የኢትዮጵያ ጦር ከባይደዋ መዉጣቱ | ኢትዮጵያ | DW | 18.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ጦር ከባይደዋ መዉጣቱ

የኢትዮጵያ ወታደሮች ከባይደዋ መዉጣታቸዉን አሶሲየትድ ፕረስ ትናንት አመልክቷል። መንግስት መፍትሄ ይፈለጋል ቢልም ወታደሮቹ ከተጠቀሰችዉ ስልታዊት የሶማሊያ ከተማ መዉጣታቸዉም በአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪዎችና የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ላይ ጫና እንደሚያስከትል እየተነገረ ነዉ።

«ከኢትዮጵያ ወታደሮች የተወሰኑት ከባይደዋ ወጥተዋል፤ አሁንም ግን በአካባቢዉ ወታደሮች ይገኛሉ። ሆኖም ግን ቀስ በቀስ ከመላ ሶማሊያ እንደሚወጡ እርግጥ ነዉ።»
መቅዲሹ የሚገኘዉ የዶቼ ቬለ ዘጋቢ ሞሐመድ ኦማር ሁሴን የኢትዮጵያ ወታደሮች ሙሉ ለሙሉ ከባይደዋ ከተማ እንዳልለቀቁ ነዉ የሚያመለክተዉ። አሶስየትድ ፕረስ ትናንት እንደዘገበዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ስልታዊቱን የባይደዋ ከተማ ለቅቆ ወጥቷል ባይ ነዉ። ሞሐመድ ግን አሁንም የኢትዮጵያ ወታደሮች በአካባቢዉ ማለትም ባይደዋ ዋና ከተማ በሆነችዉ በባይ ግዛት እንደሚገኙ እና ትናንትም የተወሰኑትን በስልክ ማነጋገር እንደቻለ ነዉ የገለጸልን። እንደእሱ አገላለጽም የተወሰኑ ወታደሮች ባለፈዉ እሁድና ሰኞ ቢወጡም የቀሩ አሉና እነሱም በቀጣይ ሳምንታት የሚወጡበት መርሃግብር በቅርቡ ይሰማል ተብሎ ይጠበቃል። እንዲያም ሆኖ ስለወታደሮቹ መዉጣት ከሶማሊያ መንግስት እስካሁን የተገለጸ ምክንያት የለም። ጋዜጠኛ ሞሐመድ ኦማር ሁሴን፤
«እንደሚታወቀዉ የኢትዮጵያ ወታደሮችና የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪዎች ባይደዋ ዉስጥ ይገኛሉ። አስቀድሞ ባይደዋን የተቆጣጠረዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት መሆኑ እዉነት ነዉ፤ እናም አሁን እዚያ ለሚገኘዉ የአፍሪቃ ኅብረት ጦር ማስረከባቸዉ እማይቀር ይሆናል። ትናንትናና ከትናንት ወዲያ የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር ሚስተር ፊቂ ከኢትዮጵያዉ አቻቸዉ ጋ ስለወታደሮቹ መዉጣት ለመነጋገር አዲስ አበባ ይገኛሉ።»


እሳቸዉ ሲመለሱም ከሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ምክንያቱ ሊታወቅ እንደሚችል ነዉ ሞሐመድ የሚገምተዉ። የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ጊና ሙፍቲ ግን ወታደሮቹን ደረጃ በደረጃ የማስወጣቱ ተግባር ቀደም ሲልም የነበረ እቅድ መሆኑን ነዉ የሚገልጹት።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከባይደዋ መዉጣታቸዉ ክፍተት ፈጥሮ በአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪዎች ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀርም የሚሉ ወገኖች አሉ። እንደ አሶሲየትድ ፕረስ ዘገባ የአፍሪቃ ኅብረት ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል አሊ አደን ሁመድ የኅብረቱ እና የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች አካባቢዉን ይቆጣጠራሉ የሚል እምነት ነዉ ያለዉ። ጋዜጠኛዉ ግን ክፍተት ይኖራል የሚለዉን ስጋት ይጋራል፤
«አዎ እኔም ይህ ክፍተት መፍጠሩ ጥርጥር የለዉም ባይ ነኝ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ወታደሮችና የአፍሪቃ ኅብረት ሠራዊት አካቢዉን በመቆጣጠሩ፣ በቅኝቱና አሸባብን በመከላከሉ ተግባር እጅ ለእጅ ተያይዘዉ ነበር የቆዩት። እናም እርግጥ ነዉ ክፍተት ይፈጠራል።»
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸዉ አሸባብ ተዳክሟል አካባቢዉንም የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይሎችና የሶማሊያ ወታደሮች መቆጣጠር ይችላሉ ባይ ናቸዉ፤
ቀደም ሲል ባኮባ ግዛት ዉስጥ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች አሁን እንደሌሉና አሁን የአሸባብ ታጣቂዎች እንደሚገኙበት ነዉ ሞሐመድ የገለጸዉ። ከመቃዲሹ ሁለት መቶ ስልሳ ኪሎሜትር በምትርቀዉና የባኮባ ግዛት ተጎራባች በሆነችዉ ባይወደዋ ግን አሁንም የቀሩ ወታደሮች መኖራቸዉን ሞሐመድ አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic