የአፍሪቃ ስደተኞችና ቀይ መስቀል በካናሪ ደሴቶች | የጋዜጦች አምድ | DW | 29.08.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የአፍሪቃ ስደተኞችና ቀይ መስቀል በካናሪ ደሴቶች

ጀልባቸው ለሰጠመባቸው ስደተኞች የደረሰው የስፓኝ ቀይመስቀል መርከብ

default

በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚገኙት የ Kanari ደሴቶች የዘንድሮውን ያህል የአፍሪቃ ስደተኛ ጎርፎባቸው አያውቅም ። ከነዚህ ስደተኞችም ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ በመቶው ወጣት ወንዶች ሲሆኑ የመጡትም ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ነው ። ወደ አውሮፓ መሻገርን ዓላማቸው አድርገው አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ትተው ወደደሴቶቹ በጀልባ ጉዞ ከሚጀምሩት ከግማሽ በታች የሚሆኑት ናቸው የሚሳካላቸው ። ጉዞው የተቃናላቸው ከብዙ መንገላታት በኃላ የካናሪ ደሴት ደቡባዊ ኬላ ከሆነችው Teneriffa ይደርሳሉ ። የዶቼቬለዋ Sandra Petersmann ከ Los Cristianos እንደዘገበችው Los Cristianos ወደብ የሚገኘው የስፓኝ ቀይ መስቀል እዚያ ለሚደርሱት አዳዲስ ስደተኞች ያለማቅዋረጥ የአርባ ስምንት ሰዓት የህክምና ዕርዳታ ይሰጣል ። “ሁላችንም በጣም ደክሞናል ለሊቱን በሙሉ ያለአንዳች ዕንቅልፍ ነው ያሳለፍነው ። ቀጣዩ ጀልባ ከመምጣቱ በፊት ዛሬ ከሰዓት በኃላ ትንሽ ዕረፍት እናገኛለንለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን ።”
በጀልባ ወደ ቴነሪፋ ለሚመጡት የአፍሪቃ ስደተኞች የህክምናና የምግብ ዕርዳታ የሚለግሰው የስፓኝ ቀይመስቀል ቡድን መሪ ኦስትን ቴይለር ናቸው ስለ ዕረፍት የለሹ የረድኤት ተግባራቸው የተናገሩት ። በቴይለር የሚመራው የቀይመስቀል ቡድን የአርባ ስምንት ሰዓታት ዕርዳታ ይሰጣል ። በዕለቱ ከምዕራብ አፍሪቃ የመጡ አምስት ጀልባዎች በወደብ ጠባቂዎችና በህይወት አድን ሰራተኞች ዕርዳታ ወደ ሎስ ክርስቲያኖስ ወደብ ገብተዋል ። በአማካይ ወደ ዘጠና የሚሆኑ ስደተኞች ናቸው በጀልባዎቹ የመጡት ። አብዛኛዎቹ የማይጨበጥ ተስፋ ተሞልተው ነው ከሀገራቸው የወጡት ። ምኞታቸውም ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የሚገናኝ አይደለም ። እዚያ እስከሚደርሱ የሚሰቃዩትን ከዚያም በኃላ የሚጠብቃቸውን እንግልት ከመነሻቸው አያውቁትም ።
ድምፅ
“አንዴ አውሮፓ ከደረሱ ስራ ማግኘት ቀላል ነው ብለወ ነው የሚያምኑት ። ስራ የሚያገኙ ይመስላቸዋል ። አገር ቤት ላሉት ቤተሰቦቻቸው ቀለብ መሸመቻ መላክ የሚቻላቸው አድርገው ነው የሚያስቡት ። ሆኖም በአጠቃላይ ስለዚህ ጉዳይ ለኛ ብዙም አይነግሩንም ። ምክንያቱም እዚህ ሲደርሱ እጅግ ተዳክመው ነው የምናገኛቸው ። እጅግ በጣም ይፈራሉም ። ሁሉ ነገር ለነርሱ አዲስ ነው ። እዚህ ከደረሱ በኃላ ምን እንደሚያጋጥማቸውም አያውቁም ። “
እንደ ስፓኝ ቀይመስቀል ቡድን መሪ ቴይለር ብዙዎቹ ከተለያየ የጤና ችግር ጋር ነው የሚመጡት ። የሚሳፈሩባቸው ጀልባዎች የሚጭኑት ሰው መጠን ከጀልባዎቹ አቅም በላይ በመሆኑ ለብዙ ቀናት ተጨናንቀውና ተፋፍገው በመቆየታቸው ቆዳቸው ተላልጦ የሚደርሱ ጥቂት አይደሉም ። የሚጠጣ ውሀ ሳያገኙም ብዙ ቀናት ለመጓዝ በመገደዳቸውም ብዙዎቹ የሰውነታቸው ውሀ ይሟጠጣል ። እንደ ቴይለር ይህ የጀልባ ስደተኞች ዋነኛ የጤና ችግር ነው ። እናም የቀይመስቀል ሰራተኞች በዚህ ሁኔታ ወደ ወደቡ ለሚደርሱት ስደተኞች ምግብ ውሀ እና የገላ መፀዳጃ ይሰጡዋቸዋል ። ቁስለኞችንም ያክማሉ ። ከመካከላቸው የትኛዎቹ ወደ ሆስፓል መሄድ እንዳለባቸውም ይወስናሉ ። ከዚያም ወደ ስደተኞች መጠለያ ከመግባታቸው በፊት ፖሊስ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ያቀርቡላቸዋል ። ስደተኞቹ አውሮፓ ለመሻገር እዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ ለምን ለመግባት ይወስናሉ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው ። መልሱን መናገር የሚችሉት በዚህ መልኩ ለመሰደድ የወሰኑት ግለሰቦች ቢሆኑም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያለፉትም ምክንያቱን ለማስረዳት ይሞክራሉ ። በስፓኝ ቀይመስቀል ቡድን ውስጥ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሰጠው የሰላሳ ሰባት ዓመቱ ሙሳ ከዓመታት በፊት የቱሪስት ቪዛ አግኝቶ ነበር ከሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ፓሪስ የገባው ። የቤተሰብ ሀላፊ የሆነው ሙሳ በኃላም ከፈረንሳይ ወደ ስፔይን ተሻግሮ ባለፈው ዓመት የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ ስፓኝ እየኖረ ነው ። ሙሳ በጀልባ የሚመጡት ስደተኞች ይህን ዓይነቱ ውሳኔ ላይ እንዴት እንደሚደርሱ ለማስረዳት ሞክሯል ።
ድምፅ
“እነዚህ ሰዎች ወደ ዚህ የሚመጡት በአገራቸው ምንም ዓይነት ተስፋ በማጣታቸው ነው ። እዚህ ለመምጣት በርካታ ገንዘብ የሚከፍሉበት ምክንያትም የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው ። ብዙዎቹ በአገራቸው ስራ አጥ ናቸው ። የጤናም ሆነ የማህበራዊ መድን አገልግሎት የላቸውም ። በዚህ የተነሳም በህይወታቸው ላይ የሚመጣውን አደጋ ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው ። እኔ የመጣሁት ከሴኔጋል ነው ። እናም እዚያ እንዴት እንደሚኖሩና ምን ጥለው እንደመጡም አውቃለሁ ። እኔም አገሬን ጥዬ የመጣሁት በተመሳሳይ ምክንያት ነው ።”
በዚህ ዓመት ብቻ ቁጥራቸው ከአስራ ስድስት ሺህ በላይ የሚገመት የምዕራብ አፍሪቃ ስደተኞች በትላንቲክ ውቅያኖስ አድርገው ካናሪ ደሴቶች ገብተዋል ። ሌሎች ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎች ከሞሪታኒያና ከሴኔጋል ወደቦች ወደ ደሴቶቹ ለመምጣት እየተጠባበቁ ነው ። እነ ቴይለርም ከአርባ ስምንት ሰዓታት በኃላ ወደ ረድኤት ተግባራቸው ይመለሳሉ ።

ተዛማጅ ዘገባዎች