1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግምገማ እና ሹም ሽር መልስ ይሆናል?

ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 1 2008

ኢትዮጵያን የሚመራዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በቅርቡ ካካሔደው ግምገማ በኋላ በሥራ አስፈጻሚዎቹ ዘንድ ሹም ሽር ሊያካሂድ መሆኑን እየተናገረ ነው። የገዢው ግንባር ሹም ሽርም ይሁን ግምገማ ግን ለውጥ ለማምጣቱ በርካቶች ጥያቄ አላቸው።

https://p.dw.com/p/1JwJD
Äthiopische Volksgruppe der Oromos Protest
ምስል Getty Images/AFP

[No title]

ከሩብ ምዕተ-ዓመት በላይ በስልጣን ላይ የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት ተሿሚዎቹን ሊገመግም እንደሆነ አስታውቋል።ከጠቅላይ ሚንስትር ሐይለ ማርያም ደሳለኝ አማካሪዎች መካከል አቶ አባይ ፀኃዬ ግንባሩ የመንግስት ተሿሚዎችን «አመኔታ በሰራተኛ፤በሕዝብ በፓርቲ ዘንድ አለው ወይስ የለውም? ውጤታማ ነው? ውጤታማ አይደለም?» ብሎ ሊገመግም እንደሆነ ጠቁመዋል።ሌላዉ የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምዖን በበኩላቸው «የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን በአዲስ መልክ እናደራጃለን» ሲሉ ተደምጠዋል።
የዶይቼ ቬለ የፌስቡክ ገፅ ተከታታዮች ግን የኢህአዴግ ሹም ሽር ለውጥ ማምጣቱን ይጠራጠራሉ። አስተያየት ከሰጡት አንዱ፤ ጌትነት በላይ «ኢህአዴግ እኮ በ1993 በክቶ እንደገና ታደስኩ ብሎ መቅረቡ ይታወሳል። መብከት፣ መበስበስ ከአንዴ በላይ ይደብራል። አሁን እኮ በህዝብ ላይ ጦርነት በይፋ ታውጇል። ማንን ለማስተዳደር ነው መታደስ የሚያስፈልገው?» ሲሉ ይጠይቃሉ። «አንድን ጥያቄ መፍታት ጥያቄውን በቅጡ ከመረዳት ይጀምራል» የሚሉት ዮሐንስ አያሌው «ገዢው ፓርቲ የሚያልመው ለውጥ ከሕዝብ መሰረታዊ የለውጥ ጥያቄ» ጋር እንደማይጣጣም ፅፈዋል። ቹቹ ደግሞ «ላይኛውን ማን ያደራጀው? ሁሌ ታችኛው አመራር ጥፋተኛ ከተባለ የሱ አለቃስ ላይኛው ጤነኛ ይሆን?» ብለዋል።
Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker
ኢህአዴግ 'ተሐድሶ' ያስፈልገኛል ያለው የአስራ አምስት አመታት የስራ ክንውኑን በአራት ቀናት ከገመገመ በኋላ ነው። ግንባሩ ከዚህ ቀደም የገጠሙትን ፖለቲካዊ ቀውሶች በግምገማ ለመፍታት ቢሞክርም መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ግን የቻለ አይመስልም።የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ቻላቸው ታደሰ ኢህአዴግ የሚከተለውን የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት መርሕ «ያልተቀደሰ ጋብቻ» ይሉታል።
ይህ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሕ በአባል ድርጅቶች እና በግንባሩ መካከል ያለውን ግንኙነት ሚዛን አዛብቶት ቆይቷል። አራት ፓርቲዎችን የያዘው ኢህአዴግ በሥራ አስፈጻሚነት የሚያካሂዳቸው ሹም ሽሮች ውሃ ቅ ውሃ መልስ ናቸው እየተባሉ ይተቻሉ።ሰሞኑን ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትርነታቸው የተነሱት አቶ መኩሪያ ኃይሌ መልሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አማካሪ ሆነዋል። ኢህአዴግ አባል ያልሆኑ ግን ደግሞ በሙያቸው ብቁ ግለሰቦችን በሥራ አስፈጻሚነት ለመሾምም ዝግጁ አይመስልም።
Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri
ባለፈው ዓመት የተካሔደውን አገር አቀፍ ምርጫ በየክልሎቻቸው መቶ በመቶ ድምፅ በማግኘት ያሸነፉት ብአዴን እና ኦህዴድ ዘንድሮ የተቀሰቀሰባቸውን ጥያቄዎች መመለስ የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ እና ሕዝባቸውን ማረጋጋት ተስኗቸዋል። ሁለቱ ፓርቲዎች በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተዓማኒነትም ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ይመስላል። በዶይቼ ቬለ የፌስ ቡክ ገፅ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት አባ ጨብሳ «ሁለቱም ዱቄት ናቸው።» ይላሉ። ጃክ ካሬስ በበኩላቸው «ሁለቱም እኮ አቅም የላቸውም በራሳቸው በራሳቸው ምንም ነገር መወሰን አይችለም ስለዚህ በህዝቡም ዘንድ ተቀባይነታቸው አይታየኝም» ብለዋል። ሳዴን ሳዶ ሳዴን ፓርቲዎቹን «የህወሃት ጉዳይ አስፈፃሚዎች» ይሏቸዋል። ይነጋል በሚል ሥም አስተያየት ያሰፈሩ ሌላ ግለሰብ «የሞግዚት አስተዳደር እንዴት ተቀባይነት ይኖረዋል?» ብለው ጠይቀዋል። አቶ ቻላቸው ታደሰ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎችን የሚያስተዳድሩት ኦሕዴድ እና ብአዴን እና በግንባሩ መካከል ያለው የስልጫን ክፍፍል ፍትኃዊ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ