የኤርትራውያን የተቃውሞ ሰልፍ በሮም | ራድዮ | DW | 25.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ራድዮ

የኤርትራውያን የተቃውሞ ሰልፍ በሮም

በኢጣሊያ የሚኖሩ ኤርትራውያን ባለፈው ወር በጀልባ አደጋ ያለቁ ዜጎችን ለማሰብ ዛሬ በሮም አደባባይ ወተዋል።

ጀርመንን ጨምሮ ከተለያዩ የኣውሮፓ ኣገሮች የመጡ ኤርትራውያንም በሰልፉ ላይ የተገኙ ሲሆን የሰልፉ ዓላማ የኣውሮፓ ህብረት ስደተኞችን ኣስመልክቶ ያለውን ኣሳሪ ህግ እንዲያሻሽል ለመጠቀቅ ነው ተብለዋል።

ሰልፈኞቹ የዚህ ሁሉ መከራ ዋናው መንስዔ ነው ያሉትን የኤርትራን መንግስትም ያወገዙ ሲሆን የኢሳያስ አፈወርቂን ፎቶግራፍ በአደባባይ ሲቀዱም ተስተውለዋል።

በርካታ ኤርትራውያን የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው ሞንቴቺቴሪዮ በሚባለው እና ከጣሊያን ፓርላማ ፊትለፊት ወደሚገኘው ታሪካዊ አደባባይ የተመሙት ዛሬ ከረፋዱ ጀምሮ ነበር። የሰልፉ ዓላማ ባለፈው ወር በላምፔንዱዚው የጀልባ አደጋ ያለቁትን ኤርትራውያን ለማሰብ ሲሆን ካነገቡኣቸው መፈክሮች መካከልም በርካቶቹ እነዚህኑ ሰማዕታት የሚያስታውሱ ነበሩ።

ሰልፈኞቹ ሞንቴቺቴሪዮ አደባባይ እንደ ደረሱም በኦርቶዶክስ በካቶሊክ እና በእስልምና ኃይማኖት አባቶች እየተመሩ ሙታኑን በጸሎት ኣስበዋል።እንደየ ኃይማኖቱ ወግ መሰረትም ስርዓተ ፍትኃት ተደርጎላቸዋል። በተለይም በሰልፈኞቹ የተዘጋኙት የሬሳ ሳጥኖች በቀሳውስቱ እየተመሩ እና በኣሳዛኝ ኤርትራዊ ዜማ ታጅበው ኣደባባዩን ሲዞሩ የዶቸቬሌው ዘጋቢ ተክለግዚ ገ/እግዚኣብሔር ከስፍራው እንደዘገበው በእንባ ያልተራጨ ሰልፈኛ ኣልነበረም።

ለቅሶ ይብቃ ከሚለው መፈክር በተጨማሪም ኤርትራ ክፍት ወህኒ ቤት ናት አንባገነንነት ይብቃ የኢሳያስ አፈወርቂ ኣንባገነናዊ ኣገዛዝ ይወገድ የሚሉ እና ሌሎችም መፈክሮች ተስተጋብተዋል። በትልቁ ተስሎ በቀይ X የተደረገበት የኢሳያስ አፈወርቂ ፎቶም ሲወገዝ እና ሲቀደድ ተስተውለዋል።

የዚህ ሰልፍ ዋናው ዓላማ በኢጣሊያ የዲሞክራሲያዊት ኤርትራ ሰልፍ ኣስተባባሪ አቶ ደስበለ መኃሪ እንደሚሉት በኣሰቃቂ ሁኔታ የሞቱትን ወገኖች ማሰብ ብቻም ኣልነበረም።የኢጣሊያ መንግስትም ሆነ የኣውሮፓ ህብረት ስለ ስደተኞች ያላቸውን ኣመለካከት እንደገና እንዲመረምሩ ለመጠየቅ እና ኣንባገነናዊውን የኣስመራ መንግስትም ለማውገዝ ጭምር እንጂ።

በሰልፉ ላይ ከኢጣሊያ ብቻም ሳይሆን ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ ስዊድን እና ኖርዌይም ሳይቀሩ ከኔዘርላንድ እና ከሌሎችም የኣውሮፓ ኣገሮች የመጡ ከ500 በላይ ኤርትራውያን ተገኝተዋል። በሰልፉ ላይ ለመገኘት ከጀርመን የመጡት ዶ/ር ሳህለ ተስፋዬም ለተለያዩ ኣገሮች የሚሰራጭ ያሉትን ፔቲሺን ለጣሊያን መንግስት ለማስጠት ይዘው መምጣታቸውን ለዶቸቬሌ ነግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ሮም የሚገኘውን የኤርትራ ኢምባሲ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ግን ኣልተሳካም።

ባለፈው ወር በደረሰው የላምፔንዱዚው የጀልባ አደጋ በአብዛኛው ምናልባትም ከሞላ ጎደል ኤርትራዊያን የሆኑ 366 ስደተኞች ህይወታቸውን ማጣታቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ 157 ያህል ደግሞ መትረፋቸው ኣይዘነጋም።

ጃፈር ዓሊ

ሂሩት መለሰ