የአፍቃኒስታን ሠላምና የጀርመን ሠራዊት ተልዕኮ | ዓለም | DW | 18.08.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍቃኒስታን ሠላምና የጀርመን ሠራዊት ተልዕኮ

ወታደሩ ግዳጁን ለመወጣት ለቀቅ ያለ ደንብ ያስፈልገዋል።እስካሁን በነበረዉ የዘመቻ ሕግ መሠረት ወታደሮች የጦር መሳሪያቸዉን የሚተኩሱት በራሳቸዉ ወይም በባልደረቦቻቸዉ ላይ አደጋ ሲጋረጥባቸዉ ብቻ ነዉ።

default

ወታደሩ በግዳጅ ላይ

18 08 09

ሰሜን አፍቃኒስታን የሠፈረዉ የጀርመን ሠራዊት ከቅርብ ጊዚያት ወዲሕ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየተፈፀሙበት ነዉ። የጥቃቱ ማየል የተለያዩ ወገኖች ፦ሠራዊቱ ከዚሕ ቀደም የተሰጠዉ የማረጋጋት ተልዕኮ መሻሻል አለበት የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ምክንያት ሆኗል።መከላከያ ሚንስትር ፍራንስ የሴፍ-ዩንግ ከዚሕ ቀደም እንደሚሉት ሁሉ አሁንም የሠራዊቱ ተልዕኮ መዋጋት እንዳልሆነ እየተናገሩ ነዉ።በተጨባጭ ግን ሠራዊቱ የጦር መሳሪያዉን የሚጠቀምበት ሕግ ተቀይሯል።አዲሱ ሕግ ቀላል ግልፅና ለወደፊቱ ወታደሮች ፈጥነዉ እንዲተኩሱ የሚፈቅድ ነዉ።ዳንኤል ሼሽኬቪትስ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የአፍቃኒሲታን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊደረግ ሁለት ቀን ሲቀረዉ ዛሬ ያቺ ሐገር ከሰሜን-እስከ ደቡብ፥ ከርዕሠ-ከተማ ካቡል እስከ ኡርዝጋን ግዛት በነብሰ ገዳዮች ጥይት፥በአጥፍቶጠፊዎች ቦምብ፥ በሸማቂዎች ሮኬት እየተተራመሰች ነዉ።አንፃራዊ ሠላም በሰፈነበት ሰሜናዊ አፍቃኒስታን የሠፈረዉ የጀርመን ሠራዊት ዛሬ በርግጥ የደረሰበት ጥቃት የለም።እስካሁን ግን የተደጋጋሚ ጥቃትና ኢላማ እንደሆነ ነዉ።

የሠራዊቱን የእስካሁን ተልዕኮ የሚቃወሙ ወገኖች ሠራዊቱ በአፍቃኒስታን ካለዉ የጦርነት ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ግዳጅ እንዲሰጠዉ አጥብቀዉ ሲከራከሩም ነበር።እነዚሕ ወገኖች እንደሚሉት ወታደሩ ግዳጁን ለመወጣት ለቀቅ ያለ ደንብ ያስፈልገዋል።እስካሁን በነበረዉ የዘመቻ ሕግ መሠረት ወታደሮች የጦር መሳሪያቸዉን የሚተኩሱት በራሳቸዉ ወይም በባልደረቦቻቸዉ ላይ አደጋ ሲጋረጥባቸዉ ብቻ ነዉ።

በየትኛዉም ሁኔታ ቢሆን ወታደሩ አደጋ ያደርሳል ብሎ በጠረጠረዉ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ ተኩስ ከመክፈቱ በፊት በእንግሊዝኛ ወይም ባካባቢዉ ቋንቋ «ቁም---እንዳትንቀሳቀስ ልተኩስ ነዉ» የሚል የቃል ማስጠንቀቂያ ማሰማት አለበት።መከላከያ ሚንስትር ፍራንስ ዮሴፍ ዩንግ ያፀደቁት አዲሱ ሕግ እስካሁን ታትሞ አልወጣም።ሁሉም የሚያስማሙበት ነጥብ ግን ሕጉ ወታደሮች ለአደጋ የሚያጋልጣቸዉ ሁኔታ ካጋጠማቸዉ መተኮስ እንዲችሉ የሚፈቅድ ነዉ።

በጀርመን ፌደራላዊ ጦር የየምዕራብ ክፍለ-ሐገራት የወታደሮች ማሕበር ሊቀመንበር ቶማስ ዞህስት እንደሚሉት የሕጉ መሻሻል በጣም አስፈላጊ ነዉ።

«በጣም አስፈላጊ ነዉ።ወታደሩ የባላጋራዉ ማለት የጠላቱን ሐይል መመከት አለበት።ለዚሕም ነዉ የዘመቻዉን ሕግ ሙሉ በሙሉ ማሻሻል የሚያስፈልገዉ።መሆን የሚገባዉ ሕጉ ሁል ጊዜ ካለዉ ተጨማጭ ሁኔታና ከሐይል አሰላለፍ ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት።የጠላትን ሐይል ለመግደል ከመተኮስ በፊት በሌላ መንገድ መከላከል በሚቻልበት ጊዜ ሥለሚወደዉ እርምጃ ከአፍቃኒስታን ጓዶች ጋር በመቀናጀት መወሰን ይቻላል።»

ሕጉ እንዲቀየር ያስፈለገዉ ሰሜናዊ አፍቃኒስታንን ጨምሮ የሐገሪቱ ወታደራዊ ሚዛን በመለወጡ ነዉ።የታሊባን ደፈጣ ተዋጊ ሐይላት ኩንዱስ በሠፈረዉ በጀርመን ሠራዊት ላይ የሚያደርሱት የሮኬት እና የመንገድ ዳር ቦምብ ጥቃት ባለፉት ጥቂት ወራት ዉስጥ እየተበራከተ ነዉ።በተለይ የአፍቃኒስታን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጊዜዉ እየተቃረበ በመጣበት ባሁኑ ጊዜ በጀርመን ጦር ሠፈር፥ የሚደርሰዉ የሮኬትና የቦምብ ጥቃት እያየለ ነዉ።

የፌደራላዊዉ ጦር ማሕበር ሊቀመንበር ኮሎኔል ኡልርሽ ኪርሽ እንደሚሉት የጠላት ሐይል የሥልት ለዉጥ ሳያደርግ አልቀረም።

«አፍቃኒስታን ዉስጥ የጠላት ሐይል አዲስ ሥልት እየተከተለ ነዉ።ብልሐት የተሞላበት የዉጊያ ሥልት እየተከተለ ነዉ።ተጠባባቂ ሐይል ማከማቸት እየተሳከለት ነዉ።በቅርብ ርቀትና ለረጅም ጊዜ የመዋጋት አቅምም እያዳበረ ነዉ።ይሕ አዲስ ብቃት ነዉ።አዲስ መጠናከርም ነዉ።»

ኮሎኔል ኪርሽ በአዲስ ሥልት፥ በአዲስ ሐይልና ብቃት ተጠናከረ ያሉትን የደፈጣ ተዋጊዎች ሐይል ለመቋቋም የጀርመን ሠራዊት እስከ ቅርብ ጊዜ የሚመራበት ጥብቅ ሕግ መሻሻል እንዳለበት ብዙዎች ያምናሉ።አዲሱን ሕግ ወታደሮቹ በቀላሉ እንዲረዱት በግልፅ ቋንቋና ወታደሩ ባለበት ሥፍራ ሆኖ መልዕክቱን መገንዘብ እንዲችል ባጫጭር ሰነድ የተዘጋጀ ነዉ።

ይሁንና አዲሱን ሕግ የሚቃወሙ ሐይላትም አልጠፉም።ወታደሩ ጠላት በሚለዉ ላይ እንዲተኩስ በተፈቀደለት ቁጥር የሚያደርሰዉና የሚደርስበት አደጋም ይባባሳል ባዮች ናቸዉ።

Daniel Sceschkewitz/Negash Mohammed/AA

Audios and videos on the topic