የኢሬቻ በዓል አከባበር ቅድመ ዝግጅት | ኢትዮጵያ | DW | 25.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢሬቻ በዓል አከባበር ቅድመ ዝግጅት

በመጭዉ መስከረም  21 ቀን የሚከበረዉን የኢሬቻ በአል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም አመለከተ። በበአሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ የጦር መሳሪያ የታጠቁ የፖሊስ አባላት አይገኙም ተብሏል።በቦታዉ ሰንደቅ ዓላማ እንደማይዉለበለብም ተገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00

«ከከተማ ዉጭ ያለዉ ጥበቃ የተጠናከረ ይሆናል»

የአንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸዉ የተደረገዉ ቅድመ ዝግጅት በተግባር ላይ የሚዉል ከሆነ መልካም መሆኑን ገልጸዋል። 
አዲሱን አመት በሠላም ለመቀበልና አምላኩን ለማመስገን በየዓመቱ መስከረም ወር የኦሮሞ ህዝብ የኤሬቻ በዓልን በሆራ ሰርዴ ያከብራል።  ያለፈዉ ዓመት በዓል ግን እንደሁል ጊዜዉ በምስጋናና በፀሎት አልተጠናቀቀም ። ለፈጣሪያቸዉ ምስጋና ለማቅረብ በበዓሉ የታደሙ በርካታ ሰዎች ህይወታቸዉን አጥተዋል። በዚህ የተነሳ ያለፈዉ ዓመት  የኤሬቻ በዓል ዋይታና ሀዘን ያጠላበት ሆኖ አልፏል።
የዘንድሮዉ የኢሬቻ በዓል  በሠላም እንዲከበር  የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአባገዳወች ህብረት ጋር በመሆን ቅደመ ዝግጅት እንዳጠናቀቀ  የቢሮዉ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወይዘሮ አልፊያ ሀጅየሱፍ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ህዝቡ ዓሉን በሰላም እንዲያከብር ለማድረግም ስነ-ስርዓቱን  የሚያስተባብሩ  300 ወጣቶች በአባገዳወች ተመርጠዉ ከፖሊስ ጋ ስልጠና ወስደዋል።  
እንደ ወይዘሮ አልፊያ ገለፃ የቢሮአቸዉ ስራ በዋናነት በዓሉን ማስተዋወቅ ቢሆንም ህዝቡ በዓሉን በሰላም እንዲያከብር ለማድረግ የጦር መሳሪያ የታጠቁ የፖሊስ አባላት  በዓሉ  ወደ ሚከበርበት ቦታ አይገቡም።


በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት የክልልም ይሁን የፌደራል መንግስት ሰንደቅ ዓላማ  እንደዚህ ቀደሙ ለበዓሉ ማድመቂያ እንደማይዉለበለብም ተገልጿል።
በ 2009 ዓ/ም በተከበረዉ የኢሬቻ በዓል ላይ ሁለት የቅርብ ዘመዶቻቸዉን በሞት እንዳጡ የነገሩንና ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ  የክልሉ ነዋሪ እንደሚሉት በዓሉን ሰላማዊ ለማድረግ የተደረገዉ ቅድመ ዝግጅት በተግባር ላይ የሚዉል ከሆነ በአወንታዊ መልኩ ይመለከቱታል።
ባለፈዉ ዓመት በበዓሉ ላይ ህይወታቸዉን ላጡ ሰዎች የቆመዉ የመታሰቢያ ሀዉልት ላይ የሰፈረዉ የጽሁፍ ይዘትም ዉይይት እየተደረገ እንደሚስተካከል ተገልጿል። ህዝቡ ለሞቱት ሀዘኑን የሚገልጽበትንና ሌሎች የአከባበሩ ዝርዝር ጉዳዮች መካተታቸዉ  እንዳስደሰታቸዉ ነዋሪዉ ገልጸዉ የታጠቁ ሀይሎች ጣልቃ እንዳይገቡ ማሳሰባቸዉን ግን አልዘነጉም።
በዘንድሮዉ የኢሬቻ በዓል  የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ ዓባላት ያለምንም ትጥቅም ቢሆን የበዓሉን ፀጥታ ለማስከበር በአካባቢዉ እንደሚሰማሩ ተገልጿል።በአባ ገዳወች በተመረጡ ወጣቶች አማካኝነትም ፍተሻ ይካሄዳል።ከከተማ ዉጭ የሚደረገዉ ጥበቃም የተጠናከረ ይሆናል ተብሏል።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic