1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሬቻ መታሰቢያ ሐውልት ተቃውሞና አዲስ ዓመት 

ዓርብ፣ ነሐሴ 26 2009

የዛሬ ዓመት ግድም በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት የሞቱትን ሰዎች ለማስታወስ የተሠራው ሐውልት መመረቁ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቁጣን ቀስቅሷል።  በኢትዮጵያ መንግስት የበዓል አከባበር መርሐ-ግብር በሚል ይፋ ያደረገው ዝግጅት ሌላናው መነጋገሪያ ርእስ ነበር።

https://p.dw.com/p/2jAhv
Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የዛሬ ዓመት ግድም መስከረም 22 ዓ ም በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት የሞቱ ሰዎችን ለማስታወስ ያሠራውን ሐውልት ባሳለፍነው እሁድ አስመርቋል፡፡ የሐውልቱ በመንግሥት ተሠርቶ መመረቅ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች አግራሞትን አጭሮ ቁጣንም አስነስቷል። በሌላ መልኩ መንግሥት የ2010 አዲስ ዓመትን ለ10 ቀናት በዘለቀ ጊዜ የአቀባበል ዝግጅት ለማድረግ መወሰኑም ሌላ ጥያቄ አጭሯል። 

ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናና አውታሮች አብይ መነጋገሪያ ከነበሩ ርእሰ ጉዳዮች መካከል የዛሬ ዓመት ግድም በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት የሞቱትን ሰዎች ለማስታወስ በሚል ደብረ ዘይት ወይንም ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በመንግሥት ተሠርቶ የተመረቀው ሐውልት ይገኝበታል። ሐውልቱ ላይ  መታሰቢያነቱ «በድንገተኛ ሞት» ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች የሚል ጽሑፍም ይገኝበታል። በተለይ በድንገተኛ የሚለው ቃል በበርካቶች ዘንድ ተቃውሞ አጭሯል። በሐውልቱ ምረቃ ወቅት በመንግሥት የመገናኛ አውታሮች የቀረቡ ዘገባዎች «በተወሰኑ አካላት አነሳሽነት ምክንያት  በተከሰተ ግርግር እና መረጋገጥ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል» ሲሉም አትተዋል።   

እዝራ በረከት በፌስቡክ በሰጠው አስተያየት፦« የኢሬቻ እልቂት ሰለባዎችና ቤተሰቦቻቸው የሚፈልጉት ገዳዮቻቸውና አስገዳዮቻቸው ለፍርድ እንዲቀርቡና ለተጎጂ ቤተሰቦች የሕይወት ካሳ መንግስት እንድከፍል እንጂ ሐውልት አይደለም። ያለ ፍትህ መታሰቢያ የለም» ሲል ተቃውሞውን አስፍሯል። ሰላሚና በበኩሏ «ኢሬቻ ላይ ያለቁትን ወንድም እህቶቻችን ዛሬም ነገም በጥልቅ ሀዘን እናስባቸዋለን» ብላለች። 

Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

አልሚ አልማዝ ደግሞ፦  «ኢሬቻ ላይ የሞቱት ሰዎች ያለቁት በድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ከሰማይ በወረደ መብረቅ ነበር እንዴ?» ስትል አጠይቃለች። «ዛሬ ደግሞ "ለኢሬቻ ሰማእታት መታሰቢያ ሀውልት ገንብቼ ልመርቅ ነው" እያለልህ ነው። የጉድሀገር» ሲል አግራሞቱን በትዊተር የማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ያሰፈረው አብዲ ለሜሳ ነው። 

ወዳጆ ተኮር በፌስቡክ ያሰፈረው አስተያየት እንዲህ ይነበባል፦ «ሞቱ ድንገተኛ ነዉ፡፡ አሟሟቱ ግን...እ/ር እና መንግሰትይወቁት።» ታሪኩ ተሾመ በበኩሉ፦ «ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል» ብሏል።  

ከኢትዮጵያ በዋትስአፕ ከደረሱን መልእክቶች መካከል ደግሞ« የኔ አስተያየት፣ ራሱ ገድሎ ወይም ለሞታቸው ምክንያት ሆኖ ሲያበቃ ሀውልት መስራት ቀልድ/ፌዝ ነዉ» የሚል አስተያየት ይገኝበታል። 

ሐውልቱ ባሳለፍነው እሁድ ሲመረቅ በስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናትም መገኘታቸው ተዘግቧል። 

አድማጮች አሁን ደግሞ ወደ ሁለተኛው ርእሰ ጉዳያችን እንሻገር። “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ መንግስት አዲሱን የ2010 ዓመት ከወዲሁ ለመቀበል ልዩ ዝግጅት መጀመሩን ይፋ አድርጓል። የአዲስ ዓመት አቀባበል ልዩ ዝግጅቱ ከዛሬ እንደሚጀምርም አዘጋጆቹ ይፋ አድርገዋል። 

አዲስ ዓመት እስኪጠባ ድረስ ያሉት ቀናት ዛሬን ጨምሮ የተለየ ስያሜም ተሰጥቷቸዋል።የዛሬው ዕለት ««የፍቅር ቀን» በሚል ነው የተሰየመው። የኢትዮጵያን 13 ወራት ልዩ ቀናት ማክበሩ ጥሩ ነው» ሲል በእንግሊዝኛ የዶይቸ ቬለ ፌስቡክ ገጽ ላይ አስተያየቱን ያሰፈረው ጤናው ፈንታው ነው። አዲሱ ጌትነት ከጤናው በተቃራኒ፦ «ጥላቻን ለአርባ አመት ሰብኮ ፍቅርን በአስር ቀን መጠበቅ ከሞኝነት ወጪ ምን ይሉታል?» ብሏል። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ካሳሁን ተስፋዬ «አሜን ሰላም ያድረገው» የሚል አጠር ያለ አስተያየት ሲሰጥ፤ በላይ አድማስ በበኩሉ « ሰንት ወላጅ አልባ የጎዳና ተዳዳሪወችን የበዓል እለት መርዳት እየተቻለ የህዝብ ሀብት በሠበብ ወጪ አድርጎ ለመብላት የታሠበ ሴራ ሰለሆነ ይመቻቸው ይህ ጊዜ አኪጥላቸው ድረስ» ብሏል።  «እንኳን አደረሳችሁ»  የኪዳነ ከበደ አጠር ያለ መልእክት ነው። 

በዋትስአፕ ከተላኩልን የጽሑፍ እና የድምጽ መልእክቶች መካከል ደግሞ ዘለግ ያለ አስተያየት ከዩናይትድ ስቴትስ ደርሶናል። «8 ሚሊየን ህዝብ ተርቦ ለነሱ አስቸኩይ የምግብ እርዳታ እያስፈለገ የአዲስ አመትን እና የብሄር ብሄረሰብ ቀን እናከንራለን በሚል እጅግ በርካታ ሚሊየን ብሮችን ማባከን አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም» የሚለው የዩናይትድ ስቴትሱ አድማጮቻችን አስተያየት «አዲስ ዓመትን ህዝብ መንግስት ባያስገድደውም እንዳቅሙ ያከብረዋል የህዝብን በአል ለፕሮፖጋንዳ መጠቀም እንደ ዝርፊያ ነው የሚቆጠረው» በማለት ይጠናቀቃል። «ያሳዝናል ህዝብ እየተራበ እነሱ ምክንያት ፈልገው ይደግሳሉ» ከሳዑዲ ዓረቢያ በዋትስአፕ የደረሰን መልእክት ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ