የኤውሮ ቀውስና የልማት ዕርዳታ | ኤኮኖሚ | DW | 01.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኤውሮ ቀውስና የልማት ዕርዳታ

የአውሮፓ ሕብረት በወቅቱ በዓባል ሃገራቱ የበጀት ቀውስ ተወጥሮ ነው የሚገኘው። በክፍለ-ዓለሚቱ ጥቂት ረዘም ካለ ጊዜ ወዲህ የዚህን የፊናንስ ቀውስ ያህል መወያያ የሆነ ሌላ ነገር ተፈልጎ አይገኝም።

የአውሮፓ ሕብረት በወቅቱ በዓባል ሃገራቱ የበጀት ቀውስ ተወጥሮ ነው የሚገኘው። በክፍለ-ዓለሚቱ ጥቂት ረዘም ካለ ጊዜ ወዲህ የዚህን የፊናንስ ቀውስ ያህል መወያያ የሆነ ሌላ ነገር ተፈልጎ አይገኝም። በመሆኑም የልማት ዕርዳታ ደጋፊዎች በቀውሱ የተነሣ ለድሆች አገሮች የሚሰጠው ዕርዳታ እንዳይጓደል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

የትናንሽ ፋብሪካዎች የሙያ ሥልጠና በኡጋንዳ፣ የዕርሻ ልማት ዕርዳታ በአፍጋሃኒስታን ወይም በምድረ-በዳ አካባቢዎች የውሃ አቅርቦትን ማራመድን የመሳሰሉት ተግባራት ለምሳሌ በአውሮፓ ሕብረት ከሚደገፉት ፕሬዤዎች መካከል የሚገኙት ናቸው። አውሮፓ በዓለም ላይ ታላቋ የልማት ዕርዳታ አቅራቢ ስትሆን ለድሆች አገሮች ከሚሰጠው ገንዘብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚመነጨውም ከህብረቱ 27 ዓባል ሃገራት ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ከዕርዳታ ፕሮዤዎች ሌላ ለታዳጊ ሃገራት ምርቶች ገበዮቹን በመክፈት በንግድ ረገድም ያግዛል። ሰባ ከመቶ ገደማ የሚጠጋው ወደ ሕብረቱ ገበዮች የሚገባው የእርሻ ምርት የሚመጣው ከአደጊዎቹ ሃገራት ነው። ይሁን እንጂ ይህ የስኬት ታሪክ አሁን አደጋ ላይ መውደቁ ነው የልማት ዕርዳታ ደጋፊዎችን የሚሰማቸው። በ U2 የሮክ ሙዚቃ ቡድን ባልደረባ በቦኖና በአበሮቹ የተቋቋመው የድጋፍ ድርጅት ዋን በወቅቱ የፊናንስ ቀውስ የተነሣ በድሃ አገሮች ትከሻ ላይ ቁጠባ እንዳይደረግ በጣሙን ነው የሚሰጋው።

«እኛ የዋን ዓባላት አሁን ይህ አደጋ መኖሩን የሚያሳይ፤ በዓለም ላይ የድሃ-ድሃ የሆኑት ሃገራት ለአውሮፓ ቀውስ ዋጋ ከፋይ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት አዲስ ዘገባ አቅርበናል»

U2 in Gelsenkirchen

ይህን የሚሉት የዋን የብራስልስ ቢሮ ባልደረባ ዮሃና ስትራትማን ናቸው። የዕርዳታው ድርጅት ዋን በዳታ ዘገባው የአውሮፓ ሕብረት ድህነትን ለመታገል የሚሰጠውን የገንዘብ ዕርዳታ ከፍ እንደያደርግ የገባውን ቃል መለስ ብሎ ይመረምራል። የሕብረቱ ዓባል ሃገራት እስከ 2015 ድረስ ከዓመታዊ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው አንጻር 0,7 ከመቶ የምትሆነዋን ድርሻ ለልማት ዕርዳታ ስራ ላይ ለማዋል ከዓመታት በፊት ራሳቸው ግዴታ መግባታቸው የሚታወቅ ነው። ግን ዮሃና ስትራትማን እንደሚሉት ከገቡት ቃል ኋላ ቀርተው ነው የሚገኙት።

«ከአሥር ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓመት የሕብረቱ የልማት ዕርዳታ አቅርቦት ሲያቆለቁል 14 ሃገራትም የፊናንስ ዕርዳታቸውን ቀንሰዋል። በ 2011 ዕርዳታው በአማካይ በ 0,43 ከመቶ ነበር ያቆለቆለው። በሌላ አነጋገር የሕብረቱ ዓባል ሃገራት የገቡትን ቃል ለማሟላት እስከ 2015 ዓመተ-ምሕረት ተጨማሪ 43 ሚሊያርድ ኤውሮ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

ዕርዳታው በወቅቱ ከ 50 ሚሊያርድ ኤውሮ ጥቂት ከፍ ያለ ሆኖ ነው የሚገኘው። ዋን በተሰኘው ድርጅት ግምት በ 2015 አጠቃላዩ የዕርዳታ አቅርቦት ከሕብረቱ የኤኮኖሚ ብቃት አንጻር 94 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ሊጠጋ የሚችል ነው። የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ከሚጨመረው ገንዘብ ግማሹን ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል በስራ ላይ ለማዋል ይፈልጋል። ይሁንና በዚህ ነጥብም አንዳንድ ለጋሽ ሃገራት ከአቋሙ እንዳፈነገጡ ነው ስትራትማን የሚናገሩት።

«እዚህ ላይ ከግባችን በሃያ ሚሊያርድ ኤውሮ ርቀን ነው የምንገኘው። ማለት የአውሮፓ ሕብረት በዓለምአቀፍ ደረጃ ስኬታማ ቢሆን እንኳ ብዙ ስራ ይጠብቀናል ማለት ነው»

የአውሮፓ ሕብረት የራሱን የፊናንስ ቀውስ ለማረቅ ቁጥር ስፍር የሌለው ገንዘብ ማፍሰስ እንደሚኖርበት ሲታሰብ ይህ በመሠረቱ ከባድ ተግባር ነው የሚሆነው። ሕብረቱ የስፓኛን ባንኮች ከክስረት ለማዳን ብቻ 100 ሚሊያርድ ኤውሮ ያቀርባል። ስለዚህም ብዙዎች ተመራማሪዎች ተሥፋ ሰጭ ሁኔታ አይታያቸውም። ለምሳሌ ያህል ቦን ውስጥ ተቀማጭ የሆነው የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ማሪዮ ኔግረ የአውሮፓ ሕብረት በገባው ቃል መሠረት ዕርዳታውን ከፍ ማድረጉን ብዙም አስተማማኝ አድርገው አይመለከቱትም።

«ምናልባት ከዚህ ግብ ልንደርስ አንችልም። አማካዩ የወቅቱ አሃዝ የሚያመለክተው በዚያ አቅጣጫ እያመራን አለመሆኑን ነው። በዚህ ዓመት ሂደቱ አቆልቋይ ሲሆን የዓባል ሃገራቱም ወኔ ያነሰ ሆኖ ነው የሚገኘው»

ለነገሩ የልማት ዕርዳታው ገንዘብ በሰፊው መቆረጡ በርካታ የአውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራት እንደ ስፓኛና እንደ ግሪክ ሁሉ በቀውሱ የተጎዱ መሆናቸው ሲታሰብ ብዙም አያስደንቅም። እርግጥ በሌላ በኩል የልማት ዕርዳታውን ከፍ ያደረጉ ሃገራትም አሉ። ከነዚሁ መካከል ለምሳሌ ጀርመንን፣ ስዊድንንና ቤልጂግን የመሳሰሉት ይገኙበታል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ከልብ ከተፈለገ በመሠረቱ በቀውስ ሰዓትም መርዳት እንድሚቻል ነው።

ለማንኛውም የመስኩ ጠበብት በጉዳዩ የሚተቹት ነገር አይጡ እንጂ በጥቅሉ የአውሮፓ ሕብረት ጥሩ ስራ እየሰራ በመሆኑ ይስማማሉ። ሕብረቱ የልማት ዕርዳታውን ገንዘብ ከፍ በማድረጉ ረገድ ጽኑ ዓላማ ያለው ብቸኛው የመንግሥታት ስብስብ እንደሆነም ነው የሚታመነው። የልማት ኮሜሣሩ አንድሪስ ፒባልግስም ታዲያ ሕብረቱ እስካሁን ባደረገው አስተዋጽኦ ኩራት ሳይሰማቸው አልቀረም።

«ባለፉት አሠርተ-ዓመታት የሰጠነው ዕርዳታ ለትክክለኛውሕዝብ መድረሱንና ትልቅ ጥቅም መስጠቱንም ለመረዳት ችያለሁ። በጅቡቲ በሚገኝ ሆስፒታል፣ ወይም በቫኑታቱ በቆመ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ወይም ደግሞ በአፍጋሃኒስታን በሚገኝ የከብት ሕክምና ላቦራቶሪይ ዕርዳታው ፍቱን ሆኖ መስራቱን ራሴ በገዛ ዓይኔ ያየሁት ነገር ነው»

የአውሮፓ ሕብረት በቅርቡ የወደፊት የልማት ዕርዳታ ዕቅዱን በይፋ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። በወቅቱ ዓባል ሃገራቱ ሕብረቱ ከ 2014 እስከ 2020 በሚያስፈልገው በጀት ላይ እየተደራደሩ ነው። እዚህ ላይ ደግሞ ምን ያህል ገንዘብ የፊናንሱን ቀውስ ለማለዘብ ጥቅም ላይ እንደሚውልና የልማት ዕርዳታው ለሕብረቱ ምን ያህል ክብደት እንዳለውም የሚለይለት ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

የሆነው ሆኖ በአውሮፓው ሕብረት ውስጥ የተከሰተው የበጀት ቀውስ በቀላሉ መፍትሄ ማግኘቱን በቀር በወቅቱ እንዲህ ብሎ መናገሩ ቀላል ነገር አይሆንም። በቀውሱ ክፉና የተመታችው ግሪክ አልጋ ላይ ተጋድሞ ከሚያጣጥር ሕመምተኛ ብዙም የተለየች አይደለችም። በስፓኝም ቢሆን የኤውሮው ቀውስ ተጽዕኖ አስከፊና አስደንጋጭ መልክ እየያዘ በመሄድ ላይ ነው።

በዋና ከተማይቱ ማድሪድ ለወትሮው ባለጸጎች በሚኖሩበት ቀበሌ በትሬስ-ካንቶስ ሳይቀር አንዲት ነዋሪ እንደምትለው ዜጎች ከቀይ መስቀል ማሕበር የምግብ ዕርዳታ እስከመቀበል ደርሰዋል።

«እኔም በኤውሮ ቀውስ የተነሣ ነው ከዚህ ሁኔታ ላይ የወደቅኩት። ቀድሞ በሣምንት አምሥት ቀን በአጽጂነት እሰራ ነበር። ግን ከማጸዳቸው አምሥት ቤቶች አሁን የቀሩኝ ሁለት ብቻ ናቸው። በወቅቱ በወር 500 ኤውሮ ነው የማገኘው። እዚህ የምመጣው ደግሞ ሌላ የተሻለ ስራ ለማግኘት ባለመቻሌ ነው»

ስፓን ውስጥ ስራ አጥነት ዛሬ በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን በወቅቱ መጠኑ 25 በመቶ ገደማ ተጠግቷል። ይህ ደግሞ የአገሪቱ ቀይ መስቀል ባልደረባ ላውራ ቴይዶር እንደሚሉት ሰውን ይበልጥ የዕርዳታ ጥገና እያደረገ ነው።

«ቀድሞ የኛን ዕርዳታ የሚሹት ከሁሉም በላይ የውጭ ተወላጆች ነበሩ። ባለፉት ጊዜያት ግን ወደኛ የሚመጡት ስፓኞች ቁጥር እየጨመረ ነው የሄደው»

የግሪክ ሁኔታም ከዚህ ይብስ እንደሆን እንጂ አይተናነስም። በኢጣሊያና በሌሎች የበጀት ኪሣራ ከባድ የቁጠባ ፖሊሲን በጠየቀባቸው ሃገራትም ሕብረቱ ብዙ ገንዘብ በማፍሰስ መቀጠሉ የሚቀርለት አይመስልም። ተቀዳሚው ዓላማ የኤውሮን ምንዛሪ ሕብረት ከመፍረስ ጠብቆ ማቆየትና የሕብረቱ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ ግሪክን አስመልክተው በቅርቡ እንደተናገሩት የአውሮፓው ቤተሰብ እንዳይበተን ማድረግ ነው።

«ግሪክ የአውሮፓ ቤተሰብና የኤውሮው አካባቢ አካል ናት። እናም ይሄው ባለበት እንዲቀጥል ለማድረግ እንፈልጋለን። መላው የኤውሮ ሃገራት መሪዎች ግሪክ ግዴታዋን እስከተወጣች ድረስ በኤውሮ ዞን ውስጥ መቆየት እንዳለባት በማያሻማ ሁኔታ ነው ግልጽ ያደረጉት»

የኤውሮን ስብስብ ይዞ ማቆየቱ ታዲያ ትልቅ ዓላማ ሲሆን ይህን ለማሳካት ደግሞ የፈጀውን ያህል ይፍጅ ብዙ ገንዘብ መፍሰሱ ግድ ነው። በሌላ አነጋገር ይህ በዜጎች ዘንድ በሚቀጥሉት ዓመታት ወገብን ሸንቀጥ አድርጎ ማሰር ማለት ሲሆን ለልማት ዕርዳታ ተጨማሪ ገንዘብ መገኘቱ እንግዲህ ሲበዛ አጠራጣሪ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 01.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/15hF6

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 01.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/15hF6