ምድር ሠላም መፈየዱ አቶ ዩሱፍን እንደሚያምኑት አጠራጣሪ ነዉ። ምክንያት ዋናዉ ችግር ሌላጋ ነዉና።

የአፍሪቃ ቀንድ። ሌላ ተስፋ ግን ሌላ ቀቢፀ ተስፋ።አቶ ዩሱፍ ያሲንን አመሰግናለሁ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic