የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ጥበቃ ትግል፣ | ጤና እና አካባቢ | DW | 23.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ጥበቃ ትግል፣

ሴት ልጆችን መግረዝ ፤ መጥለፍ፤ አስገድዶ መድፈር ፣ ዘመናዊ ትምህርት እንዳያገኙ መከልከል፤ ይህን የመሳሰሉ ለሴቶች ልጆች አስከፊ ሁኔታዎች፣ በብዙ አካባቢዎች ይታዩባት በነበረችው እ ጎ አ የ 1950ኛዎቹ ኢትዮጵያ፤ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ የተባሉ

default

ኢትዮጵያዊት፤ ትምህርት ቤት ገብተው በከፍተኛ ደረጃ በውጭ ሀገር ጭምር የአካደሚ ትምህርታቸውን ሲከታተሉና ሲሠሩ ከቆዩ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው በተደጋጋሚ የተወደሰና የተሸለመ ፣ በሴቶች ለሴቶች የቆመውን «ኬ ኤም ጂ ኢትዮጵያ» የተባለውን ድርጅት መሠረቱ። እናም ዛሬ ብራሰልስ ውስጥ በፖለቲካው መስክ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን «የንጉስ ቦዷንን የአፍሪቃ ልማት ሽልማት » ይቀበላሉ።

ከዕለታት አንድ ቀን ፣ በልጅነታቸው ፣ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ፣ በቁልምጫ ስማቸው «ቦጌ» «እኔ ከብት አይደለሁም፣ ከእንግዲህ እንደ ጥጃ የምነዳ አይደለሁም፤» የሚለውን ተቃውሞአቸውን ሳያሰሙ አልቀረም። በትውልድ ቦታቸው በደቡብ ኢትዮጵያ፣ የሴት ልጆችን የአስተዳደግ ሁኔታ በአጭሩ እንዲህ ነው የገለጡት።

Wasserholen im Fluss - Äthiopien

«ሴት ልጆች( ልጅገረዶች ) የሚያድጉት ይህን ማድረግ አትችሉም፤ ሴቶች ናችሁና፤ እንደዚህ አይኬድም፦ እንዲህ አይሣቅም፤ እንዲያ ዓይነት ፈግግታ ማሳየት የለም፤ እንዲህ ባላችሁ አትቀመጡ፤ እንደዚህ አይለበስም!። እንዲህ --እንዲህ እያሉ ነው ያሳደጉን። ነገር ግን ነጻነት ማለት ሁሉም ነው። ያለነጻነት ምንም ማሰብ አይቻልም።»

የዶክተር ቦጋለች፤ የነጻነት ትግል ሂደት የሚጀምረው፤ ከቤት ወደ ት/ቤት ካመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው። በልጅነት ፣ በድብቅ ት/ቤት ይሄዱ ነበር። ተሰጥዖ የነበራቸው ተማሪ ጽናታቸውን ጭምር ነበረ ያሥመሰከሩት። ወደ 2ኛ ደረጃ ተዛውረው ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ከአካባቢአቸው የመጀመሪያቱ ልጃገረድ ነበሩ። ነጻ የትምህርት ዕድል በማግኘት በመጀመሪያ ወደ እሥራኤል ከዚያም ወደ ዩናይትድ እስቴትስ ሄዱ። በዚያም ነው በወረርሺኝ በሽታዎች ጥናት የዶክተርነት ማዕረጋቸውን ያገኙት። አገሬን ልርዳ ብለው የተመለሱት ከ 16 ዓመት ገደማ በፊት ነው።

Flash-Galerie Dürre ohne Ende Äthiopien Landleben im Norden Rural life in Northern Ethiopia

«ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶችን ይዞታ እመለከት ነበር። ሴቶች ልጆች ከማግባታቸው በፊት፤ ሲገረዙ፣ ተደግሶ እንደበዓል ይከበር ነበር። ዘግናኝ ፤ አስፈሪ ነገር ነው! እናት ፤ ሴት ልጅዋን አስገርዛ ለጋባቻ ዕድሜ እንድትበቃ በማድረጓ ልዩ ኩራት ነበረ የሚሰማት።»

ቦጋለች ገብሬ፣ የሚናገሩትን ያውቃሉ። የ 12 ዓመት ልጅ ሳሉ በግርዛት ደምተዋል ተሠቃይተዋል፤ ቀጣዩ ትውልድ በዚያ መጥፎ ልማድ እንዳይጎዳ ፤ ለማስቀረት ነው ትግላቸው ። ለዚህም ነው ከእኅታቸው ጋር፤

(Kembatti Mentti Gezzima)KMG «የከምባታ ሴቶች ተባብረው ይሠራሉ »እንደማለት ነው፣ ይህን የመንግሥት ያልሆነ ድርጅት የመሠረቱት። በሴቶች ላይ የኃይል እርምጃ እንዳይፈጸም መታገል የአትማማቾቹ ተግባር ሆነ። በ 5,000 መነሻ ወረት፣ የጀመሩት ፕሮጀክት፤ ከጉድጓድ የሚጠጣ ውሃ ማቅረብ፤ መሸጋገሪያ ድልድይ መሥራት፣ በዚህና በመሳሰለው ተግባራቸው፤ እትማማቹ የመንደሩን ህዝብ አመኔታ አተረፉ። ከዚሁ መተማመን በመነሳት፤ ስብሰባዎችን ማዘጋጀት፤ ጥናትም እንዲካሄድ ማድረጉን ተያያዙት።

«ይህ የምታደርጉት ስህተት ነው፤ ወይም፤ መጥፎ ነው ብለን መጫን ሳይሆን፤ልጃገረዶች ሲገረዙ፤ በጤንነት፤ በህክምና ረገድ ያለውን ችግር በግልፅ እናስረዳቸዋልን። የሚያለቅሱም ነበሩ። በ 2002 ዓ ም፤ የመጀመሪያቱ ያልተገረዘች ልጃገረድ፤ በአደባባይ የጋብቻ ሥርዓት ፈጸመች።»

ያልተገረዘችውን ልጃገረድ ሙሽራ ለማየት ፤ያኔ በሺ የሚቆጠር ህዝብ ነበረ የተሰበሰበው። ለዓቅመ ሔዋን ያልደረሱ ልጅገረዶችም፤ «አልገረዘም፤ ከእኔ ተማሩ» የሚል የጽሑፍ ሰሌዳ ያሳዩ ነበር። ከዓመታት በኋላ ፣ የተባበሩት መንግሥታት ለልጆች የአስቸኳይ ሁኔታ እርዳታ አቅራቢው ድርጅት(ዩኒሴፍ) ያካሄደው ጥናት እንደሚያስረዳው፣ KMG ዘመቻ ባካሄደባቸው ቦታዎች ህዝቡ፤ በመቶ ሺ የሚቆጠር መሆኑ ነው፤ መቶ በመቶ የሴት ልጅ ግርዛት ተቃዋሚ መሆኑን አረጋግጧል። ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ፤ ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች አርእስትም አትኩረዋል።HIV/AIDS ፣ ቀጣይ ልማት፤ በተለይም የሴትና የወንድ መብት በእኩልነት እንዲከበር ጥረት ማድረጋቸውን እንደቀጠሉ ናቸው። ሁለት እትማማች የጀመሩት ንዑስ ፕሮጀክት ፤ አሁን ለትርፍ የማይሠራ አገር አቀፍ የመንግሥት ያልሆነ ድርጅት ለመሆን በቅቷል። ለሥራውም ዓለም አቀፍ ሽልማት እየቀረበለት ነው። ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ እንዴት እዚህ ደረጃ ደረሱ? አዎ ለዚህ ማን መመሥገን እንዳለበት ለእርሳቸው ግልፅ ነው።

«ወላጅ እናቴ ምስጋና ይግባት። ሹልክ እያልን ወደ ት/ቤት እንድንሄድ ትፈቅድልን ነበር። እኔ የማደንቃት አርአያ ናት። ለሴት ልጆቿ የተሻለ ነገር እንዲያጋጥማቸው ነበረ ፍላጎቷ! በሷ ጥረት ነው ነጻነቴን የተጎናጸፍሁ!»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ