የአፍሪቃ የእርሻ ልማትና ተሃድሶ | ኤኮኖሚ | DW | 27.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ የእርሻ ልማትና ተሃድሶ

በርሊን ውስጥ ባለፈው ሰንበት በተካሄደ ዓለምአቀፍ የአርሻ ሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ጭብጥ የአካባቢ አየር ጥበቃ ጥረትን ለማንቀሳቀስ ከአንድ አጠቃላይ የሃሣብ ስምምነት ተደርሶ ነበር። በጉባዔው ግንዛቤ መሠረት የአርሻ ልማት የአካባቢ አየር ችግሮች መፍትሄ አንድ አካል እንጂ የችግሩ መንስዔ ብቻ ሆኖ መታየቱ መቀጠል የለበትም።

default

በተለይም በታዳጊው ዓለም ከአየር እንክብካቤ ተያይዞ በሚካሄድ የእርሻ ልማት ቁጥሩ እያደገ ለሚሄደው ሕዝብ የበለጠ ምግብ ማምረት እንደሚቻል ጠበብት ይናገራሉ። እርግጥ ይህ የሚሆነው አፍሪቃንም ጨምሮ የእርሻው ልማት በዘመናዊ መልክ ሲዳብር ነው። ከዚሁ በተጨማሪ የዓለም ንግድ ስርዓትም የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጥ መንገድ መቀናጀት አስፈላጊ መሆኑ ይታመንበታል።

ሁል ገብ በመሆን ፋንታ አንድ ዓይነት የእርሻ ምርትን ለውጭ ገበዮች በማቅረብ ላይ ጥገኛ የሆኑት የአፍሪቃ አገሮች ብዙዎች ናቸው። በዚህ መሰል ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙት መካከል ደግሞ ለምሳሌ ስዋዚላንድም አንዷ ናት። ሰባ ከመቶው የአገሪቱ ሕዝብ በእርሻ ተግባር፤ በተለይም በሸንኮራ አገዳ ተክል ላይ የተሰማራ ሲሆን አብዛኛው የሚኖረውም በከፋ የድህነት ሁኔታ ነው። የስኳር ኢንዱስትሮው በአገሪቱ ራመድ ያለው ዘርፍ ከመሆኑም በላይ የሚያስገኘው ገቢ ከጠቅላላው ዓመታዊ ብሄራዊ ምርት ሩቡን ድርሻ ይይዛል። ዋነኛው የምርቱ ገዢም 150 ሺህ ቶን የሚያህለውን የሚቀበለው የአውሮፓ ሕብረት ነው። ይሁን እንጂ ባለፈው ሰንበት በዚህ በጀርመን በተጠቃለለው አረንጓዴ ሣምንት የተሰኘ ዓለምአቀፍ የእርሻ ምርት ትዕይንት ላይ የተገኙት የስዋዚላንድ የእርሻ ሚኒስትር ክሌመንት ዲያሚኒ እንዳሉት የዓለምአቀፉ ፉክክር መጠናከር ለአገራቸው ተጨማሪ ችግር እየሆነ መሄዱ አልቀረም።

“ከ 1991/92 የምርት ወቅት ወዲህ ስዋዚላንድ መልሶ-መላልሶ በከባድ ሙቀት፣ ድርቅና የምርት ማቆልቆል ስትጎዳ ነው የቆየችው። ባዕድ የተክል አይነቶች በምድሩ ሰፍረዋል። በበኩላችን በተሻለ የመስኖ አጠቃቀም ዘዴና ድርቅን የሚቋቋሙ ተክሎችን በማልማት ሁኔታውን ለመቋቋም እየጣርን ነው”

የስዋዚላንድ ሃቅ ብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች የሚገኙበትን ተመሳሳይ ሁኔታም ያንጸባርቃል። በዓለምአቀፉ የእርሻ ምርት ንግድ ያላቸው ሚና ከሞላ ጎደል በሙሉ በውጭ ንግድ ላይ ብቻ የተወሰነ ነው። ከስኳር ሌላ በተለይም ቡና፣ ኮኮና ጥጥ ዋነኞቹ ለውጭ የሚቀርቡት የገበያ ምርቶች ሆነው ይገኛሉ። ሆኖም ይህ የአንድ-ወጥ ዘር አመራረት ዘይቤ የመሬቱን ልምላሜ እየመጠጠና የሚሰጠውንም ፍሬ እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው። በዚሁም የተነሣ የአፍሪቃ የእርሻ ልማት ብቃት እየተገታ መምጣቱ አልቀረም። የምርታማነት ዝቅተኝነት፣ የመዋዕለ-ነዋይ እጥረትና የአቅርቦት ጉድለት የአፍሪቃ አርሶ-አደር ራሱን በራሱ አቅም እንዳይቀልብ ነው ያደረገው። በጀርመን የምገባ፣ የእርሻ ልማትና የተጠቃሚዎች ደህንነት ጥበቃ የሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ዴኤታ እንደሆኑት እንደ ጌርድ ሙለር ከሆነ በመሠረቱ ይህ ሁሉ ሊሆን ባልተገባ ነበር። ባለሥልጣኑ አፍሪቃ ራሷን ለመቀለብና ረሃብን ለማሸነፍ ብቃት አላት ባይ ናቸው።

“ለዚሁ ቁልፉም የትምሕርት ተሃንጾ ነው። ይህም የተወሰኑ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ሣይሆን ሰፊውን ሕብረተሰብ፤ በተለይም የገጠሩን ሕዝብ ሊያዳርስ ይገባል። ታዲያ አዲሱ የእርሻ ልማት ፖሊሲ በዚህ ረገድ ወሣኝ ጥርጊያ መክፈት መቻሉ ግድ ነው። በሕዝብ ላይ የሚደረግ መዋዕለ-ነዋይ፤ ማለት ሥልጠና መስጠቱ፣ የመሬት፣ የውሃ ወይም የተክሎች አያያዛችን፣ ዘመናዊ ቴክኒክን በሥራ ላይ የምናውልበት ሁኔታም ይህን ልምድ አሳልፎ መስጠቱ ገቢር መሆን ይኖርበታል። እንዲህ ከሆነ በአፍሪቃ አገሮችም አረንጓዴ ዓብዮትን ልናስነሣ እንችላለን”

የዓለም ሕዝብ ቁጥር እ.ጎ.አ. እስከ 2050 ዓ.ም. ድረስ፤ ማለት በሚቀጥሉት አርባ ዓመታት ውስጥ ወደ ሶሥት ሚሊያርድ ገደማ እንደሚያድግ ነው የሚገመተው። አብዛኞቹ የሚኖሩትም አፍሪቃን ጨምሮ በታዳጊው ዓለም ይሆናል። ከዚህ አንጻር ምርታማ፣ ለገበያ ፉክክር ብቁ የሆነና ከአካባቢ አየር ለውጥ ጋር ራሱን ያጣጣመ የእርሻ ልማት ማስፈኑ መሟላት ያለበት የሕልውና ጥያቄ ነው። ይሁንና የወደፊቱ የእርሻ ልማት ዘይቤ ምን መልክ ሊይዝ ይገባዋል? በመለስተኛ ገበሬዎች ደረጃ ወይስ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚካሄድ ወይም ደግሞ በሁለቱ መካከል ያለ የምርት ዘዴ፤ ጠበብትን ብዙ ማነጋገሩን የቀጠለ ጉዳይ ነው። እንግዲህ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ ማለት ነው። ሆኖም ግን የተባበሩት መንግሥታትን የዓለም የእርሻ ዘገባ በማርቀቅ የተባበሩት ጀርመናዊው የእርሻና የልማት አዋቂ ሃንስ ሄረን እንደሚሉት ቢቀር የሚከተለው መሆን የለበትም።

“ሕዝብ በረሃብ በመጠመዱ የተነሣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ማምረት ይፈለጋል። በመሆኑም ማዳበሪያዎች፣ የተባይ መከላከያዎችና አዳዲስ ዘሮች ጥቅም ላይ ይውላሉ። እርግጥ በዚህ በፍጥነት ውጤት ለማግኘት ይቻል ይሆናል። ሆኖም ግን ችግሩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዘዴው መክሽፉ ላይ ነው። ማዳበሪያዎች ይወደዳሉ፣ ገበዮች በምርቶች ይሞላሉ፣ ዋጋም እንዲሁ ያቆለቁላል። ሁሉም ነገር እንደገና ቀድሞ ወደነበረበት ደረጃ ይመለሳል ማለት ነው። ስለዚህም ቀጣይነት ባለው መልክ ማምረት የሚቻልበትን ሁኔታ የግድ መፍጠር ያስፈልጋል። ገበሬዎች አስተሳሰባቸውን እንዲቀይሩ፣ ልምዳቸውን ከዘመናዊው ጥበብ መጣመር እንዲችሉም መረጃና ሥልጠና መስጠቱ ግድ ነው”

ሃንስ ሄረን አያይዘው እንደሚያስረዱት ይሁንና ይህ በተግባር ቀላል ነገር አይደለም። አፍሪቃ ውስጥ ሰፊ ገበያ የሚታያቸው ታላላቅ የዘርና የተባይ መከላከያ መድሃኒት አቅራቢዎች በቀላሉ የሚገፉ ሆነው አይገኙም።

“የፖለቲካው ባለሥልጣናት ከግሉ ዘርፍ ይተባበራሉ። ይህ ደግሞ ሁሉም ቦታ ያለ ነው። ታላላቁ ኩባንያዎች ባየርን፣ ቢኤስኤፍን፣ ሞንሣንቶንና ሲንጌንታን የመሳሰሉት እጅግ ሃያል ከመሆናቸው የተነሣ እኔ ራሴ እንዳየሁት በልማት ፖሊሲ ላይም ብርቱ ተጽዕኖ ነው ያላቸው። ታዲያ ይህ የግድ መለወጥ ይኖርበታል። አሁን ማድረግ ያለብን ለሰውልጅ፣ ለዓለም የሚጠቅመውን እንጂ ለኤኮኖሚው ዘርፍ የሚበጀውን ብቻ አይደለም”

ለባለሙያው የመጀመሪያው ጠቃሚ ዕርምጃ የመሬትን ፍሬያማነት ማዳበር ነው። እርሳቸው እንደሚሉት ይህ በቀላሉ በተወሰነ አያይዝና በተፈጥሮ ማዳበሪያ ሊደረስበት ይችላል። ጥቅም ላይ በሚውልበት ቦታ ሊመረትም የሚችል ነው። ጥሩ መሬት ድርቅን በመቋቋምና ለምሳሌ በጎርፍ ጊዜ የበለጠ ውሃ በመሳብም ጠቀሜታ አለው። ሃንስ ሄረን የተባለው ተግባራዊ ቢሆን ምርትን በፍጥነት በሶሥትና በአራት ዕጅ ከፍ ለማድረግ ይቻላል ባይ ናቸው። ከዚሁ በተጨማሪ ይህንኑ ግንዛቤ ለአፍሪቃ ገበሬ ማሳወቁም አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። የቡርኪና ፋሶ የእርሻ ሚኒስትር ሎራን ሤዶጎ እንዲያውም ወደፊት ራመድ በማለት የገበሬውን አስተሳሰብ ለመለወጥ ነው የሚፈልጉት።

“የአፍሪቃን ገበሬ በመጀመሪያ ደረጃ ወደ እርሻ አምራች ኩባንያነት መለወጥ ይኖርብናል። ሌላ የአስተሳሰብ ዘይቤ ሊኖረው የሚገባም ነው። እና የጠቅላላው ሂደት አንድ አካል የመሆን ስሜትን ማዳበሩ ግድ ይሆናል። ገበሬው የሠለጠነ ሠራተኛና ምርቱን የሚያመላልሱ ሰዎችም ያስፈልጉታል። መሬቱም መኪናውም ያውልህ ብለን ከአንድ ሰው ሁሉን እንዲገነባ ልንጠብቅ አንችልም። ይህ ጨርሶ የማይሰራ ነገር ነው”

የሆነው ሆኖ ሤዶጎ ይህን ሁሉ ለማራመድ የገንዘብ ችግር መኖሩንም አላጡትም። እርግጥ የአፍሪቃ መንግሥታት መሪዎች ከዘጠኝ ዓመት ገደማ በፊት በተቋቋመ አዲሰ የአፍሪቃ ልማት ሽርክና፤ በአሕጽሮት ኔፓድ በተሰኘ መድረካቸው በያመቱ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው አሥር በመቶውን ድርሻ ለእርሻ ልማት ለማዋል መስማማታቸው ,ይታወሣል። ግን የተባለው ሁሉ እስካሁን ገቢር ሲሆን አልታየም። ይልቁንም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው ዓለም ዕርዳታውን እንዲያጠናክር እንደገና ጥሪ መደረጉ ነው የቀጠለው። ይህ በተለይም በኮፐንሃገኑ ዓለምአቀፍ የአካባቢ አየር ጉባዔ ዋዜማና አሁንም በማግሥቱ ይበልጥ ተጠናክሯል። ውጤቱ በተጨባጭ ምን እንደሚሆን ለጊዜው ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው። እስከዚያው የአፍሪቃ አገሮች የእርሻ ይዞታቸውን ዘመናዊ ለማድረግና ሁኔታውን ለማሻሻል የራሳቸውን የቤት ሥራ ቢያከናውኑ ይሄው ጠቃሚ ዕርምጃ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።

በሌላ በኩል የአፍሪቃን የእርሻ ልማት ይዞታ ለማሻሻልም ሆነ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፍትሃዊ የሆነ የገበያ ሁኔታን ማመቻቸቱን ይጠይቃል። በብዙዎች አገሮች ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ረሃብ ማሸነፉ በዓለም ንግድ አቀነባበር ሁኔታ ላይ ጥገኛ መሆኑም ዛሬ ሰፊ ዕውቅናን ያገኘ ጉዳይ ነው። ይሁንና በዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር ዙር እንደሚታወቀው የገበያውን ሁኔታ የማለዘቡ ሃሣብ አንዳች የረባ ዕርምጃ ወደፊት ፈቀቅ አላለም። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የእርሻ ድጎማቸውን ለመቁረጥም ሆነ ታዳጊ አገሮች ወደ ገበዮቻቸው እንዲዘልቁ ለማድረግ ፖሊሲያቸውን በሚገባ ለማለዘብ ብዙም ፈቃደኛ አይደሉም። የታዳጊው ዓለም ገበሬ ከድህነት እንዲላቀቅ ከተፈለገ ችግሩ መፍትሄ ማግኘቱ ግድ ነው። አለበለዚያ አርሶ-አደሩ ሕዝብ ከዓለምአቀፉ ዕርምጃ እንደተገለለና ድሃ እንደሆነ ይቀጥላል። በአጠቃላይ የአፍሪቃን እርሻ ልማት በዘመናዊ ሁኔታ ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት ፍትሃዊ ንግድን ማስፈኑም ቁልፍ ጉዳይ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን/ተክሌ የኋላ

ተዛማጅ ዘገባዎች